ለሽያጭ የቀረቡ የመንግስት የስኳር ፋብሪካዎችን ወደ ግል ማዛወር የሚፈልጉ ኩባንያዎች ምክረ ሃሳባቸውን እንዲያቀርቡ ተጠየቁ

የኢትዮጵያ መንግስት በስሩ ያሉ ስምንት የስኳር ፋብሪካዎችን ወደ ግል ማዛወር ለሚሹ ገዢዎች ምክረ ሃሳባቸውን (proposal) እንዲያቀርቡ ጋበዘ። ለሽያጭ ከቀረቡት መካከል የአርጆ ዴዴሳ፣ ከሰም፣ ጣና በለስ እና ተንዳሆ የስኳር ፋብሪካዎች ይገኙበታል።

በመንግስት እጅ ከሚገኙት ከእነዚህ ስምንት ፋብሪካዎች ውስጥ አራቱ በኦሞ ኩራዝ የስኳር ፕሮጀክት ስር የሚገኙ ናቸው። እነዚህን የስኳር ፋብሪካዎች መግዛት የሚሹ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ምክረ ሃሳቦቻቸውን ከዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 15፤ 2015 ጀምሮ እንዲያስገቡ ግብዣ ቀርቦላቸዋል። 

የገንዘብ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የተሰኘው መንግስታዊ ተቋም በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ ዛሬ ይፋ የሆነው ሂደት “መንግስት ወደ ተወዳዳሪ የገበያ መዋቅር ለመሸጋገር እና በስኳር ዘርፍ ያለውን የግሉን ዘርፍ ዕድገት ለማጠናከር የሚያደርገው ጥረት ወሳኝ ምዕራፍ” እንደሆነ አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ስምንቱን የስኳር ፋብሪካዎች መግዛት ለሚሹ ኩባንያዎች ፍላጎታቸውን እንዲያሳውቁ ጥሪ ያቀረበው በነሐሴ 2014 ነበር።

በጥሪው መሠረት ከ20 በላይ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ወገኖች በጨረታው ለመሳተፍ ፍላጎታቸውን እንዳሳወቁ፤ የገንዘብ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልንዲንግስ በጋራ ባወጡት መግለጫ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መንግስት የስኳር ፋብሪካዎቹን የመግዛት ፍላጎታቸውን ካሳወቁ ኩባንያዎች ጋር በዘርፉ “ሊደረግ በታቀደ የፖሊሲ ማሻሻያ ላይ ግብረ መልስ ለመቀበል” ግንኙነት ሲያደርግ መቆየቱንም መግለጫው ጠቅሷል። 

በዚህም መሰረት የጨረታውን ሂደት የሚገልጽ አጠቃላይ የምክረ ሐሳብ መጠየቂያ (RFP) ይፋ መደረጉም ተመላክቷል። የምክረ ሐሳብ መጠየቂያው፤ የስኳር ፋብሪካዎቹን ወደ ግል የማዘዋወር ሂደት ወሰን፣ ተጫራቾች ማሟላት የሚጠበቁባቸውን እና የግምገማውን መስፈርት እንዲሁም የጊዜ ሂደቱን ጨምሮ ስለ ሽያጩ ዝርዝር መረጃ የሚያቀርብ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)