በደቡብ ኦሞ ዞን በተከሰተ የኮሌራ እና ወባ ወረርሽኝ፤ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በበሽታዎቹ መያዛቸው ተገለጸ 

በአማኑኤል ይልቃል

በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን በአምስት ወረዳዎች የኮሌራ እና ወባ ወረርሽኞች መከሰታቸውን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ። በዞኑ ውስጥ ባለው ዳሰነች ወረዳ በዚህ ሳምንት ብቻ 3,800 ገደማ ሰዎች በወባ መሽታ መያዛቸው እንደተረጋገጠም መምሪያው ገልጿል። 

በስሩ አስር ወረዳዎች እና ሶስት የከተማ አስተዳደሮችን የያዘው የደቡብ ኦሞ ዞን፤ 800 ሺህ ገደማ ነዋሪዎች እንዳሉት ይገመታል። ከእነዚህ የዞኑ መዋቅሮች ውስጥ የኮሌራ ወረርሽኝ የተከሰተው በሐመር፣ በና ጸማይ፣ ማሌ እና ሰሜን አሪ በተባሉት አራት ወረዳዎች መሆኑን የደቡብ ኦሞ ዞን ጤና መምሪያ የጤና እና ጤና ነክ ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ነጋሽ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

በወረዳዎቹ በሚገኙ 27 ቀበሌዎች የሚኖሩ 248 ሰዎች በኮሌራ መጠቃታቸውን እና በወረርሽኙ ሳቢያ አንድ ሰው መሞቱን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ህይወቱ ያለፈው የሰሜን አሪ ወረዳ ነዋሪ በወረርሽኙ ከተያዘ በኋላ “ወደ ህክምና ባለመምጣቱ” ህመሙ ተባብሶ ለሞት መዳረጉን አቶ ዮሐንስ አስረድተዋል። የኮሌራ ወረረሽኙ ከአካባቢው ነዋሪዎች በተጨማሪ በበና ጸማይ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው “ናሳ እርሻ ልማት” የተቀጠሩ የቀን ሰራተኞች ላይ መታየቱንም አክለዋል።

በወባ ወረርሽኝ በተጠቃው ዳሰነች ወረዳ ደግሞ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ ሰባት ሺህ ገደማ ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸውን በዞኑ የጤና እና ጤና ነክ ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። በወረዳው በወረርሽኙ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በእጥፍ እየጨመረ መምጣቱን የገለጹት አቶ ዮሐንስ፤ በዚህ ሳምንት 3,800 ገደማ ሰዎች የወባ በሽታ እንዳለባቸው በምርመራ መረጋገጡን አመልክተዋል። 

በአካባቢው ከዚህ ቀደምም የወባ በሽታ የሚከሰት ቢሆንም፤ ባለፉት ሳምንታት በታየው ልክ የበሽተኞች ቁጥር በፍጥነት ጨምሮ እንደማያውቅም አብራርተዋል። በዳሰነች ወረዳ ለተከሰተው የወባ ወረርሽኝ በምክንያትነት የሚጠቀሰው፤ በአካባቢው ያሉ ሜዳማ ቦታዎች በጎርፍ መጥለቅለቃቸው ነው። የኦሞ ወንዝ ሞልቶ በመፍሰሱ ምክንያት በውሃ የተሸፈኑት እነዚህ ሜዳማ ቦታዎች፤ ለወባ ትንኝ መራቢያነትን ምቹ ሁኔታን መፍጠሩን የደቡብ ኦሞ ዞን ጤና መምሪያ አስታውቋል። 

በደቡብ ኦሞ ዞን አራት ወረዳዎች የታየው የኮሌራ ወረርሽኝ መነሻ፤ በአቅራቢያ ከሚገኙት ጋሞ እና ጎፋ ዞኖች በሽታው ከመከሰቱ ጋር የተያያዘ መሆኑን የዞኑ ጤና መምሪያ ጨምሮ ገልጿል። “እነዚህ [ዞኖች] በተለይ ማሌ ከሚባለው ወረዳ ጋር አጎራባች ናቸው። እዚህ አካባቢ ሰው የሚጠጣው ወራጅ ውሃ በኮሌራ ተበክሏል። ያንን ውሃ የጠጣ በጠቅላላ እየታመመ ነው” ሲሉ አቶ ዮሐንስ ወረረሽኙ በዞኑ ወዳሉ ወረዳዎች የተስፋፋበትን መንስኤ አብራርተዋል። 

በዞኑ የተስፋፋውን የኮሌራ እና የወባ ወረርሽኝ ለመከላከል የጤና ባለሙያዎች “ሙሉ ትኩረታቸውን” በዚያ ላይ ማድረጋቸውን የሚናገሩት አቶ ዮሐንስ፤ በዚህም የተነሳ ሁኔታዎች እየተሻሻሉ መምጣታቸውን ይገልጻሉ። ሆኖም ወረርሽኞቹን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ግን የተወሰነ ጊዜ ሊወስድ ይችላል ባይ ናቸው። አርብቶ አደር የሆኑት የአካባቢው ነዋሪዎች የአኗኗር ዘይቤ ለበሽታዎቹ  የሚያጋልጥ መሆኑ፤ የዞኑ ጤና መምሪያ ወረርሽኞቹን ለመቆጣጠር ለሚያከናውናቸው ስራዎች ፈተና እንደሆነበትም አክለዋል። 

የጤና ሚኒስቴር ባለፈው መጋቢት ወር ባወጠው መግለጫ፤ የኮሌራ ወረርሽኝ በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 18 ወረዳዎች ውስጥ መከሰቱን አስታውቆ እንደነበር አይዘነጋም። በኢትዮጵያ ያለው የወባ በሽታ ስርጭትም ካለፉት አምስት ዓመታት “በተለየ ሁኔታ ከፍ ብሎ” እንደታየም በወቅቱ ገልጾ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)