በአማኑኤል ይልቃል
የወላይታ ዞን ወደፊት በሚመሰረተው የ“ደቡብ ኢትዮጵያ” ክልል ውስጥ ከሌሎች ዞን እና ወረዳዎች ጋር እንዲደራጅ መወሰኑን የተቃወሙ ሁለት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ላይ በፍርድ ቤት ክስ መሰረቱ። ፓርቲዎቹ በክስ ማመልከቻቸው ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የወላይታ ዞን ከሌሎች መዋቅሮች ጋር እንዲደራጅ ያሳለፈው ውሳኔ እንዲሻር እና የዞኑ ምክር ቤት ከአራት ዓመት ተኩል ገደማ በፊት ወላይታ ክልል እንዲሆን የሰጠው ውሳኔ እንዲጸና ጠይቀዋል።
ይህንን ክስ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረቡት፤ በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን ውስጥ የሚንቀሳቀሱት የዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ዎሕዴግ) እና የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ዎብን) ናቸው። ሁለቱ ፓርቲዎች የክስ መዝገቡን በፍርድ ቤት የከፈቱት ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ግንቦት 24፤ 2015 መሆኑን የዎብን ሊቀመንበር አቶ አማኑኤል ሞጊሶ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
ዎሕዴግ እና ዎብን ክሱን ባለፈው ሳምንት ቢመሰርቱም፤ ጉዳዩ በየትኛው ችሎት መታየት እንዳለበት ለመወሰን እስከ ዛሬ ረቡዕ ግንቦት 30፤ 2015 በተለያዩ ችሎቶች ሲዘዋወር መቆየቱን የዎሕዴግ ሊቀመንበር አቶ ጎበዜ ጎአ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። በጉዳዩ ለመወሰን ለዛሬ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ የፓርቲዎቹ ክስ “በመሰረታዊ መብቶች እና ነጻነት ችሎት” እንዲታይ መወሰኑንም አስረድተዋል።
በዚሁ ችሎት ከነገ በስቲያ መታየት የሚጀምረው የሁለቱ ፓርቲዎቹ ክስ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በደቡብ ክልል የሚገኙ 11 መዋቅሮችን በተመለከተ በነሐሴ 2014 ዓ.ም. የሰጠውን ውሳኔ በመቃወም የቀረበ ነው። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከዘጠኝ ወር በፊት ባደረገው አስቸኳይ ጉባኤ፤ ወላይታ ዞንን ጨምሮ በደቡብ ክልል የሚገኙ 11 ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ያቀረቡትን በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ ተቀብሎ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል። ዎሕዴግ እና ዎብን የፌዴሬሽን ምክር ቤት “በህግ ከተሰጠው ስልጣን ውጪ” አሳልፎታል ያሉት ይህ ውሳኔ እንዲሻር መጠየቃቸውን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ፓርቲዎቹ ካቀረቡት ክስ ተመልክታለች።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የወላይታ ዞን ምክር ቤት በክልል መደራጀትን በተመለከተ ከዓመታት በፊት አቅርቦት ለነበረው አቤቱታ ምላሽ ሳይሰጥ ይህን ውሳኔ ማሳለፉ፤ በሕገ መንግስቱም ይሁን ምክር ቤቱን ባቋቋመው አዋጅ “የሕግ መሰረት የሌለው ነው” ሲሉ ሁለቱ ፓርቲዎች በክሳቸው መከራከሪያ አቅርበዋል። ምክር ቤቱ ይህን ውሳኔ በመስጠቱ ምክንያትም ቀድሞ በቀረበው ጥያቄ ላይ “ለህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ አቤቱታ የማቅረብ” እና “ውሳኔው እንደገና እንዲታይ” የማድረግ መብት “መጣሱም” በክሱ ላይ ተመላክቷል።
የወላይታ ዞን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት ጥያቄን በተመለከተ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የይግባኝ አቤቱታ ያስገባው በታህሳስ 2012 ዓ.ም. ነበር። ለዚህ አቤቱታ መነሻ የሆነው የዞኑ ምክር ቤት ያሳለፈውን የመደራጀት ውሳኔ፤ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ተቀብሎ ምላሽ አለመስጠቱ ነበር። በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት መሰረት፤ ይህን መሰል ጥያቄ የቀረበለት የክልል ምክር ቤት ጥያቄው በደረሰው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ እንዲደራጅ ማድረግ ይኖርበታል።
