በአማኑኤል ይልቃል
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ያሉ መስሪያ ቤቶች፤ የተወሰኑ ስራዎቻቸውን በውክልና ለግል ተቋማት አስተላልፈው (outsource) ሊያሰሩ ነው። በዚህ አሰራር ምክንያት ከስራቸው የሚነሱ የከተማ አስተዳደሩ ሰራተኞችን ወደ ሌሎች መስሪያ ቤቶች ለማዘዋወር እና “በሚፈልጉበት የስራ መስክ” እንዲሰማሩ ለመደገፍ መታሰቡም ተገልጿል።
አዲሱን አሰራር ተግባራዊ የማድረግ ሂደትን እየመራ ያለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ነው። በከተማ አስተዳደሩ ስር ያሉ መስሪያ ቤቶችን የአገልግሎት አሰጣጥ የመከታተል ኃላፊነት ያለበት ይህ ቢሮ፤ አዳዲስ አሰራሮችን የመዘርጋት ስልጣንም በአዋጅ ተሰጥቶታል። ቢሮው የተወሰኑ የመንግስት ስራዎችን ወደ ግል ተቋማት የማስተላለፍ እቅዱን በተመለከተ፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ካሉ መስሪያ ቤቶች ጋር ዛሬ ሰኞ ግንቦት 21፤ 2015 ዓ.ም ውይይት አድርጓል።
ይህንን አሰራር በቅድሚያ እንዲጀምሩ በጥናቱ የተለዩ የከተማ አስተዳደሩ አምስት መስሪያ ቤቶች እና ስድስት ሆስፒታሎች መሆናቸው በዛሬው ውይይት ላይ ተጠቅሷል። በቅድሚያ ወደ ተግባር ይገባሉ የተባሉት የንግድ፣ ትራንስፖርት፣ ገቢዎች እንዲሁም የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮዎች እና የአሽከርካሪ፣ ተሽከርካሪ ፈቃድ እና ቁጥጥር ባለስልጣን ናቸው። በአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ ውስጥ ያሉት የካቲት 12፣ ጥሩነሽ ቤጂንግ፣ ዳግማዊ ሚኒሊክ፣ ዘውዲቱ፣ ጋንዲ መታሰቢያ እና ራስ ደስታ ዳምጠው መታሰቢያ ሆስፒታሎች የተወሰኑ አገልግሎታቸውን ለግል አካላት ከሚያስተላልፉት ውስጥ ተመድበዋል።
እነዚህ የከተማ አስተዳደሩ ተቋማት ለግል አካላት የሚያስተላልፏቸውን የአገልግሎት አይነቶች፤ በ15 ቀናት ውስጥ ለይተው ለፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ እንዲያቀርቡ በዛሬው ውይይት ላይ ተነግሯቸዋል። ተቋማቱ የአገልግሎት አይነቶቹ የሚፈልጉትን ዝርዝር መስፈርት እና ይህንን ሊሰሩ የሚችሉ አካላትን ለይተው እንዲያቀርቡም ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።
የመንግስት አገልግሎቶችን ለግል አካላት ለማስተላለፍ የተወሰነው፤ የከተማዋ መስሪያ ቤቶች የሚሰጡት አገልግሎቶች ላይ “ነዋሪዎች ያላቸው የእርካታ መጠን ዝቅተኛ በመሆኑ ምክንያት ነው” ሲሉ የከተማይቱ የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሂክማ ከይረዲን ተናግረዋል። “በምን አይነት መንገድ ብንሰራ የተሻለ እና ውጤታማ አገልግሎት መስጠት እንችላለን? የሚለው አንዱ መነሻ ምክንያታችን ነው” ነው ያሉት ወ/ሮ ሂክማ፤ ይህ አሰራር በህግም የሚደገፍ መሆኑን በዛሬው ውይይት ላይ ገልጸዋል።
