ኢትዮጵያ እና አሜሪካ “ከታቀደለት ዓላማ ውጪ ለሽያጭ ውሏል” የተባለውን እርዳታ ጉዳይ ሊመረምሩ ነው

“ከታቀደለት ዓላማ ውጪ ለሽያጭ ውሏል” በተባለው የአሜሪካ የምግብ እርዳታ ጉዳይ ላይ፤ የኢትዮጵያ መንግስት “ሙሉ ምርመራ” ለማድረግ መስማማቱን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታወቀ። ከምርመራው በኋላ ጥፋተኛ ሆነው የሚገኙ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግም የኢትዮጵያ መንግስት ቁርጠኝነቱን መግለጹን መስሪያ ቤቱ ገልጿል።

ይህን ምርመራ በተመለከተ አሜሪካ እና ኢትዮጵያ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውንም የመስሪያ ቤቱ ቃል አቃባይ አስታውቀዋል። ሁለቱ አገሮች ጉዳዩን ለመመርመር የተስማሙት፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና የአሜሪካው አቻቸው አንቶኒ ብሊንከን ዛሬ በሳዑዲ አረቢያ ተገናኝተው ከተወያዩ በኋላ ነው። 

ሁለቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ወደ ሳዑዲ አረቢያ የተጓዙት 81 ሀገራትን በአባልነት በያዘው ዓለም አቀፍ ጥምረት ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ነው። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ከዚሁ ስብሰባ ጎን ለጎን በነበራቸው ውይይት የተለያዩ ጉዳዮች መነሳታቸውን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር ዛሬ ሐሙስ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል። ደመቀ እና ብሊንከን ከተወያዩባቸው ጉዳዮች መካከል “በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ያለውን ውጥረት መፍታትን” የተመለከተው ይገኝበታል ተብሏል። 

ምዕራብ ትግራይን ጨምሮ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶችን ማስከበር እንደሚገባ እንዲሁም ግልጽ እና ሁሉን አቀፍ የሽግግር ፍትህ ሂደት ማፋጠን እንደሚያስፈልግም በውይይቱ ላይ ተነስቷል ተብሏል። በዚሁ ውይይት ላይ በተነሳው የአሜሪካ የምግብ እርዳታ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ያሳየውን ቁርጠኝነት ብሊንከን በበጎ መቀበላቸውንም የመስሪያ ቤታቸው ቃል አቀባይ ገልጸዋል።

ብሊንከን እና ደመቀ የዛሬውን ውይይታቸውን ከመጀመራቸው በፊት ለጋዜጠኞች በሰጡት አጭር ማብራሪያ፤ በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል በፕሪቶሪያ የተፈረመው የግጭት የማቆም ስምምነት በንግግራቸው ትኩረት እንደሚያገኝ ጥቆማ ሰጥተው ነበር። በመጋቢት ወር አዲስ አበባን መጎብኘታቸውን ያስታወሱት የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ በስምምነቱ “አተገባበር እና በትግራይ በፈጠረው ከፍተኛ ለውጥ ተደንቀው” እንደነበር ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። 

“ሰላሙን እንዴት በጋራ ማረጋገጥ ይቻላል?” በሚለው ጉዳይ ላይ ከአቶ ደመቀ ጋር እንደሚወያዩ የጠቀሱት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል ያለው ግንኙነት የሚጠናከርበት መንገድም ሌላው የውይይት ነጥብ እንደሚሆን አክለዋል። አቶ ደመቀ ከብሊንከን ጋር የሚያደርጉትን ውይይት “በጣም ወቅታዊ እና አስፈላጊ” ሲሉ ገልጸውታል። ከብሊንከን የአዲስ አበባ ጉብኝት በኋላ “ተስፋ ሰጪ እርምጃ” እንዳለ ያነሱት አቶ ደመቀ፤ መንግስታቸው “ዋና ዋና ልዩነቶችን ለመፍታት” እየሰራ እንደሚገኝም ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።

የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እንዲቆም ከፍተኛ ግፊት ስታደርግ የቆየችው አሜሪካ፤ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ የአዲስ አበባ ጉብኝት በኋላም የፕሪቶሪያውን ስምምነት አተገባበር በቅርበት እየተከታተለች ትገኛለች። ባለፈው ሳምንት ወደ አዲስ አበባ የመጡት የአሜሪካ አፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር ዋነኛ ትኩረት የስምምነቱ ጉዳይ ሆኖ ታይቷል።

ልዩ ልዑኩ፤ የሰላም ስምምነቱን አተገባበር ለመከታተል በአፍሪካ ህብረት የተቋቋመውን ቡድን እና ኃላፊዎች በመቐለ እና በአዲስ አበባ አግኝተው አነጋግረዋል። በአፍሪካ ህብረት የተቋቋመው እና ባለፈው ታህሳስ 2015 ዓ.ም. ስራውን የጀመረው የክትትል፣ ማረጋገጫ እና ተገዢነት ቡድን የስራ ጊዜ፤ ለመጪዎቹ ስድስት ገደማ ወራት መራዘሙን በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በትላንትናው ዕለት ባወጣው መረጃ አስታውቆ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)