ጠቅላላ ጉባኤውን እንዳያደርግ ተከልክሎ የነበረው ባልደራስ ፓርቲ፤ በመጪው እሁድ ስብሰባውን ሊያካሄድ ነው

በአማኑኤል ይልቃል

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ፤ ከሁለት ወራት በፊት በክልከላ ሳቢያ ተደናቅፎ የነበረውን የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባውን ከነገ በስቲያ እሁድ ግንቦት 13፤ 2015 ሊያካሄድ ነው። የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ በድጋሚ እንዳይስተጓጎል፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስብሰባው ከሚደረግበት ሆቴል ጋር ውል የመግባት እና ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማሳወቅ ስራ እንዳከናወነ ተገልጿል። 

ከሶስት ዓመት በፊት የተመሰረተው ባልደራስ ፓርቲ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ሊያደርግ የነበረው፤ ባለፈው መጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ ነበር። በዕለቱ የፓርቲው አባላት ጠቅላላ ጉባኤው ይካሄድበታል በተባለው ጋምቤላ ሆቴል ቢሰባሰቡም፤ ሆቴሉ ስብሰባውን ማስተናገድ እንደማይችል ማስታወቁ ይታወሳል። በአዲስ አበባ ራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ የሚገኘው ይህ ሆቴል ጠቅላላ ጉባኤውን ለማስተናገድ ፈቃደኛ ያልሆነው፤ ከኦሮሚያ ፖሊስ የመጡ አባላት ስብሰባው በዚያ እንዳይካሄድ “ትዕዛዝ እና ማስፈራሪያ አድርሰውብኛል” በማለቱ እንደሆነ የፓርቲው አመራሮች በወቅቱ ገልጸዋል።

ከዚህ በኋላ ፓርቲው በሚያዝያ 22፤ 2015 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤውን ለማድረግ በድጋሚ ቀጠሮ ይዞ እንደነበር የባልደራስ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አምሃ ዳኘው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ፓርቲው ለዚህ ስብሰባው ዝግጅት እያደረገ ባለበት ሰዓት፤ ራሳቸው ምክትል ፕሬዝዳንቱ በመታሰራቸው ምክንያት የታቀደው ጠቅላላ ጉባኤ መስተጓጎሉን አቶ አምሃ አስረድተዋል። 

“በአማራ ክልል ውስጥ ሁከት እና ብጥብጥ በመፍጠር” ተጠርጥረው የተያዙት የባልደራስ ምክትል ፕሬዝዳንት፤ ለአንድ ወር ገደማ በእስር ላይ ቆይተዋል። በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸው የነበሩት አቶ አምሃ፤ በ30 ሺህ ብር ዋስትና የተፈቱት ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይ ነው። የእርሳቸው እስራት ጠቅላላ ጉባኤውን “ለተወሰነ ጊዜ ለማራዘም ጥቅም ላይ የዋለ ዘዴ ነው” ብለው እንደሚያምኑ አቶ አምሃ ተናግረዋል። 

እርሳቸው ከእስር ከተፈቱ በኋላ የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባኤ ለማድረግ በድጋሚ ዝግጅት መጀመሩን የገለጹት የባልደራስ ምክትል ፕሬዝዳንት፤ ይህ ዝግጅት ተጠናቅቆ በመጪው እሁድ ጉባኤውን በኢትዮጵያ ሆቴል ለማካሄድ ቀጠሮ መያዙን አስታውቀዋል። የእሁዱ ጠቅላላ ጉባኤ በድጋሚ እንዳይደናቀፍ፤ ምርጫ ቦርድ ከኢትዮጵያ ሆቴል ጋር ውል በመፈጸም እገዛ ማድረጉን አስረድተዋል። ለሆቴሉ የሚፈጸመውን ክፍያ ያከናወነው ግን ፓርቲው መሆኑን አክለዋል።