በ2014 ዓ.ም የወጣው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈጻሚ አካላት ማቋቋሚያ አዋጅ፤ ቢሮዎች “ለስራ ቅልጥፍና አስፈላጊ” ሆኖ ሲያገኙት ስልጣን እና ተግባራቸውን “በከፊል” ለሌላ አስፈጻሚ አካል በውክልና መስጠት እንደሚችሉ ደንግጓል። ይህንን መነሻ በማድረግ የከተማይቱ ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ፤ ላለፉት ሰባት ወራት ገደማ ጥናት ሲያደርግ እና ሲዘጋጅ መቆየቱን የቢሮ ኃላፊዋ አመልክተዋል። በዛሬው ውይይት ላይ የቀረበው የቢሮው ጥናት፤ የመንግስት ስራዎችን ወደ ግል አካላት ማስተላለፍ አገልግሎቶችን “በተሻለ መልኩ ውጤታማ ያደርጋል” የሚል ድምዳሜ አሳይቷል።
ይህ አሰራር የከተማ አስተዳደሩ ስራውን ለማከናወን የሚያወጣቸውን አስተዳደራዊ ወጪዎች እንደሚያስቀር በፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ አማካሪ የሆኑት አቶ ተፈራ ሙሉነህ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። ለግል ተቋማት ተላልፈው ቢሰጡ መንግስት ሲያወጣው የቆየውን ወጪ ከሚቀንሱ አገልግሎቶች መካከል አማካሪው በምሳሌነት የጠቀሱት የንግድ ፈቃድ አገልግሎትን ነው። ይህ አገልግሎት ከተጠቃሚዎች ክፍያ የሚፈጸምበት በመሆኑ ስራውን የሚረከቡ የግል አካላት ከዚህ ገቢ እንደሚያገኙ የሚገልጹት አቶ ተፈራ፤ በአንጻሩ ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ለሰራተኞች ደመወዝ እና ለሌሎች አስተዳደራዊ ስራዎች የሚያወጣው ገንዘብ እንደሚያስቀርለት ያብራራሉ።
ከንግድ ፈቃድ አገልግሎት ሌላ “መንግስት የተቆጣጣሪነት ስራ የማያከናውንባቸው” የተባሉ የስራ ዘርፎችም፤ ለግል አካላት እንዲተላለፉ መታሰባቸው ተነግሯል። በዚህ የስራ ዘርፍ ካሉት ውስጥ የተወሰኑቱ፤ ለሶስተኛ ወገን ከመተላለፋቸው በፊት አዋጭነታቸው ታይቶ ውሳኔ የሚሰጥባቸው እንደሚኖሩም በዛሬው የውይይት መድረክ ተገልጿል። በቢሮው ጥናት ላይ ለግል አካላት የማይተላለፉ እና በመንግስት ብቻ መሰራት ያለባቸው የአገልግሎት አይነቶች እንዳሉም ሰፍሯል። ከእነዚህ ውስጥ ከመሬት ካርታ እና ከመኪና ሊብሬ ጋር የተያያዙ ስራዎች ይገኙበታል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መስሪያ ቤቶች የሚያከናውኗቸውን ስራዎች ለግል አካላት ለማስተላለፍ ሶስት አይነት አማራጮች መቅረባቸውን አቶ ተፈራ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የመጀመሪያው “ለግል ባለሀብት እና ተቋማት መስጠት” የሚለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እነዚህን ስራዎች “ተደራጅተው ለማከናወን ፍላጎት ላላቸው የየመስሪያ ቤቶቹ ሰራተኞች ማስተላለፍ” እንደሆነ አመልክተዋል። በሶስተኛ አማራጭነት የቀረበው ደግሞ ስራዎቹን “የተደራጁ ወጣቶች እንዲሰሯቸው” ማድረግ መሆኑን አክለዋል።
