ዐቃቤ ህግ በ51 ግለሰቦች ላይ የመሰረተው የሽብር ወንጀል ክስ ዝርዝር እና የተከሳሾች የፍርድ ቤት ውሎ

በሃሚድ አወል

አምስት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የተካተቱበት እና በእነ ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ መዝገብ በፌደራል ዐቃቤ ህግ የተከፈተው የክስ ቻርጅ፤ በትላንትናው ዕለት ለተወሰኑ ተከሳሾች እንዲደርሳቸው ተደረገ። በፍትህ ሚኒስቴር የዐቃቤ ህግ ዘርፍ በ51 ግለሰቦች ላይ የሽብር ወንጀል ክስ የመሰረተው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ሰኔ 1፤ 2015 ነበር።

ክሱ የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሶስተኛ የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት፤ ክሱ በሬጅስትራር ተረጋግጦ ለተከሳሾች እንዲደርሳቸው ለትላንት ሰኞ ሰኔ 5፤ 2015 ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር። ሆኖም ግን ጉዳያቸውን በችሎት ተገኝተው ከተከታተሉ 23 ተከሳሾች መካከል ክሱ የደረሳቸው 13ቱ ብቻ ናቸው። 

የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎቱ፤ የፍርድ ቤቱን የሬጅስትራር ባለሙያ ጠርቶ የዐቃቤ ህግ ክስ ተረጋግጦ ለተከሳሾች ያልደረሰበትን ምክንያት ጠይቋል። ለችሎቱ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ባለሙያዋ፤ ለክሱ ተረጋግጦ አለመቅረብ የማስረጃዎችን “ብዛት” በምክንያትነት አንስተዋል። ከዚህ በተጨማሪም “በዐቃቤ ህግ በኩል ተሟልቶ የቀረበ ክስ እንዳልነበር” አስረድተዋል። 

ተከሳሾችን ወክለው ፍርድ ቤት ከቀረቡ 10 ጠበቆች መካከል አንዱ የሆኑት ጠበቃ ቤተማርያም አለማየሁ፤ “የተከሳሾችን መብት በተመለከተ የምናነሳው ጥያቄ ስላለ፤ የተረጋገጠው ክስ ይድረሰን እና ዝግጅት እናድርግ” ሲሉ ጠይቀዋል። በጠበቃው ጥያቄ መሰረት በ71 ገጾች የተዘጋጀው የዐቃቤ ህግ የክስ ቻርጅ፣ የተለያየ ገጽ ያላቸው 67 የሰነድ ማስረጃዎች እንዲሁም “የተለያዩ ማስረጃዎችን የያዘ” 32 “ጌጋ ባይት ፍላሽ” ለአስራ ሶስቱ ተከሳሾች ደርሷቸዋል። 

ለቀሪዎቹ ተከሳሾች ክሱ በሚቀጥለው ቀጠሮ ተረጋግጦ እንዲደርሳቸው ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ቢሰጥም፤ የተከሳሽ ጠበቆች ከአፍታ ቆይታ በኋላ ይህንን ውሳኔ እንዲቀለበስ ያደረገ መከራከሪያ አቅርበዋል። ተከሳሾችን ወክለው ችሎት የተገኙት ሌላኛው ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ፤ “ክሱ በፍርድ ቤት ሬጅስትራር አልተረጋገጠም። ከዐቃቤ ህግ ማህተም ውጭ ምንም የለውም። ኮፒ ተደርጎ ነው የደረሰን” ሲሉ ለተከሳሾች የተሰጠው ክስ የፍርድ ቤቱ ሬጅስትራር ማህተም ሊያርፍበት ይገባ እንደነበር አስገንዝበዋል። 

ሌላኛው ጠበቃ አቶ ቤተማርያም በበኩላቸው “ክሱ ላይ የዐቃቤ ህግ ስም እና ፊርማ” እንደሌለው ጠቅሰው፤ “የከሰሰው አካል በትክክል ማን እንደሆነ ማወቅ አለብን” ሲሉ ተከራክረዋል። ዐቃቤ ህግ ለዚህ መከራከሪያ በሰጠው ምላሽ “ግለሰብ ሳይሆን ተቋም ነው የከሰሰው። [ክሱ] የተቋሙ የራስጌ አርማ እና ክብ ማህተም አለው” ብሏል። “ስም ለመጻፍ የሚያስገድድ ህግ የለም” ሲል ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጠው ዐቃቤ ህግ፤ “የስም አለመኖር በክሱ ሂደት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ የለም። በቀረበበት አግባብ ክሱ ይቀጥል” ሲል የጠበቃው መከራከሪያ ተቀባይነት እንዳያገኝ ጠይቋል።

በክስ አቀራረቡ ላይ የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት፤ የጠበቆች መከራከሪያ “የክስ መቃወሚያ ሆኖ ነው መቅረብ ያለበት ወይስ በማንኛውም ጊዜ መቅረብ ይችላል የሚለውን ማየት ያስፈልጋል” ብሏል። ይህን ተከትሎም ቀደም ሲል “ለቀሪ ተከሳሾች ክሱ ተረጋግጦ ይቅረብ” በሚል የሰጠው ትዕዛዝ በይደር እንዲቆይ ወስኗል። ፍርድ ቤቱ ይህን ውሳኔ ያስተላለፈው፤ “ችሎቱ በጉዳዩ ላይ የተለየ አቋም ሊይዝ ስለሚችል” በሚል ምክንያት ነው። 

በ71 ገጾች የተዘጋጀው ክስ ምን ይዟል?

