በአማኑኤል ይልቃል
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ወደ ሀገር አቀፍ ፓርቲነት ለማደግ ዛሬ እሁድ ግንቦት 13፤ 2015 ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ወሰነ። በዛሬው የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ፤ ባልደራስን በምክትል ፕሬዝዳንትነት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ አምሃ ዳኘው በፕሬዝዳንትነት ተመርጠዋል።
ባልደራስ ከምስረታ ጉባኤው በኋላ ባካሄደው የዛሬው የመጀመሪያ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ፤ የፓርቲውን የወደፊት አቅጣጫ በሚወስኑ ዋነኛ ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎች ተላልፈዋል። ለፓርቲው አዲስ ፕሬዝዳንት መሾም፤ በጠቅላላ ጉባኤው ቅድሚያ ውሳኔ የተሰጠበት ጉዳይ ነው። ባልደራስ አዲስ ፕሬዝዳንት ለመምረጥ የወሰነው፤ ፓርቲውን ከምስረታው ጀምሮ በፕሬዝዳንትነት የመሩት አቶ እስክንድር ነጋ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ራሳቸውን ከኃላፊነት በማግለላቸው ምክንያት ነው።
አቶ እስክንድርን ለመተካት በዛሬው ጠቅላላ ጉባኤ ከቀረቡ ሶስት ዕጩዎች መካከል፤ የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አምሃ ዳኘው ይገኙበታል። ለፕሬዝዳትነት ለመወዳደር የቀረቡት ሌሎች ዕጩዎች፤ የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት ጸሀፊ ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ እና የፓርቲው የህግ ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ ሳምሶን ገረመው ናቸው።
ድምጽ ከሰጡ 208 ጉባኤተኞች መካከል አቶ አምሃ 170 ድምጽ በማግኘት ቀዳሚ ሲሆኑ፤ አቶ በቃሉ 25 ድምጽ በማግኘት ተከታይ ሆነዋል። የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ሳምሶን ደግሞ የሰባት ሰዎችን የድጋፍ ድምጽ አግኝተዋል። ስድስት ጉባኤተኞች በትክክል ድምጽ ባለመስጠታቸው ድምጻቸው ሳይቆጠር ቀርቷል። በጉባኤተኞች ከፍተኛ ድምጽ ባልደራስን በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ የተመረጡት አቶ አምሃ፤ ከ1960ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ የፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸው ናቸው።
አቶ አምሃ በአሜሪካው ዩኒቨርስቲ ኦፍ ማሳቹሴት በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርታቸውን ይከታተሉ በነበረበት ወቅት፤ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ህብረት ሊቀመንበር ሆነው አገልግለዋል። ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ ደግሞ በ1977 በተመሰረተው የኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲ (ኢሰፓ) አባል ሆነዋል። አቶ አምሃ በኢሰፓ የአባልነት ጊዜያቸው፤ የፓርቲው የኢኮኖሚ መምሪያ ምክትል ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል።
ኢህአዴግ ወደ መንበረ ስልጣኑ ከመጣ በኋላ በግል ስራ ላይ ተሰማርተው የቆዩት አዲሱ የባልደራስ ፕሬዝዳንት፤ በድጋሚ ወደ ፖለቲካው የተመለሱት በ1997 ምርጫ ወቅት ነው። አቶ አምሃ በዚህ ምርጫ ጉልህ ድርሻ በነበረው “ቅንጅት” በተሰኘው የአራት ፓርቲዎች ጥምረት ውስጥ ተሳትፎ ነበራቸው። ከቅንጅት መከፋፈል በኋላ በ1999 ዓ.ም በተመሰረተው አንድነት ለዲሞክራሲ እና ፍትህ ፓርቲ የስራ አስፈጻሚ አባልም ነበሩ። በወቅቱ የፓርቲውን የጥናት እና ምርምር ዘርፍ በኃላፊነት መርተዋል።
