ኮንዶሚኒየም ደርሷቸው “በቀበሌ ቤቶች” ውስጥ የሚኖሩ ግለሰቦች፤ በአንድ ወር ውስጥ ቤቶቹን እንዲያስረክቡ ቀነ ገደብ ተሰጣቸው  

በአማኑኤል ይልቃል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ ኮንዶሚኒየም ደርሷቸው “በቀበሌ ቤቶች” ውስጥ የሚኖሩ የከተማዋ ነዋሪዎች እስከ ሰኔ 30 ድረስ የተከራዩዋቸውን ቤቶች እንዲያስረክቡ ቀነ ገደብ አስቀመጠ። የከተማ አስተዳደሩ የሚረከባቸውን እነዚህን የቀበሌ ቤቶች “የደሃ ደሃ” ተብለው ለተለዩ ነዋሪዎች ለማከፋፈል እቅድ መያዙን አስታውቋል። 

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የግንባታ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቶማስ ደበሌ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት፤ የቀበሌ ቤቶቻቸውን አስረክበው ወደ ኮንዶሚኒየም ቤት እንዲገቡ ደብዳቤ የተሰጣቸው የከተማይቱ ነዋሪዎች፤ በየካቲት 2011 ዓ.ም እና በዘንድሮ ዓመት ህዳር ወር ላይ ዕጣ የወጣላቸው ዕድለኞች ናቸው። በቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ የሚመራው አስተዳደር፤ በየካቲት 2011 ዓ.ም. ዕጣ ያወጣባቸው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ብዛት 51,200 ገደማ ነበር። 

በወቅቱ ለነዋሪዎች ሊተላለፉ በዝግጅት ላይ እያሉ በተነሳባቸው ተቃውሞ ምክንያት ከባለ እድለኞች ጋር ርክክብ ሳይፈጸምባቸው የዘገዩት እነዚህ የኮንዶሚኒየም ቤቶች፤ የቁልፍ ርክክብ የተፈጸመባቸው ግን ባለፈው ዓመት ነው። የከተማ አስተዳደሩ በዚህ ዓመት ህዳር ወር በ25,791 ቤቶች ላይ ዕጣ ያወጣ ሲሆን፤ ከዕድለኞች ጋር ውል የመዋዋል ስራው የተከናወነው ደግሞ ካለፈው ጥር እስከ ግንቦት ወር ባሉት  አምስት ወራት ውስጥ ነበር። 

በከተማ አስተዳደሩ የሚገነቡ የኮንዶሚኒየም ቤቶችን የመከታተል ኃላፊነት ያለበት የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን፤ የኮንዶሚኒየም ዕጣ ወጥቶባቸው ነገር ግን እስካሁን ድረስ ያላለቁ 139 ሺህ ቤቶች ላይ የማጠናቀቂያ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ የግንባታ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ኮርፖሬሽኑ በ32 የግንባታ ሳይቶች ላይ የሚገኙትን እነዚህ ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ፤ ባለፉት አራት ወራት ሲሰራ መቆየቱን አስረድተዋል። 

“ካሉን 32 ሳይቶች ውስጥ almost 90 በመቶ አካባቢ ጨርሰን እየወጣን ነው” ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ የኮንዶሚኒየም ዕጣ የደረሳቸው ባለእድለኞች እስከ ሰኔ 30 ድረስ ወደ መኖሪያ ቤቶቹ እንዲገቡ መታቀዱን ተናግረዋል። ከእነዚህ ባለእድለኞች መካከል የተወሰኑት “የቀበሌ ቤቶች” ተብለው በሚታወቁት የመንግስት ቤቶች ውስጥ፤ ዕጣ ከወጣላቸው በኋላ “ለረጅም ጊዜ” የቆዩ መሆናቸውን አክለዋል። 

