የአዲስ አበባ ከተማ መስሪያ ቤቶች አገልግሎት የሚሰጡበትን ጊዜ፤ ወደ 16 ሰዓት ለማራዘም የሚያስችል ጥናት እየተደረገ ነው

በአማኑኤል ይልቃል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በስሩ ያሉ መስሪያ ቤቶች አገልግሎት የሚሰጡበትን ጊዜ ከስምንት ወደ 16 ሰዓት ለማራዘም የሚያስችል ጥናት እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ። ይህ ጥናት፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር የሚገኙ መስሪያ ቤቶችን የስራ ሰዓት ከጠዋቱ 2፡30 አስቀድሞ ለማስጀመር እና ከ11፡30 በኋላ እስከ ምሽት ለማስቀጠል ያቀደ ነው።  

ይህ ዕቅድ ይፋ የተደረገው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ፤ የከተማዋ መስሪያ ቤቶችን አገልግሎት አሰጣጥን አስመልክቶ ትላንት ሐሙስ ግንቦት 3፤ 2015 ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው ውይይት ላይ ነው። ይህ ቢሮ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር የሚገኙት 47 መስሪያ ቤቶች የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች አፈጻጸም የመከታተል ኃላፊነት በአዋጅ የተሰጠው ነው።

የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮው የከተማዋ መስሪያ ቤቶች አገልግሎቶች “በተገቢው ስታንዳርድ” መሰረት መሰጠታቸውን የማረጋገጥ ስራም ይሰራል። የከተማይቱን መስሪያ ቤቶች “አቅም ግንባታ ስራን የሚያሳልጡ ዘመናዊ አሰራሮች እና ተሞክሮዎች” ተግባራዊ እንዲሆኑ የማድረግ ስልጣንም በአዋጅ ተሰጥቶታል። ቢሮው በትላንትናው ዕለት ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው ውይይት ላይ የአገልግሎት ቅልጥፍናን ለመጨመር ሊከተል ያሰባቸውን አሰራሮች አስተዋውቋል።

አዲሶቹን አሰራሮች ለውይይቱ ተሳታፊዎች ያሳወቁት፤ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ሂክማ ከይረዲን ናቸው። ወ/ሮ ሂክማ በቀጣዩ በጀት ዓመት የአዲስ አበባ ከተማ መስሪያ ቤቶችን የስራ ሰዓት ከስምንት ወደ 16 ሰዓት ለማሳደግ “አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት” እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። “አንዳንድ ተቋማት ላይ ከሰዓት ጋር ተይይዞ ተገልጋዮች ተገፍተው የሚወጡበት” ሁኔታ መኖሩን የተናገሩት የቢሮ ኃላፊዋ፤ ይህም የከተማዋ መስሪያ ቤቶች በሚሰጡት አገልግሎት ላይ ቅሬታ መፍጠሩን አስረድተዋል። 

በፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ በአማካሪነት የሚሰሩት አቶ ኤፍሬም ግዛውም ተመሳሳይ ሃሳብ አንስተዋል። በአዲስ አበባ ከተማ መስሪያ ቤቶች ላይ በተደረጉ “የተገልጋይ እርካታ” ጥናቶች፤ ከህዝቡ ጥያቄ የሚነሳባቸው ጉዳዮችን መታየታቸውን አማካሪው ለ”ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “አንዳንድ ተቋማት አካባቢ አገልግሎቶችን ስናይ ወረፋ ይበዛቸዋል” ያሉት አቶ ኤፍሬም፤ ይህም የተቋማቱ አገልግሎት “የተደራሽነት ችግር” እንዳለበት ማመላከቱን ገልጸዋል። ይህን ችግር ለመቅረፍ በአማራጭነት ከቀረቡ መፍትሔዎች ውስጥ፤ ተቋማቱ አገልግሎት የሚሰጡበትን ሰዓት ማራዘም አንዱ መሆኑን አማካሪው አስረድተዋል።

“ ‘ሰዉ 2፡30 ለሚከፈት የመንግስት መስሪያ ቤት ለምን ሌሊት ይሰለፋል?’ [የሚል] ነው የእኛ ጥያቄ” የሚሉት አቶ ኤፍሬም ለዚህ አማራጭ መነሻ የሆኑትን አሁን ያሉ አሰራሮችን በማሳያነት ይጠቅሳሉ። “መታወቂያ ለማውጣት ለምን ተገልጋይ ቀድሞ ይሄዳል? ለምን ሰራተኛው ቀድሞ አይገባም? [መስሪያ ቤቶች] 11፡30 ሲሆን በቃ ብለው የሚዘጉ ከሆነ ለምን የስራ ሰዓታቸውን አራዝመው አይሰሩም?” ሲሉ የሚጠይቁት አማካሪው፤ የከተማይቱ መስሪያ ቤቱ ሰራተኞች እስከ ማታ ቆይተው አገልግሎት ቢሰጡ ችግሩን ለመቅረፍ ያስችላል የሚል እምነት አላቸው። 

