በሰሜን ኢትዮጵያው የግጭት ማቆም ስምምነት አፈጻጸም ላይ ለመወያየት፤ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ወደ አዲስ አበባ ሊመጡ ነው

የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት ባለፈው ጥቅምት ወር በተፈራረሙት የግጭት ማቆም ስምምነት አፈጻጸም ላይ ለመነጋገር፤ የአሜሪካ አፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር በድጋሚ ወደ አዲስ አበባ ሊመጡ ነው። ሐመር ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግስት እና ከአፍሪካ ህብረት ባለስልጣናት ጋር በአዲስ አበባ፤ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ጋር ደግሞ በመቐለ ከተማ በመጪዎቹ ቀናት እንደሚወያዩ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታውቋል።

ማይክ ሐመር ከነገ ረቡዕ ግንቦት 23፤ 2015 ጀምሮ ለሰባት ቀናት በአፍሪካ ቀንድ የሚያደርጉት ቆይታ፤ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ጅቡቲንም ያካተተ መሆኑን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቃል አቃባይ ጽህፈት ቤት ገልጿል። አምባሳደር ሐመር ወደ ጀቡቲ የሚጓዙት ሀገሪቱ በምታስተናግደው የምስራቅ አፍሪካ የጸጥታ ፎረም ስብሰባ ላይ ለመገኘት መሆኑን የቃል አቃባይ ጽህፈት ቤቱ ዛሬ ባወጣው መግለጫው አመልክቷል።

በአሜሪካ ጦር የአፍሪካ ዕዝ ስር ባለው የአፍሪካ ቀንድ የጋራ ግብረ ኃይል የተዘጋጀው የጅቡቲው ስብሰባ፤ በቀውስ ወቅት የሚሰጡ ምላሾችን እና የጸጥታ ስጋቶችን የመከላከል ጥረቶችን ማቀናጀት በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ የሚመክር ነው። ሐመር በጅቡቲ በሚኖራቸው ቆይታ፤ በቀጠናዊ እና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከሀገሪቱ ባለስልጣናት ጋር እንዲሁም ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) ዋና ጸሀፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር እንደሚወያዩ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ገልጿል።

የአሜሪካ አፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አዲስ አበባ ከደረሱ በኋላም በተመሳሳይ መልኩ ከአፍሪካ ህብረት ኃላፊዎች ጋር ውይይት ለማድረግ ማቀዳቸው ተነግሯል። አምባሳደር ሐመር በዚህ ውይይታቸው ዋነኛ ትኩረት የሚሆነው፤ የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት ባለፈው ጥቅምት ወር በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተፈራረሙት የግጭት ማቆም ስምምነት አፈጻጸም እንደሚሆን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቃባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ልዩ ልዑኩ የስምምነቱን አፈጻጸም ሂደት በተመለከተ፤ ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት እና ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ጋር እንደሚወያዩም የጽህፈት ቤቱ መግለጫ አክሏል። በአዲስ አበባ እና በመቐለ ከተሞች በሚደረጉት በእነዚህ ውይይቶች፤ የሽግግር ጊዜ ፍትህን እና ተጠያቂነትን ለማስፈን በሚደረጉ ጥረቶች ያለውን ሂደት የተመለከቱ ጉዳዮች እንደሚነሱ የቃል አቃባይ ጽህፈት ቤቱ ገልጿል። በውጊያ ላይ የቆዩ ኃይሎችን ትጥቅ የማስፈታት፣ እንዲበተኑ የማድረግ እና እንደገና ወደ ህብረተሰቡ የመዋሃድ ሂደትም የእነዚሁ ውይይቶች ሌላኛው አጀንዳ እንደሚሆን የጽህፈት ቤቱ መግለጫ አመልክቷል። 


ማይክ ሐመር ለመጨረሻ ጊዜ ወደ አዲስ አበባ የመጡት ባለፈው ሚያዝያ ወር አጋማሽ ነበር። ልዩ ልዑኩ በሚያዝያው የአዲስ አበባ ቆይታቸው ወቅትም የፕሪቶሪያውን የግጭት ማቆም ስምምነት አፈጻጸም በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት እና ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል። የኢትዮጵያ መንግስት የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እንዲያበቃ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና በሰጠበት ወቅትም፤ ልዩ ልዑኩ በስፍራው ተገኝተው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እጅ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)