በኮንዶሚኒየም ባለእድለኞች በዚህ አይነት መልኩ የተያዙ አምስት ሺህ ገደማ ቤቶች መኖራቸውንም የጠቀሱት አቶ ቶማስ፤ እነዚህን ቤቶቹ የማስረከቢያ ቀነ ገደብ እስከ ሰኔ 30 መሆኑን ለግለሰቦቹ እንደተገለጸላቸው አስታውቀዋል። “ክፍለ ከተማ፣ በወረዳ ያለው መዋቅር፣ ለእያንዳንዱ በመንግስት ቤት ውስጥ ለሚኖር ማህበረሰብ በደብዳቤ እንዲያውቅ ጭምር ተደርጓል። ይህ ማለት ‘እስከ ሰኔ 30 ድረስ ስለምንፈልገው ቤታችሁ እንድትገቡ፤ በዚህ ጊዜ ቤቱን እንድታስረክቡ’ የሚል ጭምር እንዲያውቁት ተደርጓል” ሲሉ ለኮንዶሚኒየም ባለእድለኞች የተደረገውን ገለጻ አብራርተዋል።

 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ”ቀበሌ ቤቶችን” ወደማስለቀቅ እርምጃ የገባው “በከተማ ደረጃ በርካታ የቤት ፍላጎት” በመኖሩ መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። “እጅግ በጣም የተቸገሩ ግለሰቦች አሉ። ተመዝግቦ በየክፍለ ከተማው እና ወረዳው ከ500 እስከ አንድ ሺህ ያላነሰ ሰው የደሃ ደሃ ተብሎ ተለይቶ ቤት የሚጠብቅ አለ” ያሉት አቶ ቶማስ፤ ኮንዶሚኒየም በደረሳቸው ሰዎች ተይዘው የነበሩት ቤቶች ለእነዚህ ነዋሪዎች እንደሚተላለፉ ገልጸዋል። 

አብዛኛዎቹ ኮንዶሚኒየም ባለእድለኞች በዕጣ ወደ ደረሳቸው ቤቶች ያልገቡት እንደ ውሃ እና መብራት ያሉ መሰረተ ልማቶች “አልተሟሉም” በሚል ምክንያት መሆኑን የግንባታ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል። አሁን ባለው ሁኔታ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ “ነዋሪዎች እንዲገቡ የሚያስችሉ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ተከናውኖላቸዋል” ሲሉም የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በዚህ ረገድ የሚጠበቅበትን ማሟላቱን አስረድተዋል።

ሁሉም ቤቶች ላይ በአንድ ጊዜ በስታንዳርዱ ልክ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ማከናወን እንደማይቻል የሚያነሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለዚህም ሲባል እንደ ኤሌክትሪክ ኃይል እና ውሃ ባሉት አቅርቦቶች ላይ ጊዜያዊ መፍትሄዎች በአማራጭነት መተግበራቸውን ገልጸዋል። “ለኮንስትራክሽን የገቡ የኤሌክትሪክ መስመሮች ላይ ተጨማሪ top up አድርጎ መብራት ኃይል እንዲሰጥ” መደረጉን ለዚህ በማሳያነት አንስተዋል።   

እነዚህን አቅርቦቶች “በዘላቂነት እና በስታንዳርዱ መሰረት”  የማጠናቀቅ ስራ፤ ነዋሪዎች ወደ ቤቶቹ ከገቡ በኋላ “ጎን ለጎን” ለማከናውን መታቀዱን አቶ ቶማስ ጠቅሰዋል። “ከ130 ሺህ በላይ ቤቶችን አጠናቅቀን፤ በዚህ አካሄድ ሰዉን ‘ወደ ቤት ግቡ እያልን ነው’ ያለነው” ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከቀበሌ ቤት ነዋሪዎችም በተጨማሪ ሌሎችም የቤት ባለቤቶች በዚህ ወር መጨረሻ ወደ መኖሪያ መንደሮቹ እንዲገቡ ለማድረግ መታሰቡን አንስተዋል። ከእነዚህ ውስጥ “በምደባ በልዩ ሁኔታ” የኮንዶሚኒየም ቤት ተላልፎላቸው እስካሁን ያልገቡ እንደሚገኙበትም አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)