በሱዳን ግጭት ለተሰደዱ ሰዎች፤ በምዕራብ ጎንደር ዞን በ56 ሄክታር መሬት ላይ ቋሚ የመጠለያ ጣቢያ ሊገነባ ነው 

በአማኑኤል ይልቃል

በሱዳን እየተካሄደ ባለው የእርስ በእርስ ግጭት ሳቢያ፤ በየዕለቱ ከ800 በላይ ሰዎች በአማራ ክልል መተማ ዮሃንስ ከተማ በኩል ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ መሆኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን አስታወቀ። ለስደተኞቹ በዞኑ ስር ባለ 56 ሄክታር መሬት ላይ ቋሚ የመጠለያ ጣቢያ ሊገነባ መሆኑም ተገልጿል።

ከተቀሰቀሰ አንድ ወር ያለፈውን የሱዳን ግጭት በመሸሽ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ያሉት፤ በአማራ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ ክልሎች በኩል አድርገው መሆኑን የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ትላንት ረቡዕ ግንቦት 9፤ 2015 ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር። ስደተኞችን በቀዳሚነት ማስተናገድ በጀመረው የአማራ ክልል መተማ ወረዳ በኩል፤ ካለፈው ሚያዝያ ወር ጀምሮ ከ22 ሺህ በላይ ስደተኞች ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸውን የምዕራብ ጎንደር ዞን የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበባው በዛብህ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን እስካሁን ድረስ የ66 ሀገራት ዜግነት ያላቸውን ስደተኞች መቀበሉን የጠቆሙት ኃላፊው፤ ወደ መተማ የሚገቡትን ሰዎች በሁለት ምድብ ከፍሎ ሲያስተናግድ መቆየቱን አስረድተዋል። በመጀመሪያው ምድብ የተቀመጡት በሱዳን ውስጥ ይኖሩ የነበሩት ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፤ ዞኑ “ከስደት ተመላሾች” በሚል አግባብ ማስተናገዱን ገልጸዋል። ሱዳናውያን ጨምሮ የሌሎች ሀገራት ዜጎች ደግሞ “ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች” በሚለው ሁለተኛ ምድብ አቀባበል ሲደረግላቸው መቆየቱን አብራርተዋል።

በሱዳን የእርስ በእርስ ግጭት የመጀመሪያ ሳምንታት ወደ መተማ በየዕለቱ ሲገቡ የነበሩት ስደተኞች “አንድ ሺህ እና ከአንድ ሺህ በላይ” እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ አበባው፤ ባለፈው ሳምንት ይህ ቁጥር ቀንሶ ዞኑ የሚቀበላቸው ሰዎች ብዛት 500 ደርሶ እንደነበር ገልጸዋል። በዚህ ሳምንት ደግሞ ከሱዳን የሚገቡት ስደተኞች ቁጥር በድጋሚ አሻቅቦ፤ የመተማ ከተማ በየዕለቱ ከ800 በላይ ሰዎችን እያስተናገደች መሆኑን ኃላፊው አስታውቀዋል። የስደተኞች ቁጥር የመጨመር እና መቀነስ ጉዳይ፤ ከሱዳን “ለመውጣት ምቹ ሁኔታ ከመፈጠር እና አለመፈጠር ጋር” የሚያያዝ መሆኑንም አክለዋል። 

ወደ መተማ ከተማ እየገቡ ያሉት ስደተኞች የሚስተናገዱት በከተማዋ ለምዝገባ እና ለጊዜያዊ መቆያ ተብለው በተዘጋጁት “ሼዶች” ውስጥ መሆኑን የሚገልጹት አቶ አበባው፤ በመቆያ ውስጥ ከሚኖራቸው ቆይታ በኋላ በሁለት መንገድ እንደሚስተናገዱ ተናግረዋል። ከዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) ጋር “ውል የገቡ ሀገራት” ዜጎች፤ እስከ ደባርቅ፣ ጎንደር፣ ባህር ዳር እና አዲስ አበባ ከተሞች ድረስ ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት በድርጅቱ እንደሚያገኙ አስረድተዋል። ይህንን አገልግሎት ከሚያገኙት መካከል፤ የሶማሊያ፣ ኬንያ እና ማላዊ ሀገራት ዜጎች እንደሚገኙበት ጠቁመዋል። 

“በሀገራቸው ውስጥ ጥሩ ሁኔታ የሌለ” እና “ኢትዮጵያ ውስጥ ኤምባሲ የሌላቸው” ሀገራት ዜጎች ደግሞ በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ እንዲቆዩ እንደሚደረግ አመልክተዋል። በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ እንዲቆዩ ከሚደረጉት መካከል የሱዳን፣ ኤርትራ እና ሶርያ ዜጎች እንደሚገኙበት ኃላፊው ጠቁመዋል። እነዚህ ስደተኞች እየተስተናገዱ ያሉት፤ በከተማዋ ውስጥ በተዘጋጀ መጠለያ እና ከመተማ በስድስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለ ጊዜያዊ የመጠለያ ጣቢያ እንደሆነ አስረድተዋል።

“ማንደፍሮ ተራራ” በሚባል አካባቢ የሚገኘው ይህ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የተቋቋመው፤ በስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት እንደሆነ ገልጸዋል።  የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ትላንት ባወጣው መግለጫ፤ “በቀጥታ በጦርነቱ ከተፈናቀሉ” ሱዳናውያን ውጪ ያሉ የሌሎች ሀገራት ዜጎች የሚያቀርቧቸው “የቡድን እና የግለሰብ የስደተኝነት እውቅና ጥያቄን” እንደ ጉዳዩ አግባብነት እያየ “የመወሰን አካሄዶችን” ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስታውቋል። እስካሁን ድረስ ጥገኝነት የጠየቁ ሰዎች ቁጥር ከሶስት ሺህ በላይ እንደሆነ መስሪያ ቤቱ በዚሁ መግለጫው ጠቅሷል።

በምዕራብ ጎንደር ዞን እነዚህ ስደተኞች “በቋሚነት” የሚጠለሉበት ጣቢያ፤ “ኩመር አውላላ” በሚባል ቦታ ላይ ለመገንባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በአማራ ክልል መንግስት፣ በስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት እንዲሁም በዓለም አቀፉ የስደተኞች መርጃ ድርጅት (UNHCR) ትብብር ለሚገነባው የስደተኞች ጣቢያ፤ ዞኑ 56 ሄክታር መሬት መስጠቱንም አመልክተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)