በ37 የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች በተካሄደ የኦዲት ምርመራ፤ “ምንም ጉድለት” ያልተገኘባቸው ሁለቱ ብቻ መሆናቸው ተገለጸ

በአማኑኤል ይልቃል

የ2013 ሂሳባቸው ኦዲት ከተደረጉ 37 የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ “ምንም ጉድለት ያልተገኘባቸው” ሁለቱ ብቻ እንደሆኑ የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ። ሚኒስቴሩ ኦዲት ከተደረጉት ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ 48.6 በመቶው “ተቀባይነት የሚያሳጣ” ደረጃ ላይ እንደሆኑ ተረጋግጧል ብሏል።

የትምህርት ሚኒስቴር ይህንን ያስታወቀው ትላንት ማክሰኞ ግንቦት 15፤ 2015 በተካሄደው የተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ነው። በዚህ ስብሰባ ላይ በቀረበው የሚኒስቴሩ የዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ከተነሱ ጉዳዮች ውስጥ፤ የመንግስት ዩኒቨርስቲዎችን የተመለከተው ይገኝበታል። ዩኒቨርስቲዎቹ ዘንድሮ ያስተናገዷቸውን ተማሪዎች ብዛት፣ በፓርላማ ለመጽደቅ በሂደት ላይ ያለው የዩኒቨርስቲዎች ራስ ገዝ አስተዳደር አዋጅ እና በዚህ ዓመት የሚጀመረው የተማሪዎች መውጫ ፈተና በሪፖርቱ የተጠቀሱ ጉዳዮች ናቸው። 

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ያላቸው የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓትም በዚሁ ሪፖርት ተካትቷል። ሪፖርቱን ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት በንባብ ያቀረቡት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ ተቋማቱ በዚህ ረገድ ያሉበት ደረጃ የፌደራል ዋና ኦዲተር ካደረገው የ2013 ዓ.ም የሂሳብ ኦዲት በኋላ ለመለየት መቻሉን አስታውቀዋል። እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ ኦዲት ከተከናወነባቸው 37 የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ 18 ያህሉ “ተቀባይነት የሚያሳጣ” የኦዲት ጉድለት ተገኝቶባቸዋል። 

የኦዲት ምርመራ ከተደረገባቸው መካከል “ጥቂት ጉድለት” የተገኘባቸው 17 ዩኒቨርስቲዎች መሆናቸውን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ተናግረዋል። ከ37ቱ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ “ምንም ጉድለት” እንደሌለባቸው የተረጋገጡት ሁለት ዩኒቨርስቲዎች ብቻ መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስትሩ ለፓርላማ አባላት ጨምረው ገልጸዋል። ይህ የፌደራል ዋና ኦዲተር የኦዲት ግኝት የደረሰው ትምህርት ሚኒስቴር፤ በጉዳዩ ላይ “የእርምት እርምጃ ለመውሰድ እና ማስተካከያ ለማድረግ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመወያየት አቅጣጫ” ማስቀመጡንም ፕሮፌሰር ብርሃኑ በትላንቱ ስብሰባ ላይ አስረድተዋል። “በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ማስተካከያ ስለመደረጉ ተገቢው ክትትል እና ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል” ሲሉም አክለዋል።

በትምህርት ሚኒስቴር ሪፖርት ላይ የተነሳው ይህ የዩኒቨርስቲዎች የኦዲት ግኝት ጉዳይ፤ መስሪያ ቤቱን ከሚከታተለው የተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት፣ ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጥያቄ ተነስቶበታል። በዩኒቨርስቲዎች የሚከናወኑ ግንባታ እና ፕሮጀክቶች ላይ “መጓተት እና የሀብት ብክነት በስፋት” እንደሚታይ ያነሱት የቋሚ ኮሚቴው አባል የሆኑት አቶ ፍሬው ተስፋዬ፤ “እነዚህን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተቀመጠው አቅጣጫ ምን እንደሆነ” እንዲብራራ ጠይቀዋል።

