ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች፤ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ በአፋጣኝ እንዲፈታ ጥሪ አቀረበ

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይን በአፋጣኝ እንዲፈቱ ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ሲፒጄ (CPJ) ጥሪ አቀረበ። መቀመጫውን በአሜሪካ ኒውዮርክ ያደረገው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ትላንት አርብ ባወጣው መግለጫ “በአገር ውስጥና በውጪ ያሉ የፕሬስ አባላትን ማዋከብ እንዲያቆሙ” ለኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጥሪ አስተላልፏል።

“የአማራ ድምጽ” የተባለው በዩቲዩብ የሚተላለፍ የግል መገናኛ ብዙኃን መስራች እና አርታኢ የሆነው ጎበዜ፤ ሚያዝያ 28፤ 2015 በጅቡቲ በቁጥጥር ስር መዋሉን የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ይፋ እንዳደረጉ ሲፒጄ በመግለጫው ጠቅሷል። የጋዜጠኛው ጠበቃ አዲሱ አልማው፤ ጎበዜ ከጅቡቲ ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፎ መሰጠቱን እና በአዲስ አበባ በሚገኘው የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ በእስር ላይ እንደሚገኝ ለሲፒጄ ተናግረዋል።

“የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይን ዝም ለማሰኘት እና ለመበቀል በድፍረት ድንበር ተሻግረዋል” ያሉት ከሰሃራ በረሃ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት የሲፒጄ ተወካይ ሙቶኪ ሙሞ፤ እስሩ “በስደት ደህንነት ፈልገው ከሀገራቸው በሄዱ ጋዜጠኞች ላይ ስጋት ይፈጥራል” ብለዋል። “ጎበዜ ያለመዘግየት ሊፈታ ይገባል” ያሉት የሲፒጄ ተወካይ የኢትዮጵያ እና የጅቡቲ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር ስለዋለበት እና ተላልፎ ስለተሰጠበት ሁኔታ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

ፎቶ፦ ፌደራል ፖሊስ

የፌደራል ፖሊስ በፌስቡክ ገጹ በተሰራጨ የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል መግለጫ፤ ጎበዜ በጅቡቲ ባለስልጣናት እና በዓለም አቀፉ ፖሊስ ድርጅት (ኢንተርፖል) ትብብር በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን አስታውቋል። በኢ-ሜይል ለሲፒጄ ምላሽ የሰጡ አንድ የኢንተርፖል ተወካይ፤ ዓለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት “በዳታቤዙ” ስለ ጎበዜ ምንም ዓይነት መረጃ እንደሌለው እና ተቋሙ “ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር የማዋልም ሆነ አሳልፎ የመስጠት ስልጣን እንደሌለው” መግለጻቸውን የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቱ አስታውቋል።

ጋዜጠኛ ጎበዜ ስለታሰረበት እና ወደ ኢትዮጵያ ስለተመለሰበት ሁኔታ ከሲፒጄ ጥያቄ የቀረበላቸው የፌደራል ፖሊስ ቃል አቀባይ ጄይላን አብዲ፤ ምላሽ ሳይሰጡ መቅረታቸውን ድርጅቱ ገልጿል። ይሁንና ጎበዜ “በአማራ ክልል ከአንድ ባለስልጣን ሞት ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር መዋሉን፤ በሽብርተኝነት መጠርጠሩን እና በጋዜጠኝነት ስራው ዒላማ አለመደረጉን” ቃል አቃባዩ በጽሁፍ መልዕክት እንደገለጹለት ሲፒጂ በመግለጫው አካትቷል።

ሲፒጄ ከዚህ በተጨማሪም ከጅቡቲ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሳኢድ ኑህ ሐሰን እና ከሀገሪቱ የህዝብ ደህንነት ምክትል ዳይሬክተር ኦማር ሀሰን፤ ተጨማሪ ማብራሪያ ጠይቆ ምላሽ እንዳላገኘ አስታውቋል። ድርጅቱ ለጅቡቲ የማስታወቂያ ሚኒስትር ሬድዋን አብዱላሂ ባህዶ የጽሁፍ መልዕት ሲልክ “ቁጥሩ አይታወቅም” የሚል ምላሽ እንዳገኘም ገልጿል። ለህዝብ ይፋ በሆነ የጅቡቲ ፖሊስ ስልክ ቁጥር ከሲፒጄ ጥያቄ የቀረበላቸው ግለሰብ በበኩላቸው፤ ስለ ጎበዜ ጉዳይ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ መመለሳቸውን ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች በመግለጫው አስፍሯል። 

ፎቶ፦ ፌደራል ፖሊስ

ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ወደ ጅቡቲ የሸሸው፤ የጸጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ሚያዝያ 22 ቀን 2015 ያወጣውን መግለጫ ተከትሎ መሆኑን ጠበቃው መናገራቸውን ሲፒጄ በመግለጫው ጠቅሷል። የጋራ ግብረ ኃይሉ በዚሁ ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ ጎበዜን “ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ለማፍረስ እና በሽብር ወንጀል” ከጠረጠራቸው እና ከሚፈለጉ 11 ግለሰቦች አንዱ መሆኑን አስታውቆ ነበር። በተመሳሳይ ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ከዋሉ ግለሰቦች መካከል ቢያንስ አምስቱ ጋዜጠኞች መሆናቸውን የመብት ተሟጋቹ በመግለጫው ጠቁሟል። 

ከጎበዜ በተጨማሪ መግለጫው በስም የጠቀሳቸው የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፤ ዳዊት በጋሻው፣ ገነት አስማማው፣ መስከረም አበራ፣ ቴዎድሮስ አስፋው እና አሰፋ አዳነ ናቸው። ግንቦት 1 እና 2፤ 2015 በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የቀረበው ጋዜጠኛ ጎበዜ፤ ፖሊስ “በሽብር” እና “ስሙ ያልተገለጸ ታጣቂ ቡድን የፕሮፖጋንዳ ክንፍ በመምራት” እንደጠረጠረው መግለጹን ሲፒጄ በመግለጫው አንስቷል። የጋዜጠኛውን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ያደረገው ፍርድ ቤቱ፤ ለፖሊስ ተጨማሪ 14 የምርመራ ቀናት በመፍቀድ ለግንቦት 16፤ 2015 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱንም አክሏል። 

በጎበዜ ላይ በፖሊስ ለቀረቡት ውንጀላዎች መነሻ የሆኑ፤ “ምንም ዓይነት ይዘት ወይም እንቅስቃሴዎች” በግልጽ እንዳልቀረቡ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ በመግለጫው አመልክቷል። ጎበዜ በቁጥጥር ስር ከመዋሉ በፊት የሰራቸው ዘገባዎች፤ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት “ወደ ተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች እንዲገቡ” መወሰኑን ተከትሎ በክልሉ የነበሩ አለመረጋጋቶች ላይ ያተኮሩ እንደነበሩም ሲፒጄ አስታውሷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)