ይህ ተፈጻሚ ባለመሆኑ በታህሳስ 2012 ዓ.ም ይግባኝ የቀረበለት የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአቤቱታው ላይ “ምንም አይነት ውሳኔ ሳይሰጥ በእንጥልጥል” ማቆየቱ፤ የምክር ቤቱን ማቋቋሚያ አዋጅን የሚቃረን እንደሆነ ሁለት ፓርቲዎቹ በክሳቸው ላይ ጠቅሰዋል። ፓርቲዎቹ የጠቀሱት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ፤ ክልልነትን በተመለከተ በቀረቡ ጉዳዮች ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሁለት ዓመት ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጥ ደንግጓል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የመጨረሻ ውሳኔውን እንዲሰጥ የሚጠበቅበት ቀነ ገደብ ከተጠናቀቀ ከስምንት ወር በኋላ ያስተላለፈው ሌላ ውሳኔም በፓርቲዎቹ ተቃውሞ ቀርቦበታል። ይህ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ውሳኔ፤ የወላይታ ዞንን ጨምሮ በደቡብ ክልል ስር የሚገኙ 11 ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች በአንድ ላይ ለመደራጀት ያቀረቡትን ጥያቄ ያጸደቀ ነው። የእነዚህን ዞኖቹ እና ልዩ ወረዳዎችን አንድ ክልል የመመስረት ጥያቄ ተቀብሎ፤ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በሐምሌ 2014 ዓ.ም. ያስገባው የደቡብ ክልል ምክር ቤት ነው።
የወላይታ ዞን ምክር ቤት “የወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት” እንዲመሰረት ቀደም ሲል ያስተላለፈውን ውሳኔ በመቀየር፤ በገዢው ፓርቲ የቀረበውን በ“ክላስተር” የመደራጀት ውሳኔ አጽድቆ ለደቡብ ክልል ምክር ቤት ያስተላለፈው በሐምሌ 2014 ዓ.ም. ነበር። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከደቡብ ክልል ምክር ቤት የቀረበለትን ጥያቄ መሰረት በማድረግ፤ የ“ደቡብ ኢትዮጵያ” ክልልን ለመመስረት የሚያስችል ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ በነሐሴ 2014 ዓ.ም. መወሰኑ ይታወሳል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይህን ውሳኔ ያስተላለፈው “ከስልጣኑ ውጪ በሕግ ባልተጻፈ አካሄድ ነው” ሲሉ ዎሕዴግ እና ዎብን በክሳቸው ላይ አስፍረዋል። ሁለቱ ፓርቲዎች ከዚህ በተጨማሪም ቀድሞ የተላለፈን በክልልነት የመደራጀት ውሳኔን በመቀልበስ በክላስተር የመደራጀት ውሳኔ ያጸደቀውን የወላይታ ዞን ምክር ቤትን ህጋዊነት አጠይቀዋል። የዞን እና የወረዳ ምክር ቤቶች ምርጫ የሚካሄደው በየአምስት ዓመቱ መሆኑን በክሳቸው ያስታወሱት ፓርቲዎቹ፤ የወላይታ ዞን ምክር ቤቱ “የምርጫ ዘመኑ ያበቃ” መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን በስራ ያለው የወላይታ ዞን ምክር ቤት “በዞኑ ጉዳይ ላይ ብቻ ሳይሆን ዞኑን ለማስተዳደር በሕገ መንግስቱ መሰረት ስልጣን የሌለው ነው” ሲሉም ተሟግተዋል። ይህንን መሰረት በማድረግም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባለፈው ነሐሴ ወር ካስተላለፈው ውሳኔ ላይ “የዎላይታ ብሔርን የሚመለከተው ብቻ ሙሉ በሙሉ ከውሳኔው እንዲሰረዝ” ሁለቱ ፓርቲዎች በክሳቸው ላይ ጠይቀዋል።
በ“ክላስተር” መደራጀትን በተመለከተ የወላይታ ዞን ምክር ቤት ያስተላለፈው ውሳኔም በተመሳሳይ መልኩ እንዲሻር ሁለቱ ፓርቲዎች ጥያቄያቸውን ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበዋል። ፓርቲዎቹ ከዚህ በተጨማሪ፤ የወላይታ ዞን ምክር ቤት ከአራት ዓመት በፊት ያስተላለፈው እና ከሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ምላሽ ያላገኘው ራስ ችሎ በክልልነት የመደራጀት ውሳኔ “እንዲጸና” ለፍርድ ቤቱ አቤት ብለዋል።
ዎሕዴግ እና ዎብን በፌዴሬሽን ምክር ቤት ላይ ክስ የመሰረቱት፤ በምክር ቤቱ ውሳኔ መሰረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በወላይታ ዞን ህዝበ ውሳኔ ለማድረግ እየተዘጋጀ ባለበት ወቅት ነው። ምርጫ ቦርድ የ“ደቡብ ኢትዮጵያ” ክልልን ለመመስረት የሚያስችለውን ህዝበ ውሳኔ በአስራ አንዱም የደቡብ ክልል መዋቅሮች ባለፈው ጥር ወር መጨረሻ ቢያካሄድም፤ በወላይታ ዞን የተደረገውን ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል።
ቦርዱ ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው በወላይታ ዞን ህዝበ ውሳኔ በተካሄደበው ወቅት የተፈጸመው “መጠነ ሰፊ” ጥሰት “የምርጫ ሂደቱን ተዓማኒነት እና እውነተኝነት ያሳጣ እና አጠቃላይ የምርጫ ውጤቱንም የሚያዛባ” መሆኑን በመግለጽ ነበር። በዚህም መሰረት በዞኑ በድጋሚ ህዝበ ውሳኔ እንዲደረግ ውሳኔ ያሳለፈው ቦርዱ፤ የድምጽ መስጠት ሂደቱን ለማከናወን ለመጪው ሰኔ 12፤ 2015 ቀጠሮ ይዟል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)