በተስፋለም ወልደየስ
ገዢው ብልጽግና ፓርቲ “የነጠላ ቡድናዊ ፍላጎታቸውን በኃይል ለማሳካት የሚጥሩ” እና “ጽንፈኛ የሆኑ” ያላቸው አካላት ባለፉት ወራት በእጅጉ እንደፈተኑት አስታወቀ። በነጻነት አስተዳደር እና አጠቃቀም መካከል “ሚዛን ለማስጠበቅ” በሚደረግ ጥረት ረገድም “ፈተናዎች” እና “ጉድለቶች” ማጋጠማቸውንም ገልጿል።
ይህ የተገለጸው ለሁለት ቀናት መደበኛ ስብሰባውን ሲያካሄድ የቆየው የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባውን ዛሬ ረቡዕ ግንቦት 23፤ 2013 ማጠናቀቁን ተከትሎ ነው። የገዢው ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በዚሁ ስብሰባዎች የተወያየባቸውን ጉዳዮች እና ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች በተመለከተ ገለጻ ያደረጉት የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፤ ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት ወራት “ከፖለቲካ አንጻር የገጠሙት ፈተናዎች እንደነበሩ” ተናግረዋል።
“ባለፉት ወራት…የነጠላ ቡድናዊ ፍላጎታቸውን በኃይል ለማሳካት ፍላጎት ያላቸው የሚጥሩ አካላት፤ በተለይ ጽንፈኛ የሆኑ አካላት፤ ሀገራዊ አንድነታችንን በህብረ ብሔራዊ መሰረት ላይ በጽኑ እንዳንገነባ እጅጉኑ ፈትነውናል” ያሉት አደም ፋራህ፤ ፓርቲው ያጋጠመውን ይህን “ፈተና ለመሻገር” የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል። የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ስራዎቹ ምን እንደነበሩ በዝርዝር ባይገልጹም፤ “ከዚህ አንጻር የተጠናከረ ስራ መስራት ያስፈልጋል” ብለዋል።
አቶ አደም በፈተናነት የጠቀሱት ሌላው “በነጻነት አስተዳደር እና አጠቃቀም መካከል” ያለውን “ሚዛን ማስጠበቅ” ነው። “ፓርቲያችን ለነጻነት ትልቅ ቦታ የሚሰጥ ነው። በቀጣይም ያንን አጠናክሮ መቀጠል ይፈልጋል” ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤ ነገር ግን ዜጎች የነጻነት መብታቸውን ለመጠቀም ጥረት ሲያደርጉ “ግዴታቸውንም በአግባቡ የሚወጡበት ሁኔታ መፍጠር ይጠይቃል” ሲሉ ብልጽግና ፓርቲ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ያለውን አቋም አብራርተዋል።
“ዜጎች፣ የተለያዩ ቡድኖች፤ የነጻነት መብታቸውን ለመጠቀም በሚያደርጉት ጥረት የሌሎች ግለሰቦችን እና ቡድኖችን ነጻነት መጋፋት የለባቸውም። መብታቸውን ሊነኩ አይገባም። ከዚህ አንጻር በነጻነት አጠቃቀም እና አስተዳደር መካከል ሚዛን መጠበቅ ያስፈልጋል” ሲሉም አቶ አደም አጽንኦት ሰጥተዋል። ይህንን ሚዛን በማስጠበቅ ረገድ “ጉድለቶች እንደነበሩ” እና ችግሮቹን ለመፍታት የተጀመሩ ስራዎች እንዳሉ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል።
የብልጽግና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ “የነጻነት አስተዳደርን” ጉዳይ በፈተናነት ሲጠቀስ የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም። የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባለፈው መጋቢት ወር ባካሄደው ስብሰባ ወቅትም፤ “ነጻነትን ማስተዳደር አለመቻል” በኢትዮጵያ እየታዩ ካሉ ተግዳሮቶች አንዱ መሆኑን አስታውቆ ነበር። ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ከስብሰባው መጠናቀቅ በኋላ በወቅቱ ባወጣው መግለጫ፤ የአካባቢ አስተዳደሮች፣ ሚዲያዎች፣ የእምነት ተቋማት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና አክቲቪስቶች “ነጻነትን የማስተዳደር ችግሮች ተስተውሎባቸዋል” ሲል ወንጅሎ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)