የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በመጪው በጀት ዓመት የ7.9 በመቶ እድገት ያስመዘግባል ተብሎ እንደሚገመት የገንዘብ ሚኒስትሩ አስታወቁ

በተስፋለም ወልደየስ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2016 በጀት ዓመት 7.9 በመቶ እድገት እንደሚያስመዘግብ መተንበዩን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ አስታወቁ። የኢትዮጵያ መንግስት በቀጣዩ በጀት ዓመት ሊሰበስብ ባቀደው ገቢ እና ወጪ መካከል የ281 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ የበጀት ጉድለት መታየቱንም ገልጸዋል።

አቶ አህመድ ይህን የገለጹት የ2016 የፌደራል መንግስት በጀትን አስመልክቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዝርዝር መግለጫ ባቀረቡበት ወቅት ነው። የመጪው ዓመት በጀት የተዘጋጀው “የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከገጠሙት ቀውሶች ተላቅቆ ሙሉ ለሙሉ ጤናማ አቋም ላይ እንደሚደርስ ታሳቢ ተደርጎ” እንደሆነ የገንዘብ ሚኒስትሩ ዛሬ ሐሙስ ሰኔ 1፤ 2015 በተካሄደው የፓርላማ ስብሰባ ላይ ባቀረቡት የበጀት መግለጫ ላይ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት ዓመታት በአማካይ 6.1 በመቶ ዕድገት ሲያመዘግብ መቆየቱን ያስታወሱት አቶ አህመድ፤ ሊጠናቀቅ አንድ ወር በቀረው በዘንድሮው በጀት ዓመት ደግሞ በ7.5 በመቶ እንደሚያድግ መገመቱን ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ተጋርጠው የነበሩት ተጽዕኖዎች “በተወሰነ ደረጃ ረገብ በማለታቸው” እና መንግስት ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ እያደረጋቸው ያሉ ጥረቶች “የተሻለ ዕድል” የሚፈጥሩ መሆናቸው ለዚህ ዕድገት መመዝገብ ታሳቢ መደረጋቸውን የገንዘብ ሚኒስትሩ አስረድተዋል። 

በቀጣዩ 2016 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 7.9 በመቶ ዕድገት እንደሚያስመዘግብ የተተነበየው፤ መንግስት ሊወስዳቸው ያሰባቸውን ጥብቅ የገንዘብ እና የፊሲካል ፖሊሲ እርምጃዎች ታሳቢ በማድረግ እንደሆነ አቶ አህመድ ለፓርላማ አባላት ገልጸዋል። “ከገንዘብ ፖሊሲ አንጻር በመካከለኛ ዘመን ውስጥ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ተግባራዊ እንደሚደረግ” የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በዚህ ረገድ መንግስት ከሚወስዳቸው እርምጃዎች መካከል “የገንዘብ አቅርቦትን መገደብ” አንዱ እንደሆነ ጠቁመዋል። ከዚህ እርምጃ ጋር በተያያዘ “አሁን የሚታየውን ከፍተኛ የዋጋ ንረት ለማረጋጋት ጥረት እንደሚደረግ” አመልክተዋል። 

ለበጀት ጉድለት መሸፈኛ የኢትዮጵያ መንግስት ከብሔራዊ ባንክ “በቀጥታ የሚወስደው ብድር” ላይም “ከፍተኛ ቅናሽ” እንደሚደረግ የገንዘብ ሚኒስትሩ በዛሬው የበጀት መግለጫ ንግግራቸው ይፋ አድርገዋል። በተለያዩ የገንዘብ ብድር ዘዴዎች (monetary instruments) አማካኝነት ባለፉት ዓመታት “ወደ ኢኮኖሚው ገንዘብ መሰራጨቱን” ያመኑት አቶ አህመድ፤ ይህን “መልሶ ለመሰብሰብ” በገንዘብ ፖሊሲው “እርምጃ እንደሚወሰድ” አስታውቀዋል። በ2016 በጀት ዓመት በአጠቃላይ “ተገቢ የሆነ የገንዘብ አቅርቦት ዕድገት እንዲኖር” እንደሚደረግም አክለዋል። 

በፊሲካል ፖሊሲ ረገድ የኢትዮጵያ መንግስት ትኩረት የሰጠው ዋነኛ ጉዳይ፤ የታክስ ገቢ አሰባሰብ “እመርታዊ ለውጥ” እንዲያመጣ ማድረግ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ለዚህም መንግስት አዳዲስ የታክስ ህጎችን እና በታክስ አስተዳደር ላይ “ትርጉም ያለው ለውጥ” ለማምጣት ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ማቀዱን በንግግራቸው ጠቁመዋል። ማሻሻያ ከሚደረግባቸው መካከል የተጨማሪ እሴት ታክስ፣ የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ እና የኤክሳይዝ ቴምብር ተጠቅሰዋል። የማህበራዊ ዋስትና ልማት ቀረጥ (social welfare develoment duty) የመሳሰሉ ህጎችም ተግባራዊ እንደሚደረጉ ተመላክቷል። 