ለፓርላማው አባል ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የትምህርት ሚኒስትር ዲኤታው ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ናቸው። የፌደራል ዋና ኦዲተር ለፓርላማው በሚያቀርባቸው የኦዲት ሪፖርቶች ውስጥ በብዛት ጉድለት የሚታየው በመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ መሆኑን ያስታወሱት ሚኒስትር ዲኤታው፤ ምክንያቱን ለመለየት “ተከታታይ ክትትል” መደረጉን ገልጸዋል። በዚህ ክትትል መሰረት ጉድለቱ የሚፈጠረው፤ በተቋማቱ “ተልዕኮ ስፋት” እና በዩኒቨርስቲዎቹ አመራሮች መካከል “የዝግጅት ልዩነት” በመኖሩ ምክንያት እንደሆነ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መረዳቱን ተናግረዋል።

የእዚህ ችግር መፍትሔ በየደረጃው ያሉ የዩኒቨርስቲ አመራሮች “በብቃታቸው ተወዳድረው” እንዲመጡ ማድረግ እና “በፍትሃዊነት መደልደል” መሆኑን አንስተዋል። “የአመራሮች አቅም ግንባታ ስራ” መስራትን በተጨማሪ በመፍትሔነት የጠቀሱት ዶ/ር ሳሙኤል፤ “ከሁሉ በላይ ግን ዩኒቨርስቲዎችን የሚመስሉ የህግ ማዕቀፎች እንዲኖሩ” ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አብራርተዋል። ዩኒቨርስቲዎች ራስ ገዝ በሚሆኑበት ወቅት ይህ የተቋማቱን “ልዩ ባህሪ” ያገናዘበ አሰራር እንደሚተገበርም አመልክተዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ በበኩላቸው በኦዲቱ ግኝት የተደረሰባቸው ጉድለቶች አንዱ ምክንያት፤ ዩኒቨርስቲዎቹ የሚመደብላቸው በጀት እና ያለባቸው ወጪ አለመመጣጠን መሆኑን አንስተዋል። ዩኒቨርስቲዎች ለአንድ ተማሪ የሚመደብላቸውን 22 ብር ዕለታዊ የምግብ ወጪ በማሳያነት የጠቀሱት የትምህርት ሚኒስትሩ፤ ይህ ገንዘብ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ በአሁኑ ወቅት ተማሪዎቻቸውን ለመመገብ በቀን ከሚያወጡት ወጪ ጋር ልዩነት ያለው መሆኑን አስረድተዋል። 

ፕሮፌሰር ብርሃኑ ዩኒቨርስቲዎቹ “ከየት ያመጡና ይሞሉታል ተብሎ ነው የሚጠበቀው?” የሚል ጥያቄ ወደ ምክር ቤቱ ከሰነዘሩ በኋላ፤ “አንዳንድ ጊዜ ከኦዲት ግኝት ጋር የተያያዘው ጥያቄ የዚያ ውጤት ነው ዩኒቨርሰቲዎች ውስጥ የሚታየው። ተማሪ ተቀብለው ሊያስርቡ አይችሉም። መንገድ መፈለግ አለባቸው” ሲሉ ተቋማቱ እያጋጠማቸው ያለውን ተግዳሮት አስረድተዋል። ዩኒቨርስቲዎቹ ይህን መሰል የሚያጋጥማቸውን ችግር ለማለፍ ከሚጠቀሙባቸው መንገዶች መካከል፤ ያሏቸውን ተማሪዎች ቁጥር “ከፍ አድርጎ” ማቅረብ አንዱ እንደሆነ ተናግረዋል። የተወካዮች ምክር ቤት የተቋማት በጀት ቀርቦለት በሚመለከትበት ጊዜ ይህንን ከግንዛቤ እንዲያስገባም ጠይቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)