የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለመጪው 2016 የበጀት ዓመት 801.65 ቢሊዮን ብር በጀት አጸደቀ። የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ካቢኔ ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ያጸደቀው በጀት፤ ካለፈው ዓመት በ15.05 ቢሊዮን ብር የላቀ ነው።
ለ2016 ከተዘጋጀው በጀት ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው የፌደራል መንግስት መደበኛ ወጪ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ዛሬ ግንቦት 29፤ 2015 ባወጣው መግለጫ፤ ለመደበኛ ወጪ የተመደበው በጀት 396.6 ቢሊዮን ብር መሆኑን አስታውቋል። ይህ የገንዘብ መጠን ከ2015 ጋር ሲነጻጸር በ51.5 ቢሊዮን ብር ጭማሪ ያሳየ ነው።
ከአንድ ወር ገደማ በኋላ በሚጠናቀቀው የዘንድሮ የበጀት ዓመት፤ ለመደበኛ የመንግስት ወጪ ተመድቦ የነበረው ገንዘብ 345.1 ቢሊዮን ብር ነበር። በቀጣዩ በጀት ዓመት ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ፤ እንደ መደበኛ ወጪ ሁሉ ጭማሪ አሳይቷል። ለክልሎች የሚሰጠው ድጋፍ ከተያዘው በጀት ዓመት በ4.67 ቢሊዮን ብር ጨምሮ 214.07 ቢሊየን ብር ደርሷል።
ለመጪው በጀት ዓመት ለካፒታል ወጪዎች የተመደበው የገንዘብ መጠን ግን ቅናሽ ታይቶበታል። ለ2016 የካፒታል ወጪዎች የተመደበው 203.9 ቢሊየን ብር ሲሆን፤ ይህ መጠን ከተያዘው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ14.2 ቢሊዮን ብር አንሷል። መንግስት ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ የመደበው 14 ቢሊዮን ብር፤ ከዘንድሮው ዓመት ጋር ተመሳሳይ ነው።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ ያስተላለፈው የ2016 በጀት 801.65 ቢሊዮን ብር መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በዛሬው መግለጫው አስታውቋል። የፌደራል መንግስት በጀት ባለፉት አምስት አመታት ከ107 ፐርሰንት በላይ ጭማሪ አሳይቷል።
በ2012 የፌደራል መንግስት አጠቃላይ በጀት 386.9 ቢሊዮን ብር ነበር። በቀጣዩ 2013 የበጀት መጠኑ በ89.1 ቢሊዮን ጭማሪ አሳይቶ ወደ 476 ቢሊዮን ብር ከፍ ብሏል። የ2014 በጀት በአንጻሩ ከቀደመው ዓመት ከ207.7 ቢሊዮን ብር በላይ ለውጥ የታየበት ነበር።
በግንቦት 2013 የሚኒስትሮች ምክር ቤት 561. 7 ቢሊዮን ብር አጽድቆ የነበረ ቢሆንም የፌደራል መንግስት ተጨማሪ 122 ቢሊዮን ብር አስፈልጎታል። በጥር 2014 የጸደቀው ተጨማሪ በጀት “ለሀገር ደህንነት ማስጠበቂያ፣ ለሰብዓዊ እርዳታ፣ በጦርነት እና ግጭቶች ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ማቋቋሚያ እንዲሁም ለሌሎች አስፈላጊ የመንግስት ስራዎች ማስፈጸሚያ” የተዘጋጀ እንደነበር የገንዘብ ሚኒስቴር በወቅቱ አስታውቋል።
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በፌደራል መንግስት በጀት ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ከ2014 ወደ 2015 ጭምር የተሻገረ ነው። ለፌደራል መንግስት ለ2015 ያጸደቀው በጀት ወደ 786.6 ቢሊዮን ብር ከፍ ቢልም፤ በዘጠኝ ወራት ብቻ 194.6 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት እንደገጠመው የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ለተወካዮች ምክር ቤት ተናግረው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)