እነዚህ አማራጮች ተግባራዊ የሚሆኑት፤ ለግል አካላት የሚተላለፈው ስራ የሚፈልገውን የገንዘብ አቅም እና የሰው ኃይል ብቃት መሰረት በማድረግ መሆኑን አማካሪው አስረድተዋል። “ ‘ትልቅ አቅም፣ ጉልበት፣ ብቃት ይፈልጋሉ’ የሚባሉ መስፈርቶች ካሉ፤ ለግሉ ሴክተር [እና] አቅም ላላቸው ሊሰጥ ይችላል፡፡ ‘ቴክኒካል ብቻ ነው ብዙ ገንዘብ አይፈልግም’ የሚባሉ ነገሮች ካሉ ሰራተኛው ራሱ ይወስዳቸዋል። ወይም ደግሞ ‘ወጣቶች ተደራጅተው ይስሩት’ የሚል ውሳኔም ካለ ለእነሱ የሚሰጥበት [አሰራር ይኖራል]” ሲሉ አቶ ተፈራ አብራርተዋል።
ለሶስተኛ ወገን የሚተላለፈው ስራ በቢሮው ሰራተኞች ሊሰራ የሚችል ከሆነ፤ ፍላጎት ያላቸው ሰራተኞች እንዲደራጁ ተደርጎ “ያለ ጨረታ በቀጥታ” ስራውን እንዲረከቡ እንደሚደረግ ዛሬ በተካሄደው ውይይት ላይ የቀረበው ጥናት አመልክቷል። የግል ባለሀብቶች እና ተቋማትን አቅም የሚፈልጉ ስራዎች ላይ ደግሞ ጨረታ በማውጣት መረጣ እንደሚካሄድ በዚሁ ጥናት ተጠቅሷል። ስራ ፈላጊ ወጣቶች ሊሰሩ በሚችሏቸው ዘርፎች ላይ ወጣቶቹን የማደራጀት ስራ እንደሚከናወንም በጥናቱ ላይ ሰፍሯል።
የከተማዋ መስሪያ ቤቶችን አገልግሎቶች ተረክበው የሚያከናውኑ አካላት የሚመረጡት፤ ለዚሁ ተብሎ በሚቋቋም ራሱን የቻለ መስሪያ ቤት እንደሆነ አቶ ተፈራ ተናግረዋል። ይህ መስሪያ ቤት ተጠሪ የሚሆነው ለፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ እንደሚሆንም ገልጸዋል። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚሰጡ አገልግሎቶችን “ለግል አካላት የማስተላለፍ፣ ሂደቱን የማመቻቸት እና የመደገፍ” ስልጣን የሚኖረው አዲስ የሚቋቋመው መስሪያ ቤት፤ ስራዎቹ በትክክል እየሄዱ ስለመሆኑ የመከታተል እና በየዓመቱ “የውጤታማነት ፍተሻ” የማካሄድ ኃላፊነትም ይጣልበታል ተብሏል።
ይህንን መስሪያ ቤት የሚያቋቋም እና በአጠቃላይ የመንግስት ስራን ወደ ግል አካላት የማዘዋወር ስራን የሚመራ ደንብ ተዘጋጅቶ ውይይት እየተደረገበት መሆኑን አማካሪው አስታውቀዋል። ይህ ደንብ፤ የመንግስት አገልግሎቶች ለግል አካላት በመተላለፍቸው ምክንያት ከስራቸው የሚነሱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኞችን ዕጣ ፈንታን የተመለከተ ክፍል እንዳለውም አቶ ተፈራ ጠቁመዋል። በዚህ መልኩ ከስራቸው ለሚነሱ ሰራተኞች ከቀረቡ አማራጮች መካከል፤ ወደ ሌሎች የመንግስት መስሪያ ቤቶች አዘዋውሮ ማሰራት፣ ድጎማ ማድረግ፣ ብድር ማመቻቸት እና ስልጠና መስጠት የሚሉት ይገኙበታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)