ከአንድነት ፓርቲ መፍረስ በኋላ የአቶ አምሃ ቀጣይ መዳረሻ የሆነው፤ በግንቦት 2011 ዓ.ም የተመሰረተው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ነው። ኢዜማን ከምስረታው ጀምሮ የተቀላቀሉት አቶ አምሃ፤ ለአስር ወራት ገደማ የፓርቲው የስራ አስፈጻሚ አባል እንዲሁም የጥናት እና ምርምር ዘርፍ ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል። አቶ አምሃ በኢዜማ ፓርቲ ከነበራቸው ኃላፊነት እና ከአባልነታቸው በገዛ ፍቃዳቸው ከለቀቁ በኋላ የባልደራስ ፓርቲን በሰኔ 2012 ዓ.ም ተቀላቅለዋል።
ከ50 ዓመታት በላይ የዘለቀ የፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸው አቶ አምሃ፤ የባልደራስ ፓርቲን እንደተቀላቀሉ “በቀጥታ የስራ አስፈጻሚ አባል” እንዲሆኑ መደረጋቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በወቅቱ የፓርቲውን የፖለቲካ ዘርፍ በኃላፊነት እንዲመሩ መደረጋቸውንም አስታውሰዋል። አቶ አምሃ በዚሁ የኃላፊነት ቦታ ለአንድ ዓመት ከቆዩ በኋላ፤ በሰኔ 2013 ዓ.ም የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ተሹመዋል። የፓርቲው ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ እስክንድር ራሳቸውን ከኃላፊነት ካገለሉበት ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ እስከ ዛሬው ስብሰባ ድረስም ፓርቲውን በጊዜያዊነት ሲመሩ ቆይተዋል።
የባልደራስ ጠቅላላ ጉባኤ በዛሬው ስብሰባው ውሳኔ ያሳለፈበት ሌላኛው ጉዳይ፤ ፓርቲውን አገር አቀፍ ማድረግን የሚመለከት ነው። ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ በየካቲት 2012 የተቋቋመው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚንቀሳቀስ ክልላዊ ፓርቲ ሆኖ ነው። ላለፉት ሶስት ዓመት ገደማ በዚሁ ማዕቀፍ ሲንቀሳቀስ የነበረውን ባልደራስ፤ ወደ ሀገር አቀፍ ፓርቲነት ለማሳደግ ያለመ የውሳኔ ሀሳብ በዛሬው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ቀርቦ ነበር። በዚህ የውሳኔ ሀሳብ ላይ ድምጽ የሰጡት 219 የጠቅላላ ጉባኤው አባላት፤ የፓርቲውን ወደ ሀገር አቀፍ ደረጃ መሸጋገር በሙሉ ድምጽ ደግፈዋል።
ከትላንት በስቲያ አርብ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጋር ቆይታ አድርገው የነበሩት አቶ አምሃ፤ ይህ የውሳኔ ሃሳብ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ፓርቲውን በሀገር አቀፍነት የማደራጀት ስራ እንደሚጀመር ተናግረው ነበር። ከሶስት ዓመት በፊት የወጣው የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ፤ ሀገር አቀፍ ፓርቲ ለመመስረት አስር ሺህ መስራች አባላት እንደሚያስፈልጉ ደንግጓል። እነዚህ መስራች አባላት ቢያንስ ከአራት ክልሎች መሰባሰብ እንዳለባቸውም አዋጁ አስቀምጧል። ከመስራቾቹ ውስጥ 40 በመቶው የአንድ ክልል መደበኛ ነዋሪዎች መሆን እንዳለባቸውም በአዋጁ ላይ ሰፍሯል።
ባልደራስ ይህንን የመስራቾች ፊርማ የማሰባሰብ ስራ፤ በሀገሪቱ ያለው “የጸጥታ ሁኔታ በፈቀደ መጠን” በክልሎች ተዘዋውሮ ለመሰብሰብ ከውሳኔ ላይ መድረሱን አቶ አምሃ ተናግረዋል። ባልደራስ በየትኞቹ ክልሎች ላይ መሰረት ይዞ ለመንቀሳቀስ እንዳሰበ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው አዲሱ ፕሬዝዳንት፤ ፓርቲው በደቡብ የሀገሪቱ ክፍል ውስጥ በሚገኙ አካባቢዎች “በስፋት” እንደሚገባ እና በአማራ ክልል “በእርግጠኝነት” እንደሚንቀሳቀስ አስታውቀዋል።
በኦሮሚያ ክልል ባልደራስ ትኩረት የሚያደርገው በከተሞች ላይ መሆኑን የገለጹት አቶ አምሃ፤ ለእዚህ የፓርቲው እንቅስቃሴ አዳማ እና ቢሾፍቱ ከተሞች ተጠቃሽ መሆናቸውን አስረድተዋል። በሀረሪ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርም ፓርቲው የመንቀሳቀስ እቅድ እንዳለው ፕሬዝዳንቱ አመልክተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)