በአማኑኤል ይልቃል
የክልል መንግስታት ላጋጠማቸው የበጀት እጥረት፤ የፌደራል መንግስት ብድር መስጠት እንጂ ቀጥታ ድጋፍ ማድረግ እንደማይችል የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ተናገሩ። የፌደራል መንግስት “ደመወዝ የመክፈል ጫና ውስጥ ለገቡ” ክልሎች፤ ከሰባት ቢሊዮን ብር በላይ ማበደሩንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት፤ ትላንት ረቡዕ ግንቦት 9፤ 2015 ከተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ ላይ ነው። የሚመሩት የሚኒስቴር መስሪያ ቤትን የዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ለማቅረብ በፓርላማ ለተገኙት አቶ አህመድ ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል፤ ክልሎች የገጠማቸውን የበጀት እጥረት የተመለከተው አንዱ ነበር።
ጥያቄውን በንባብ ያቀረቡት ዶ/ር ሚልኪያስ አየለ የተባሉ የቋሚ ኮሚቴው አባል፤ ክልሎች በፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀመር መሰረት በጀት የሚደለደልላቸው መሆኑን አስታውሰዋል። ሆኖም “አንዳንድ ክልሎች” “ቀድሞ በነበረ የማዳበሪያ እዳ ምክንያት” የተደለደለላቸው በጀት “ሙሉ ለሙሉ እንዳማይተላለፍላቸው” ተናግረዋል። በዚህም ምክንያት ክልሎቹ “ደመወዝ መክፈል እንኳ እንዳልቻሉ” የጠቀሱት የፓርላማ አባሉ፤ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይህን ችግር ለመፍታት “ከአጭር ጊዜ አኳያ ምን አስቧል?” ሲሉ ጠይቀዋል።
ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ሚኒስትሩ አቶ አህመድ፤ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ ክልሎች ደመወዝ የመክፈል ጫና” ውስጥ መግባታቸውን አረጋግጠዋል። ይህ ችግር በተለይም በአዲስ ክልሎች ውስጥ የሚታይ ቢሆንም “አንዳንድ ነባር ክልሎችም ጭምር” ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን አንስተዋል። ሚኒስትሩ “ደመወዝ የመክፈል ጫና ውስጥ ገብተዋል” በሚል የጠቀሷቸው፤ ደቡብ፣ ሲዳማ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎችን ነው። የሶማሌ እና አፋር ክልሎችም ተመሳሳይ ችግር እንዳጋጠማቸው በገንዘብ ሚኒስቴር የትሬዠሪ ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ነጠሩ ወንድወሰን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
የክልሎች የበጀት እጥረት ጉዳይ፤ ከሁለት ወራት ገደማ በፊት በፓርላማ በተካሄደ ስብሰባ ላይም ተነስቶ ነበር። ስብሰባው የተጠራው፤ ወደ ምርጫ ክልሎቻቸው የተጓዙ የፓርላማ አባላት ከመራጮቻቸው ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች ወቅት በተነሱ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር ነበር። ከአማራ እና ከደቡብ ክልል የተመረጡ የፓርላማ አባላት አስተባባሪዎች፤ የተወከሉባቸው ክልሎች የሰራተኞችን ደመወዝ ለመክፈል መቸገራቸውን ካደረጓቸው ውይይቶች መረዳታቸውን ጠቅሰዋል።
ክልሎች ደመወዝ ለመክፈል እስከመቸገር የደረሰ የበጀት እጥረት ውስጥ እየገቡ ያሉት፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “አስተዳደራዊ ወጪያቸው ከፍ እያለ” በመምጣቱ ምክንያት እንደሆነ የገንዘብ ሚኒስትሩ በትላንትናው የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ አስረድተዋል። “በክልሎች እየተፈጠሩ ያሉ የመንግስት መዋቅር እና የሰው ኃይል ስብጥር እጅግ በጣም ገዝፏል” ያሉት አቶ አህመድ፤ በክልሎች የወረዳ መዋቅር ያለው የአስፈጻሚ ሰራተኛ፣ የተሿሚ እና የሚቀጠረው የሰው ኃይል “ብዙ” መሆኑን ተናግረዋል። “የሲቪል ሰርቪስ መጠኑ በሀገር ደረጃ በከፍተኛ ደረጃ ያበጠው በክልሎች ምክንያት ነው” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ክልሎች ይህ አይነቱ ችግር ቢያጋጥማቸው የገንዘብ ሚኒስቴርም ሆነ የፌደራል መንግስት “በቀጥታ ብር” መስጠት የሚችሉበት “አግባብ” እንደሌለም አስታውቀዋል። ገንዘብ ሚኒስቴር ለክልሎች ገንዘብ የሚያስተላልፈው “በበጀት አዋጁ በተቀመጠለት መሰረት” መሆኑን የጠቀሱት አቶ አህመድ፤ ይህም በበጀት ድጋፍ እና ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ በሚውል ድጋፍ አማካኝነት መሆኑን አስረድተዋል።
“ፐብሊክ ፋይናንስ አዋጁ በሚፈቅደው መሰረት እኛ በቀጥታ ብር መስጠት አንችልም። የፌደራል መንግስቱም የሚችልበት አግባብ የለም። እኛ የምንችለው ባለው አዋጅ መሰረት ማበደር ነው” ሲሉም አሰራሩን አብራርተዋል። በዚህ አሰራር መሰረት “በተለይ የከፋ ችግር ላለባቸው” ክልሎች በተለያዩ ጊዜያት “ከሰባት ቢሊዮን ብር በላይ” ብድር መሰጠቱን ተናግረዋል። “ከወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ጋር ተይይዞ ጫና” ለተፈጠረባቸው ክልሎችም፤ “የተለያዩ ብድሮች” መሰጠታቸውን ገልጸዋል።
የፌደራል መንግስት ለክልሎች ይህ አይነቱን ብድር እየሰጠ ያለው “ከክልል መንግስታቱ ጋር እና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በመነጋገር” በሚሰጥ አቅጣጫ መሰረት መሆኑንም አቶ አህመድ ለፓርላማው ቋሚ ኮሚቴው አባላት አስገንዘበዋል። የገንዘብ ሚኒስቴር፤ ክልሎች ከፌደራል መንግስት የተበደሩትን ገንዘብ መልሰው እንዲከፍሉ የማድረግ ኃላፊነት በአዋጅ እንደተጣለበትም አክለዋል። ሚኒስትሩ ይህን ሪፖርት ለተወካዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ከቀረቡ በኋላ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው በገንዘብ ሚኒስቴር የትሬዠሪ ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ነጠሩ፤ በአሁኑ ወቅት ክልሎች ያለባቸው ብድር “ወደ ስምንት እና ዘጠኝ ቢሊዮን ብር” ማሻቀቡን አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)