ምርጫ ቦርድ ከዚህ በተጨማሪም ባልደራስ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤውን ለማከናወን ከቦርዱ ፈቃድ ያገኘ መሆኑን፤ ለአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት እንዲሁም ለከተማዋ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ የማሳወቅ ስራ ማከናወኑን አቶ አምሃ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ፕሬዝዳንቱ የጠቀሷቸውን እገዛዎች ማድረጉን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጧል።

እንደ ባልደራስ ሁሉ ጠቅላላ ጉባኤውን ባለፈው መጋቢት ወር ሊያከናውን የነበረው እናት ፓርቲ፤ በተመሳሳይ ምክንያት ስብሰባው ከተስተጓጎለ በኋላ ምርጫ ቦርድ ድርጊቱ ኮንኖ መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል። ቦርዱ በዚሁ መግለጫው፤ የፖለቲካ ፓርቲዎቹን ጠቅላላ ጉባኤን ያሰናከሉ የህግ አስፈጻሚ አካላት ላይ ፍትሕ ሚኒስቴር ክስ እንዲመሰርት ጠይቆ ነበር። የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደፊት ተመሳሳይ ችግር እንዳያጋጥማቸው፤ በመንግስት መስሪያ ቤቶች ስር የሚተዳደሩ የስብሰባ ቦታዎች እና አዳራሾች ለጠቅላላ ጉባኤዎች ክፍት እንዲሆኑ ውሳኔ ማሳለፉን በወቅቱ ማስታወቁም አይዘነጋም። 

ባልደራስ በእሁዱ ጉባኤው ከዚህ ቀደም ይዟቸው በነበሩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ አቶ አምሃ ተናግረዋል። ከእነዚህ አጀንዳዎች መካከል በቀዳሚነት የሚቀመጠው፤ “ባልደራስን ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ማድረግ” የሚለው እንደሆነ አስረድተዋል። ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ በ2012 ዓ.ም የተመሰረተው በአዲስ አበባ ከተማ የሚንቀሳቀስ ክልላዊ ፓርቲ ሆኖ ነው። ከነገ በስቲያ በሚደረገው ጠቅላላ ጉባኤ፤ ፓርቲውን ሀገር አቀፍ የማድረግ ሀሳብ በአጀንዳነት ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት እና ውሳኔ እንደሚያገኝ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል። 

ሌላኛው የጠቅላላ ጉባኤው ዋነኛ አጀንዳ፤ ባልደራስ ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚደርገውን “ትብብር” የሚመለከት መሆኑን አቶ አምሃ ጠቁመዋል። “ጥምረትም ሆነ፣ ህብረትም ሆነ፣ ውህደትም ይሁን ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ መስራትን በተመለከተ፤ በፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ በተፈቀዱት የመተባበር ስልቶች ወደፊት ሊተባበር እና አብሮ መስራት የሚችልበት ሁኔታ ይሄ ጉባኤ መወሰን አለበት” ሲሉ የአጀንዳውን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተዋል።

በእሁዱ ጠቅላላ ጉባኤ ሌላው ተጠባቂ አጀንዳ የፓርቲውን ፕሬዝዳንት መምረጥ ነው። ባልደራስን ከምስረታው ጀምሮ በፕሬዝዳንትነት ሲመሩ የቆዩት አቶ እስክንድር ነጋ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ራሳቸውን ከፖለቲካ በማግለላቸው፤ ፓርቲው ላለፉት አስር ወራት ሲመራ የቆየው በምክትል ፕሬዝዳንቱ አቶ አምሃ ዳኘው ነው። እንደ ፕሬዝዳንቱ ሁሉ ሌሎች የፓርቲው አመራር አካላት የተጓደሉበት ባልደራስ፤ ለስራ አስፈጻሚ፣ ኦዲት እና ቁጥጥር እንዲሁም የዲሲፕሊን ኮሚቴዎች አባላትን ይመርጣል ተብሏል። የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት ምርጫ እና  የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ ማጽደቅም፤ ለጠቅላላ ጉባኤው የተያዙ ሌሎች አጀንዳዎች ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)