የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በደቡብ አፍሪካ ለተፈረመው ግጭት የማቆም ስምምነት ሙሉ ትግበራ ቁርጠኛ እንዲሆኑ የቡድን ሰባት መሪዎች ጉባኤ ጥሪ አቀረበ። በኢንዱስትሪ የበለጸጉት ሰባት አገራት መሪዎች ትላንት ቅዳሜ ግንቦት 12፤ 2015 ባወጡት መግለጫ በፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ “የተገኙትን መልካም ለውጦች” በአዎንታ እንደሚቀበሉ አስታውቀዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን እና የፈረንሳዩ አቻቸው ኤማኑዌል ማክሮን ጨምሮ የቡድን ሰባት መሪዎች፤ ባለፈው ጥቅምት ወር በፕሪቶሪያ ከተማ የተፈረመውን ስምምነት በተመለከተ ጠቅለል ያለ አቋማቸውን የገለጹት በጃፓን ሂሮሺማ ባካሄዱት ጉባኤ ባወጡት መግለጫ ነው። የፕሪቶሪያው ስምምነቱ በተፈረመ በሁለተኛው ቀን በጀርመኗ ሙንስትር ከተማ ተሰብስበው የነበሩት የቡድን ሰባት አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፤ ለፕሪቶሪያው ስምምነት ድጋፋቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በወቅቱ ባወጡት መግለጫ፤ የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ እንዲያከብሩ እና ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበው ነበር። የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እና በደሎች በአፋጣኝ እንዲቆሙ በጥቅምቱ መግለጫቸው ጥሪ ያስተላለፉት የቡድን ሰባት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፤ አጥፊዎች ተጠያቂ ሆነው ተበዳዮች ፍትሕ ሊያገኙ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የበለጸጉት አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባለፈው ሳምንት በጃፓን ካደረጉት ስብሰባ በኋላ ባወጡት መግለጫም ተመሳሳይ አቋማቸውን በድጋሚ አስተጋብተዋል። “በኢትዮጵያ ጦርነት መቆሙን” በአዎንታ እንደሚመለከቱት በመግለጫቸው የጠቀሱት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ፤ ለኢትዮጵያ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ለማድረግ የተጀመረው ሂደት ወደፊት እንዲራመድም ጥሩ አቅርበዋል። ሚኒስትሮቹ የጠቀሱት የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ፤ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) የሚደገፍ ፕሮግራም ነው፡፡
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ አንድ ሳምንት በኋላ በጃፓን ሂሮሺማ ለስብሰባ የተቀመጡት የቡድን ሰባት ሀገራት መሪዎች፤ ዋነኛ ትኩረታቸውን ያደረጉት ዩክሬን፣ ሩሲያ እና ቻይናን ለተመለከቱ ጉዳዮች ነበር። መሪዎቹ ትላንት ቅዳሜ ያወጡት መግለጫ ግን ኢትዮጵያን ጨምሮ አፍሪካን በተመለከተ ያላቸውን አቋም ጭምር ያንጸባረቁበት ነው። የኢትዮጵያ መንግስት እና ሕወሓት የተፈራረሙትን የግጭት ማቆም ስምምነት ተከትሎ የመጡ “መልካም ለውጦችን” በአዎንታ እንደሚቀበሉ በመግለጫቸው ያስታወቁት መሪዎቹ፤ ሁለቱ ወገኖች ስምምነቱን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኝነታችውን እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የቡድን ሰባት አባል ሀገራት መሪዎች፤ በኢትዮጵያ ጎረቤት ሱዳን ስድስተኛ ሳምንቱን ያስቆጠረውን ጦርነት እንዲሁም የአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት ጉዳይን በመግለጫቸው ትኩረት ሰጥተው አንስተዋል። የሀገራቱ መሪዎቹ በዚሁ መግለጫቸው፤ ውጊያ የገጠሙት የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይል “ግጭት በማቆም በአፋጣኝ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ በሲቪል ፖለቲከኞች ወደሚመራ ዲሞክራሲያዊ መንግስት” እንዲመለሱ አሳስበዋል። የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ “ቅድሚያ ለሚሰጧቸው ማሻሻያዎች” እና በአልሸባብ ላይ ለጀመሩት ዘመቻ ዓለም አቀፍ ድጋፍ እንዲደረግም ጥሪ አቅርበዋል።

ቡድን ሰባት በኢንዱስትሪ የበለጸጉ እና የዳበረ ዲሞክራሲ አላቸው የሚባሉትን አሜሪካ፣ ብሪታኒያ፣ ጀርመን፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን እና ፓጃንን ያቀፈ ኢ-መደበኛ ቡድን ነው። ቡድኑ በየጊዜው በሚያካሄዳቸው ስብሰባዎች የአውሮፓ ህብረት ተወካዮችም ይሳተፋሉ። የጃፓኗ ሂሮሺማ የመሪዎቹን የዘንድሮ ጉባኤ ከግንቦት 11 እስከ 13፤ 2015 አስተናግዳለች። የዚህ ተጠባቂ ስብሰባ አስተናጋጅነት፤ በየዓመቱ በአባል አገራት ዘንድ የሚዘዋወር ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)