ይህ አይነቱ አሰራር ባደጉ ሀገራት ውስጥ በሚገኙ ትልልቅ ከተሞች ውስጥ የተለመደ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ኤፍሬም፤ የስራ ሰዓቱን በማራዘም በሌሎች ስራዎች ላይ የሚውሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ባመቻቸው ሰዓት አገልግሎት እንዲያገኙ መታሰቡን አመልክተዋል። የከተማዋ መስሪያ ቤቶችን የስራ ሰዓት በማራዘም የከተማዋን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ “ማነቃቃትም” ታሳቢ የተደረገ አንዱ ጉዳይ መሆኑንም አክለዋል። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመስሪያ ቤቶቹን የስራ ሰዓት ለማራዘም ቢያቅድም፤ በስሩ ያሉ ሰራተኞች ተጨማሪ የስራ ሰዓታትን እንዲሰሩ የማድረግ ሀሳብ እንደሌለው አማካሪው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። በ2010 ዓ.ም የወጣው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ፤ የሰራተኞች የስራ ሰዓት በሳምንት ከ39 ሰዓታት መብለጥ እንደሌለበት ደንግጓል። ይሁንና የመንግስት ሰራተኞች የስራ ሰዓት “እንደየስራው ሁኔታ” እንደሚወሰን አስፍሯል።

“አንድ ሰው በቀን ስምንት ሰዓት ይሰራል የሚለው ድንጋጌ አለ። ይሄንን ልንጥስ አንችልም” የሚሉት አቶ ኤፍሬም፤ እየተደረገ ያለው ጥናት “በአማራጭ የስራ ሰዓት ሰራተኞችን በተለያየ መንገድ መድቦ፣ ዜጎች በተራዘመ ሰዓት ውስጥ አገልግሎት እንዲያገኙ” የማድረግ ሀሳብ ያለው መሆኑን አስረድተዋል። አማካሪው ይህንን ሲያብራሩ “ለምሳሌ በሺፍት ልናደርገው እንችላለን። ለምሳሌ [ሰራተኛው] ጠዋት አንድ ሰዓት ቢገባ እስከ ስምንት ሰዓት ይሰራል። ከስምንት ሰዓት በኋላ ደግሞ እስከ ማታ ይሰራል። ሁለት አማራጭ አለ ማለት ነው። ስለዚህ 16 ሰዓት ብናደርገው፤ አንድ ሰው 16 ሰዓት ይሰራል ማለት አይደለም” ብለዋል። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመስሪያ ቤቶቹን የአገልግሎት ሰዓት የማራዘም እቅድ ቢኖረውም፤ ገና በጉዳዩ ላይ ጥናት እያደረገ መሆኑን እና “ውሳኔ ላይ ያልተደረሰበት” እንደሆነ አማካሪው ገልጸዋል። በጥናቱ “የሰራተኛው ፍላጎት፣ የከተማ አስተዳደሩ አቅም፣ መተግበር ያለበት አይነት እና የአደረጃጀት አይነቶች” እንደሚታዩ አቶ ኤፍሬም ጠቁመዋል። እስካሁን ባለው የጥናት ደረጃ የመስሪያ ቤቶቹ የስራ ሰዓት ሲራዘም፤ የከተማ አስተዳደሩ ካሉት 163 ሺህ ሰራተኞች ውጪ ተጨማሪ ሰራተኞች የመቅጠር ሀሳብ እንደሌለውም አቶ ኤፍሬም ተናግረዋል። 

የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ የሚካሄደው ጥናት በሶስት ወር ገደማ ውስጥ ለማጠናቀቅ የጊዜ ሰሌዳ መቀመጡን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተናገሩት አቶ ኤፍሬም፤ ትክክለኛውን የማጠናቀቂያ ጊዜ ግን እርግጠኛ ሆኖ መናገር እንደማይቻል አስረድተዋል። “ዝርዝር ጉዳዮቹ ታይተው ይህ [አሰራር] ተግባራዊ መሆን ‘አለበት? የለበትም?’ የሚለውን ጥናቱ ይመልሳል። ከጥናቱ በኋላ የሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች ቀርቦላቸው ይወያዩበታል። ከተወያዩበት በኋላ ደግሞ እንደገና ‘ይፈጸም? አይፈጸም?’ የሚለውን በዚያው የምንወስንበት ይሆናል” ሲሉ አሰራሩን ለመተግበር የሚኖሩ ሂደቶችን ዘርዝረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)