በአማኑኤል ይልቃል
በፌደራል መንግስት እንደ ዘንድሮው ሁሉ በቀጣዩ ዓመትም ለአዳዲስ የካፒታል ፕሮጀክቶች ግንባታ የሚውል በጀት አለመያዙ በፓርላማ ጥያቄ አስነሳ። የፌደራል መንግስት በ2016 በጀት ዓመት ለክልሎች የሚሰጠው የድጎማ በጀት መጠን፤ ከዘንድሮ ዓመት ጋር ሲነጻጸር ያለው ጭማሪ አነስተኛ መሆኑም ጥያቄ ቀርቦበታል።
እነዚህ ጥያቄዎች በፓርላማው የተነሱት፤ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የ2016 በጀት መግለጫን ትላንት ሐሙስ ሰኔ 1፤ 2015 ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ካቀረቡ በኋላ በነበረው የጥያቄ እና ምላሽ ጊዜ ላይ ነው። አቶ አህመድ በትላንቱ ስብሰባ ላይ የ2016 በጀት፤ የመንግስትን የወጪ ፍላጎት ማካተት በማያስችል የፋይናንስ እጥረት ውስጥ የተዘጋጀ መሆኑን አስታውቀዋል።
የፌደራል መንግስት ይህን በጀት ሲያዘጋጅ፤ “የተጀመሩ የካፒታል ፕሮጀክቶችም ቢሆኑ የክፍያ ጊዜያቸውን በማሸጋሸግ የወጪ ቅነሳ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ታሳቢ” ማድረጉን ተናግረዋል። በቀጣዩ ዓመት አዳዲስ የካፒታል ፕሮጀክቶችን በበጀት ውስጥ እንዳይካተት መደረጉን ያነሱት የገንዘብ ሚኒስትሩ፤ በጦርነት የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መመለስ ላይ ትኩረት ለማድረግ መታሰቡን ለፓርላማ አባላቱ አስታውቀዋል።
በ2016 በጀት ዓመት ለክልሎች በድጎማ ሊተላለፍ የታቀደው የበጀት ድጋፍ የተዘጋጀው፤ የፌደራል መንግስት “የግዴታ ወጪዎች እና የበጀት ጫናን” ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን አቶ አህመድ ጨምረው ገልጸዋል። ትላንት ለፓርላማ በቀረበው የበጀት ረቂቅ መሰረት፤ በቀጣዩ ዓመት ለክልሎች ሊተላለፍ የታቀደው የድጋፍ መጠን 214 ቢሊዮን ብር ነው። ይህ የገንዘብ መጠን ከዘንድሮ በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር 2.24 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
ለቀጣዩ ዓመት የቀረበው በጀት ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር “የሀገሪቱን የልማት ፍላጎት ለማሳካት በቂ እንዳልሆነ” ለፓርላማ አባላቱ ያስረዱት የገንዘብ ሚኒስትሩ፤ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማስጨረስ ግን “በቂ” መሆኑን አመልክተዋል። አቶ አህመድ አክለውም፤ የተያዘው በጀት “የገጠሙንን የፊሲካል ተግዳሮቶች በማስተካከል በቀጣይ ጤናማ የፊሲካል አቋም እንዲኖረን ለማድረግ ወሳኝ [ነው]” ብለዋል።
ከገንዘብ ሚኒስትሩ ገለጻ በኋላ የተወካዮች ምክር ቤት አባላቱ በቀረበው የበጀት መግለጫ ላይ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል። ጥያቄ ለማቅረብ እድል ባገኙ የፓርላማ አባላት በተደጋጋሚ ከተነሱ ጉዳዮች ውስጥ፤ የአዳዲስ ፕሮጀክት ግንባታዎች በበጀት ዓመቱ አለመካተቱ እና ለካፒታል ወጪዎች የተመደበው በጀት መቀነስ የሚጠቀሱ ናቸው።
