በአማኑኤል ይልቃል
በአዲስ አበባ ከተማ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ አለባቸው አሞኜ፤ ቢሯቸው ውስጥ በጥይት ተመትተው ህይወታቸው ማለፉን የወረዳው ኮሚዩኒኬሽን እና የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታወቁ። ግድያውን ፈጽመዋል የተባሉት ግለሰብ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደዋሉም ተገልጿል።
በዚህ ዓመት ጥቅምት ወር የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው የተሾሙት አቶ አለባቸው፤ ግድያው የተፈጸመባቸው ዛሬ አርብ ግንቦት 4፤ 2015 ረፋድ ላይ መሆኑን የወረዳው የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ንዋይ ተሰማ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ዋና ስራ አስፈጻሚው ካዛንቺስ በተለምዶ “ሀናን ዳቦ ጀርባ” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው የወረዳው ጽህፈት ቤት ቢሯቸው ውስጥ ባሉበት ግድያ የተፈጸመባቸው፤ “ባለ ጉዳይ ሆኖ በገባ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አስተባባሪ” ግለሰብ መሆኑን የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊው ገልጸዋል።
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ባወጣው መግለጫ፤ አቶ አለባቸው “በቢሮአቸው ቁጭ ብለው የህዝብ አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት ከአንድ ተገልጋይ በደረሰባቸው ጥቃት” ህይወታቸው ማለፉን አረጋግጧል። ዋና ስራ አስፈጻሚው በጥይት የተመቱት “በግራ ልብ አካባቢ” መሆኑን የገለጹት የወረዳው የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ፤ ከጥቃቱ በኋላ በአቅራቢያው ወደሚገኘው ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ለህክምና ቢወሰዱም አምስት ሰዓት ገደማ አካባቢ መሞታቸውን ተናግረዋል።
“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ሰራተኛ፤ አቶ አለባቸው ህይወታቸው ማለፉን እና ፖሊስ ለምርመራ አስከሬኑን ከሆስፒታሉ መውሰዱን አረጋግጠዋል። የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት ዋና ስራ አስፈጻሚውን በመግደል የተጠረጠሩት ግለሰብ፤ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደሚገኙ የወረዳው የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ንዋይ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ዛሬ ከሰዓት ባወጣው መግለጫ ግድያውን ፈጽመዋል ያላቸው ግለሰብ፤ “በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የካዛንቺስ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት የቀጠና ኦፊሰር አባል” መሆናቸውን ገልጿል። የፖሊስ አባሉ “በታጠቁት ሽጉጥ” ዋና ስራ አስፈጻሚውን የገደሉት፤ “ጥያቄዬ እንዳይፈጸም የከለከልከው አንተነህ” በሚል ምክንያት እንደሆነ የአዲስ አበባ ፖሊስ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል። ስማቸው ያልተጠቀሰው እኚሁ ተጠርጣሪ፤ በቁጥጥር ስር ውለው “ምርመራው እየተጣራ” የከተማይቱ ፖሊስ መሆኑን አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)