በ2016 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ መንግስት አገኘዋለሁ ብሎ ያቀደው ጠቅላላ ገቢ 520.6 ቢሊዮን ብር ነው። ከዚህ ውስጥ 84.7 በመቶውን ድርሻ የያዘው ከታክስ ገቢ ለመሰብሰብ የታቀደው 440.8 ቢሊዮን ብር ነው። ይህ የገንዘብ መጠን በዘንድሮው የበጀት ዓመት ይሰበሰባል ተብሎ ከታቀደው የ26.7 በመቶ ጭማሪ ያለው ነው። የኢትዮጵያ መንግስት በመጪው በጀት ዓመት ለታክስ ገቢዎች ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥ ቢያስታውቅም፤ ታክስ ካልሆኑ ምንጮች የሚሰበሰቡ ገቢዎችንም ታሳቢ ማድረጉ በዛሬው የገንዘብ ሚኒስትሩ ንግግር ተነስቷል።

መንግስት የገቢ ዕቅዱን ሲያዘጋጅ የእነዚህን ገቢ አይነቶች ሁኔታ የተመለከተው “አቅምን አሟጦ ለመጠቀም በሚያስችል መልኩ” መሆኑን አቶ አህመድ ተናግረዋል። በ2016 በጀት ዓመት ታክስ ካልሆኑ ምንጮች ለመሰብሰብ የታቀደው የገንዘብ መጠን 38.7 ቢሊዮን ብር ነው። ከዚህ ውስጥ 53.7 በመቶው ያህል መንግስት ለማግኘት ያቀደው፤ ከመንግስት የልማት ድርጅቶች የትርፍ ድርሻ ከሚገኝ ገቢ መሆኑ ተገልጿል። ከታክስ እና ታክስ ካልሆኑ ምንጮች በተጨማሪ የኢትዮጵያ መንግስት ገቢ ለማግኘት ያቀደው ከውጭ እርዳታ ነው።

በቀጥታ በጀት ድጋፍ እና ለተወሰኑ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ እንዲውል፤ ከልማት አጋሮች በእርዳታ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው የገንዘብ መጠን 41.1 ቢሊዮን ብር ነው። ይህ የገንዘብ መጠን በዘንድሮ ዓመት በተመሳሳይ መልኩ ይገኛል ተብሎ ከተገመተው ገቢ አንጻር የ33.4 በመቶ ጭማሪ ቢያሳይም፤ ባለፉት ዓመታት ግን የኢትዮጵያ መንግስት በዚህ ረገድ የጠበቀውን ያህል ገንዘብ ሳያገኝ መቅረቱ ይታወሳል። የገንዘብ ሚኒስትሩ በዛሬው የበጀት ማብራሪያ ንግግራቸውም ይህንኑ እውነታ አስተጋብተዋል። 

“ባለፉት ዓመታት የታክስ ገቢና የውጭ ዕርዳታና ብድር አሰባሰብ ዝቅተኛ አፈጻጸም በማሳየታቸው የተያዘውን ገቢ ዕቅድ ማሳካት አልተቻለም። በተመሳሳይም ከልማት አጋሮች የሚጠበቀው የልማት ድጋፍ በከፍተኛ ደረጃ የቀነሰ ሲሆን፤ በበጀት ድጋፍ መልክ ይገኛል ተብሎ የተያዘው ዕቅድ ሙሉ ለሙሉ ሳይገኝ ቀርቷል” ሲሉ አቶ አህመድ በዚሁ ንግግራቸው አጽንኦት ሰጥተዋል። እነዚህ እና ሌሎች “ዓለም አቀፋዊ” ብሎም “ውስጣዊ” ተጽዕኖዎች፤ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ “ከፍተኛ ጫናዎች ማሳደራቸው” በገንዘብ ሚኒስትሩ የበጀት መግለጫ ላይ ተጠቅሷል።

በበጀት መግለጫው ተደጋግሞ የተነሳው “ከፍተኛ የፋይናንስ እጥረት” ጉዳይ፤ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላጋጠመው ጫና አንዱ ማሳያ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት በመጪው በጀት ዓመት ሊሰበስበው ባቀደው ገቢ እና በእቅድ በያዘው ወጪ መካከል ያለው ጉድለትም ይህንኑ የሚያጠናክር ነው። አቶ አህመድ በዛሬው ንግግራቸው የ281.05 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ በጀት ጉድለት (gross budget deficit) መታየቱን ለፓርላማ አባላት አስታውቀዋል። ይህን የበጀት ጉድለት ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገር በሚወሰድ ብድር ለመሸፈን መታሰቡንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከሀገር ውስጥ ለመበደር ያቀደው 242.04 ብር መሆኑን የጠቀሱት አቶ አህመድ፤ ይህ “በዋጋ ንረት ላይ ተጽዕኖ እንዳይፈጥር” አብዛኛው ብድር “የትሬዠሪ ቢልና የመካከለኛ ዘመን ቦንድ በመሸጥ በመሸጥ ለመውሰድ የታቀደ” መሆኑን አብራርተዋል። መንግስት ሊበደረው ካቀደው የገንዘብ መጠን ውስጥ 53.7 ቢሊዮን ብር ያህሉ ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ብድር ክፍያ የሚውል በመሆኑም፤ የተጣራው የበጀት ጉድለት 227 ቢሊዮን ብር መሆኑን ጠቁመዋል። ይህ የተጣራ የበጀት ጉድለት ከአጠቃላይ የሀገር ምርት ያለው ድርሻም 2.1 በመቶ ብቻ መሆኑንም አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)