የብልጽግና ፓርቲ የስራ አስፈጻሚ እና ማዕከላዊ ኮሚቴዎች፤ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ መደበኛ ስብሰባዎቻቸውን ሊያካሄዱ ነው 

በአማኑኤል ይልቃል

የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ እና ማዕከላዊ ኮሚቴዎች፤ ከመጪው ሰኞ ግንቦት 21 ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ገደማ የሚቆዩ ስብሰባዎችን ሊያካሄዱ ነው። በሁለቱ ኮሚቴዎች መደበኛ ስብሰባዎች፤ ወቅታዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ይነሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተነግሯል። 

ከመጪው ሰኞ እስከሚቀጥለው ሳምንት ማክሰኞ ዕለት የሚቆዩት የብልጽግና ፓርቲ የስራ አስፈጻሚ እና ማዕከላዊ ኮሚቴዎች መደበኛ ስብሰባዎች፤ የፓርቲው የስራ አፈጻጸም “በዋነኛነት የሚገመገምባቸው” እንደሆኑ የብልጽግና ፓርቲ የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አዳራሽ የሚደረጉት ስብሰባዎች በቅደም ተከተል የሚደረጉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል። 

በቅድሚያ የሚደረገው የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ሲሆን፤ ሰኞ ግንቦት 21፤ 2015 ተጀምሮ በማግስቱ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። አርባ አምስት አባላት ያሉት የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፤ ለመጨረሻ ጊዜ ስብሰባውን ያደረገው ከሁለት ወራት በፊት መጋቢት ላይ ነበር። የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ይህን ስብሰባውን ሲያጠናቅቅ ባወጣው መግለጫ፤ በሀገሪቱ እየታዩ ላሉ ተግዳሮቶች “ምክንያት ናቸው” በሚል ከስምምነት ላይ የደረሰባቸውን አምስት ዋነኛ ጉዳዮችን ማስታወቁ ይታወሳል።

ከእነዚህ ምክንያቶች ውስጥ በፓርቲው በቀዳሚነት የተጠቀሱት “መግባባት ያልተፈጠረባቸው እና ያልተፈቱ የታሪክ ዕዳዎች”፣ “ነጻነትን ለማስተዳደር አለመቻል” እንዲሁም “ህብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚፈታተኑ ሁኔታዎች እየገነገኑ መምጣታቸው” ነበሩ። ብልጽግና ፓርቲ በዚሁ መግለጫው በፈተናነት ከጠቀሳቸው ውስጥ “የኑሮ ውድነት” እና “ሌብነት” ይገኙበታል። 

የገዢው ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በመጪዎቹ ሰኞ እና ማክሰኞ የሚያደርገውን ስብሰባ ካጠናቀቀ አንድ ቀን በኋላ የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ እንደሚቀጥል አቶ አዲሱ ተናግረዋል። ሐሙስ ዕለት ለሚጀምረው ስብሰባ አንድ ቀን አስቀድመው በአዲስ አበባ እንዲገኙ ጥሪ የቀረበላቸው የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፤ እስከ ሚቀጥለው ሳምንት ማክሰኞ ግንቦት 29 ድረስ በስብሰባ ላይ ይቆያሉ። 

ብዛታቸው 225 የሆኑት የብልጽግና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ከዚህ ቀደም ስብስባ ያካሄዱት፤ ከስድስት ወራት በፊት ባለፈው ህዳር ነበር። የፌደራል መንግስት እና ህወሓት ተደራዳሪዎች በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ የሰላም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ በተካሄደው በዚሁ ስብሰባ ላይ “ወቅታዊ አገራዊ አጀንዳዎች” ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷቸው ነበር ተብሏል። ይህ ስብሰባ ካበቃ ከቀናት በኋላ፤ ገዢው ፓርቲ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ መጥራቱም ያታወሳል። 

በሀዋሳ ከተማ የተካሄደው የብልጽግና ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ የተጠራው፤ የፓርቲውን ኢንስፔክሽንና ሥነ-ምግባር ኮሚሽን አባላትን በድጋሚ ለመምረጥ ነበር። አስራ አንድ አባላት ያሉበት የፓርቲው ኮሚሽን አባላት በድጋሚ እንዲመረጡ ውሳኔ ያስተላለፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነበር። ብልጽግና ፓርቲ በመጋቢት 2014 ዓ.ም. ባካሄደው አንደኛ ጠቅላላ ጉባኤ የመረጣቸው የኢንስፔክሽንና ሥነ-ምግባር ኮሚሽን አባላት፤ “ግልጽ፣ ነጻ እና ፍትሃዊ በሆነ፤ በሚስጥር በሚሰጥ ድምጽ ያልተመረጡ ናቸው” በሚል ነበር ቦርዱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው።

ገዢው ፓርቲ በዚሁ ጠቅላላ ጉባኤው ያስቀመጣቸው “አቅጣጫዎች”፤ ከመጪው ሳምንት መጀመሪያ ጀምሮ በሚካሄዱት የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ እና ማዕከላዊ ኮሚቴዎች ስብሰባዎች ላይ እንደሚገመገሙ አቶ አዲሱ አመልክተዋል። በእነዚሁ ስብሰባዎች “አጠቃላይ የዓመቱ የእቅድ አፈጻጸም” ግምገማ እንደሚካሄድ ገልጸዋል። በፓርቲው የስራ አፈጻጸም ግምገማ ወቅት ሀገራዊ ጉዳዮችም ተካተው እንደሚታዩ የፓርቲው የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። 

“በአመቱ እቅድ የያዝነው የፓርቲ ስራ አፈጻጸሙ ምን ይመስላል ተብሎ ሲገመገም፤ እዚያ ውስጥ ሰላም እና ጸጥታ ላይ ምን መሻሻል አለ? ምንድነው የሚቀረን? የሚለው ይታያል” ሲሉ አቶ አዲሱ ገልጸዋል። በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ከሚታዩት ውስጥ “የማክሮ ኢኮኖሚ ጉዳዮች፣ የኑሮ ውድነት፣ ስራ አጥነት፣ ከመልካም አስተዳደር ጋር ተይያዞ የሚነሱ ችግሮች እንዲሁም የተለያዩ ዘርፎች አፈጻጸሞች” እንደሚገኙበትም አክለዋል። በስብሰባዎቹ ላይ “ለውይይት ይቀርባሉ” ተብለው የሚጠበቁ ሌሎች አጀንዳዎች ይኖሩ እንደሆነ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የብልጽግና ፓርቲ የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ፤ “ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ሊነሱ ይችላሉ። ግን የተለየ አጀንዳ የለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)