የመጀመሪያውን ጥያቄ ለማቅረብ እድል ያገኙት ወ/ሮ ፀጋነሽ ጋማቶ የተባሉ የተወካዮች ምክር ቤት አባል “በየዓመቱ አዳዲስ የልማት ፕሮጀክቶችን ማስጀመር አይቻልም” እየተባለ በጀት እየጸደቀ መሆኑን በጥያቄያቸው ላይ አንስተዋል። የፓርላማ አባሏ በዚህ ሁኔታ “የህዝቡን የልማት ፍላጎት እንዲሁም በምርጫ ጊዜ ለህዝብ የገባናቸው ቃሎችን እንዴት ማስፈጸም ይቻላል?” ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል።
አቶ ወልደየስ ደበበ የተባሉ የተወካዮች ምክር ቤት አባል በበኩላቸው ባለፈው ዓመት የአዲስ ፕሮጀክቶች ግንባታ እንዳይኖር ተገልጾ እንደነበር አስታወሰው፤ ይህንኑ ለመረጣቸው ማህበረሰብም ይህንኑ መንገራቸውን ጠቅሰዋል። ለተወካዮች ምክር ቤት በቀረበው የበጀት ዝርዝር ላይ ለካፒታል ውጪ የተመደበው ገንዘብ ከአምናው በ6.7 በመቶ መቀነሱን የጠቆሙት እኚሁ የፓርላማ አባል፤ ባለፈው ዓመት “እንዲቋረጡ የተደረጉ የመንገድ ፕሮጀክቶችን” እንዴት ለማስጀመር እንደታቀደ ማብራሪያ ጠይቀዋል።
አቶ ነዚፍ ዝናብ የተባሉ የተወካዮች ምክር ቤት አባል የካፒታል በጀት ቅናሽ ማሳየቱን በተመለከተ ተጨማሪ ጥያቄ ሰንዝረዋል። በአሁኑ ወቅት በህዝብ ዘንድ የሚነሱት አብዛኞቹ ጥያቄዎች ከፕሮጀክቶች አፈጻጸም ጋር የተያያዙ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ነዚፍ፤ ከዚህም አንጻር “የመደበኛ በጀት ቀንሶ የካፒታል በጀት ይጨምራል” የሚል ግምት እንደነበራቸው ገልጸዋል። በጀቱ አመዳደቡ ከዚህ በተቃራኒው የሆነበት ምክንያት እንዲብራራላቸውም ለገንዘብ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርበዋል።
እኚሁ የፓርላማ አባል ለ2016 በተዘጋጀው የበጀት ድልድል ላይ ለክልሎች ድጋፍ የተመደበው የገንዘብ መጠን ካለፈው ዓመት ጋር ሲተያይ “እምብዛም” አለመጨመሩንም ጠቅሰዋል። ክልሎች ባለፉት ሁለት ዓመታት በዞን እና በወረዳ ባሉ መዋቅሮቻቸው የፕሮጀክት ግንባታን አለማስጀመራቸውን የገለጹት አቶ ነዚፍ፤ “የሚመደቡ በጀቶች ደመወዝ ላይ እያለቁ፤ ካፒታል በጀት እንዳይዙ እያደረገ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። በቀጣዩ ዓመት ለክልሎች የሚደረገው ድጎማ “አለመጨመሩ” ይህ ችግር እንዲቀጥል የሚያደርግ በመሆኑ፤ በመፍትሔነት ምን እንደታሰበ ጠይቀዋል።
“ለክልሎች የተመደበው በጀት አንሷል” የሚል ቅሬታ፤ አቶ ብርሃኑ ሃንካራ በተባሉ የፓርላማ አባልም ቀርቧል። በጦርነት እና በድርቅ የተጎዱ እንዲሁም “በጸጥታ ችግር ምክንያት ልማት ያልተሰራባቸው” ክልሎች መኖራቸውን ያስታወሱት አቶ ብርሃኑ፤ አንደ ሲዳማ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ያሉ አዳዲስ ክልሎችም “ልዩ ድጋፍ” ያስፈልጋቸዋል ብለው እንደሚያስቡ ገልጸዋል። የገንዘብ ሚኒስትሩም ከዚህ አንጻር በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል።
ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት አቶ አህመድ ሽዴ፤ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በተለያዩ ምክንያቶች ጫና እያስተናገደ የሚገኝ መሆኑን ለፓርላማ አባላቱ ተናግረዋል። በኢኮኖሚው ላይ ጫናውን ከፈጠሩት ውስጥ፤ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት፣ ከልማት አጋሮች ጋር የሚገኝ የገንዘብ ፍሰት መቀነስ እንዲሁም የዩክሬን ሩስያ ጦርነት በገንዘብ ሚኒስትሩ ተጠቅሰዋል። የሚቀጥለው ዓመት በጀት የተዘጋጀው ሀገሪቱ የምታመነጨው የገቢ መጠን እስከ መጨረሻው መጠን ድረስ “ተለጥጦ” መሆኑን የተናገሩት አቶ አህመድ፤ “አዳዲስ ፕሮጀክቶች ለመያዝ የሚያስችል የገቢ አቅም በሌለበት ‘ዴፌሲቱም’ የዋጋ ጉድለት እንዳያመጣ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ [አለበት]” ሲሉ አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት በግንባታ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ “በጣም ከፍተኛ በጀት” እንደሚጠይቅ ለፓርላማ አባላቱ የተናገሩት የገንዘብ ሚኒስትሩ፤ የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ብቻ ለመጨረስ በቀጣይ ዓመታት ውስጥ “አንድ ትሪሊዮን ብር ያስፈልጋል” የሚል ግምት መኖሩን ገልጸዋል። ዩኒቨርስቲዎች የጀመሯቸው እና የመስኖ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በተመሳሳይ ከፍተኛ በጀት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
“ከዚህ አንጻር ነባር ፕሮጀክቶች በህግም የጸደቁ፤ ፓርላማ ያጸደቃቸው ስለሆነ እነሱ ላይ ትኩረት አድርገን መሄድ አለብን ከሚል አቅጣጫ አንጻር ታይቶ ነው” ሲሉ ከአዳዲስ ፕሮጀክቶች ይልቅ በግንባታ ላይ ላሉ ቅድሚያ የተሰጠበትን ምክንያት አስረድተዋል። ተይዘው የነበሩ ፕሮጀክቶች “በገንዘብ እጥረት” ምክንያት ሽግሽግ እንደተደረገባቸው የጠቆሙት አቶ አህመድ፤ ይህ ማለት ግን ፕሮጀክቶቹ ይዘገያሉ እንጂ “ተቋረጡ” ማለት እንዳልሆነ ከግንዛቤ እንዲወሰድ አሳስበዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ ለክልሎች ለመስጠት ስለታቀደው የድጋፍ በጀትን በተመለከተ የተነሳውን ጥያቄ የመለሱት፤ በቀጣዩ ዓመት ለፌደራል መንግስት ወጪዎች ከተመደበው ገንዘብ ጋር በማነጸጸር ነው። የፌደራል መንግስት ለካፒታል በጀት የመደበውን ገንዘብ መቀነሱን የጠቀሱት አቶ አህመድ፤ ለመደበኛ ወጪ የተመደበውም ቢሆን ከእዳ ክፍያ ውጪ ያለው ካለፈው ዓመት አንጻር ዝቅተኛ መሆኑን አስረድተዋል።
የፌደራል መንግስት ከቋቱ በቀጥታ ለክልሎች የሚያስተላልፈው የድጋፍ በጀት ግን ሳይቀንስ ባለፈው ዓመት ባለበት እንዲቀጥል ማድረጉን ሚኒስትሩ ገልጸዋል። የ2016 የክልሎች የድጋፍ በጀት ላይ የታየው የ2.24 በመቶ ጭማሪም ቢሆን “በብድር እና እርዳታ ከሚመጣው” ላይ ጭማሪ ተደርጎ የመጣ እድገት መሆኑን ለፓርላማ ቤት አባላቱ ተናግረዋል። ክልሎች ከፌደራል መንግስት የሚያገኙት የጋራ ገቢ “በጣም ከፍተኛ” መሆኑን የተናገሩት የገንዘብ ሚኒስትሩ፤ የክልል መንግስታቱ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እንዳላቸው መዘንጋት እንደሌለበት አመልክተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)