በአማኑኤል ይልቃል
በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን በሚገኘው ፊንጫኣ ስኳር ፋብሪካ ላይ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት፤ 11 የፋብሪካው ሰራተኞች እና ሶስት የአካባቢው ነዋሪዎች እንደተገደሉ ማረጋገጡን የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታወቀ። ፋብሪካው በተፈጸመበት በዚሁ ጥቃት እና ዘረፋ ምክንያት ስራ ማቋሙም ተገልጿል።
ከአዲስ አበባ በ350 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የፊንጫኣ ስኳር ፋብሪካ ላይ ጥቃቱ የተፈጸመው ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ግንቦት 12፤ 2015 መሆኑን የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ የህዝብ ግንኙነት እና ተሳትፎ ክፍል ኃላፊ አቶ ረታ ደመቀ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ፋብሪካው ባለፈው 2014 ዓ.ም እና በዚህ ዓመት ተመሳሳይ ጥቃቶችን ቢያስተናግድም፤ የአሁኑ ከዚህ ቀደም ከነበሩት “ከበድ ያለ” እንደሆነ ተነግሯል።
የፊንጫኣ ስኳር ፋብሪካ እና በስሩ ያለው የሸንኮራ አገዳ እርሻ፤ በአጠቃላይ በ67 ሺህ ሄክታር ይዞታ ላይ ያረፈ ነው። የቀደሙት ጥቃቶች ይበልጥኑ ኢላማ የሚያደርጉት የፋብሪካው እርሻ ላይ እንደነበር የሚናገሩት አቶ ረታ፤ ታጣቂዎቹ “የአገዳ እና የእርሻ ማሽነሪዎችን የማቃጠል” ድርጊት ይፈጽሙ እንደነበር ያስታውሳሉ። የአሁኑ ከዚህ ቀደም ከነበሩት የሚለየው፤ ታጣቂዎቹ ወደ ፋብሪካ ጭምር በመግባት ጥቃቶቹን በመፈጸማቸው እንደሆነ ያስረዳሉ።
የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ጥቃቱን እንዲመረምር ያቋቋመው ግብረ ኃይል፤ በጥቃቱ 11 የፋብሪካው ሰራተኞች እና ሶስት የአካባቢው ነዋሪዎች እንደተገደሉ ማረጋገጡን ኃላፊው አስታውቀዋል። ሰኞ ዕለት ወደ አካባቢው የተሰማራው ይኸው ግብረ ኃይል፤ “እንደ ልብ ተዘዋውሮ ለመስራት የሚያስችል ሁኔታ ባለመኖሩ” የደረሱ ሌሎች ጉዳቶችን እስካሁን ሙሉ ለሙሉ ለማረጋገጥ አለመቻሉንም ጠቅሰዋል። ሆኖም ግብረ ኃይሉ እስካሁን ባሰባሰበው መረጃ፤ በታጣቂዎች ከተገደሉት ሶስት የአካባቢው ነዋሪዎች በተጨማሪ ጉዳት የደረሰባቸው ሌሎች እንዳሉ መረዳቱንም አቶ ረታ ተናግረዋል።
ግብረ ኃይሉ በስኳር ፋብሪካው ባደረገው ቅኝት “ውድመት እና ዘረፋ” እንደተፈጸመበት ማረጋገጡን የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ የህዝብ ግንኙነት እና ተሳትፎ ክፍል ኃላፊ ገልጸዋል። “ቢሮዎች ወድመዋል። ፋብሪካው ውስጥ ያለ መቆጣጠሪያ ኮምፒውተር [ተሰብሯል]። ከዚያ ውጪ የእርሻ ማሽነሪዎች፣ ትራክተሮች፣ አገዳ ወደ ፋብሪካው የሚያመላልሱ የተለያዩ [ተሽከርካሪዎች] ሙሉ ለሙሉ የወደሙ አሉ፤ የተጎዱም አሉ” ሲሉ አቶ ረታ በፋብሪካው ላይ የደረሰውን ጉዳት አብራርተዋል።
በቅዳሜው ጥቃት የፋብሪካው “የፋይናንስ ሰነዶች” ጭምር መውደማቸውን የሚናገሩት ኃላፊው፤ አጠቃላይ ጉዳቱን በዝርዝር ለማወቅ የሚያስችለው ምርመራ ገና አለመጠናቀቁን ገልጸዋል። በፊንጫኣ ስኳር ፋብሪካ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ከተዘረፉት ንብረቶች ውስጥ የተለያዩ ተሽከርካሪዎች፣ ኮምፒውተሮች እና ፕሪንተሮች ይገኙበታል ተብሏል። ታጣቂዎቹ በፋብሪካው መጋዘን ውስጥ የተከማቹ ስኳር እና የአፈር ማዳበሪያ ዘርፈው መውሰዳቸውን ግብረ ኃይሉ ሪፖርት ማድረጉንም አቶ ረታ አክለዋል።
ጥቃቱን የፈጸሙት ታጣቂዎች ማንነት በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ረታ፤ በእርሳቸውን የስራ ኃላፊነት የታጣቂዎችን ማንነት ለይተው መናገር እንደማይችሉ ምላሽ ሰጥተዋል። ከቅዳሜው ጥቃት በኋላ ፋብሪካው ወደሚገኝበት አካባቢ የመከላከያ ሰራዊት አባላት እንዲገቡ በመደረጋቸው በአሁኑ ወቅት በስፍራው “የተሻለ ሁኔታ” መኖሩን ኃላፊው አስረድተዋል። ሆኖም አሁንም ቢሆን “በእርሻ መንደሮች አካባቢ ታጣቂዎች አሉ” የሚል ስጋት በሰራተኞች ዘንድ እንዳለ አልሸሸጉም።
በዓመት 270 ሺህ ቶን ስኳር የማምረት አቅም ያለው የፊንጫኣ ስኳር ፋብሪካ፤ ከአምስት ቀናት በፊት በተፈጸመበት ጥቃት ምክንያት እስካሁንም ወደ ስራ እንዳልተመለሰ አቶ ረታ አስታውቀዋል። ፋብሪካው በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ መመለስ እንደሚችል መወሰን የሚቻለው፤ የደረሰውን ውድመት ለማወቅ እየተከናወነ ያለው ምርመራ ሲጠናቀቅ መሆኑንም ተናግረዋል። የስኳር ፋብሪካዎች በየዓመቱ በክረምት ወራት የጥገና ስራ ለማከናወን ስራቸው እንደሚያቆሙ የጠቆሙት አቶ ረታ፤ የክረምት ወራት እየተቃረበ ከመሆኑ አንጻር ፋብሪካው በዚሁ ወደ ጥገና ሊገባ የሚችልበት እድል እንዳለም አመልክተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)