የፌደራል ዐቃቤ ህግ በትላንትናው የችሎት ውሎ ለ13 ተከሳሾች እንዲደርስ ያደረገው ክስ፤ አምስት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን ጨምሮ 51 ግለሰቦች የተካተቱበት ነው። ተከሳሾቹ የወንጀል ህግ እንዲሁም የሽብር ወንጀልን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል የወጣው አዋጅ ላይ ያሉ ድንጋጌዎችን ተላልፈዋል በሚል ነው ክስ የቀረበባቸው። ሃምሳ አንዱም ተከሳሾች “በዋና ወንጀል አድራጊነት፣ የወንጀሉ ድርጊት በሚሰጠው ውጤት ሙሉ ተካፋይ በመሆን እና ውጤቱን የራሳቸው በማድረግ፣ ወንጀሉን በቀጥታ በመፈጸም እና ወንጀል ለመፈጸም ቀድመው ስምምነት በማድረግ በህብረት እና በማደም በፈጸሙት ሽብር ወንጀል” መከሰሳቸውን ዐቃቤ ህግ በክስ ሰነዱ ላይ አስፍሯል። 

ተከሳሾቹ “ ‘መነሻችን አማራ መድረሻችን ኢትዮጵያ’ በሚል የፖለቲካ እና የርዕዮት አላማቸውን ለማራማድ በማሰብ”፤ “የሽብር ድርጊት ፈጽመዋል” ሲል ዐቃቤ ህግ ወንጅሏል። ተከሳሾቹ “ፈጽመውታል” በተባለው የሽብር ድርጊት፤ “ከ217 በላይ ሰው እንዲሞት፣ በ297 ሰው ላይ የአካል ጉዳት እንዲደርስ” አድርገዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል። ከህይወት መጥፋት እና ከአካል ጉዳት በተጨማሪም፤ 1.298 ቢሊዮን ብር የሚገመት የንብረት ውድመት መድረሱን ዐቃቤ ህግ በክሱ አስፍሯል።

ይህ ጉዳት የደረሰው፤ ተከሳሾች “የፖለቲካ እና የርዕዮት አላማቸውን ለማራመድ በማሰብ፣ ህዝብን ለማሸበር እና መንግስትን አስገድዶ ከስልጣን ለማውረድ በማሰብ በፈጸሙት የሽብር ድርጊት” መሆኑን ዐቃቤ ህግ በክሱ ላይ ገልጿል። ተከሳሾቹ “ሀገሪቷን እያስተዳደረ ያለውን መንግስት በተለያየ ወታደራዊ ስልት እና ስትራቴጂ በመውጋት፤ የአማራን ህዝብ ክብር እና ኩራት በወታደራዊ ኃይል ለመመለስ” መንቀሳቀሳቸውም በክሱ ላይ ተጠቅሷል። 

ተከሳሾቹ “ፈጽመውታል” በተባለው የሽብር ድርጊት፤ “ከ217 በላይ ሰው እንዲሞት፣ በ297 ሰው ላይ የአካል ጉዳት እንዲደርስ” አድርገዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል። ከህይወት መጥፋት እና ከአካል ጉዳት በተጨማሪም፤ 1.298 ቢሊዮን ብር የሚገመት የንብረት ውድመት መድረሱን ዐቃቤ ህግ በክሱ አስፍሯል።

የዐቃቤ ህግ የክስ ሰነድ ተከሳሾቹ የተወነጀሉባቸውን ድርጊቶች የፈጸሙት “በጋራ እና በአንድነት በመሆን፣ በህቡዕ ቡድን በማደራጀት፥ አንደኛው የሌላኛውን ተከሳሽ ድርጊት በመቀበል እና በሚያስከትለው ውጤት በመስማማት” መሆኑን አትቷል። ሃምሳ አንዱ ተከሳሾች፤ “ፖለቲካዊ እና ርዕዮት ዓለማዊ ግባቸውን በኃይል እርምጃ ለመጫንና ከፍጻሜ ለማድረስ እንዲሁም መንግስት እና ህዝብን ለማስገደድ በማሰብ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን በማስገደል፣ በተለያዩ አካባቢዎች አመጽ እንዲነሳ እና ሰዎች እንዲገደሉ በማድረግ” መወንጀላቸውም በክስ ሰነዱ ላይ ተቀምጧል።

ተከሳሾቹ “የመንግስትን ኃይል በማያዳግም መልኩ በመደምሰስ፣ የክልሉን ገዢ ፓርቲ በማስወገድ፣ የሀገሪቷን ማዕከላዊ ስልጣን ለመቆጣጠር” ተንቀሳቅሰዋል የሚል የወንጀል ጭብጥም ቀርቦባቸዋል። የፌደራል ዐቃቤ ህግ በተከሳሾች ላይ በጅምላ ካቀረበው ይህን መሰል የወንጀል ጭብጥ በተጨማሪ፤ እያንዳንዳቸው ተከሳሾች “ተፈጽሟል” ከተባለው “የሽብር ወንጀል” ጋር ያላቸውን ግንኙነት በዝርዝር አብራርቷል።

በአንደኛ ተከሳሽነት የቀረቡት የህክምና ባለሙያው ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ፤ “የህቡዕ አደረጃጀቶች እንዲፈጠር ያደረጉ እና በእነዚህ አደረጃጀቶች ማዕከላዊ አስተባባሪ በመሆን የመሩ፣ ያቀናጁ እና አቅጣጫ ሲሰጡ የነበሩ መሆኑ” በዐቃቤ ህግ ክስ ላይ ተጠቅሷል። በዚሁ ክስ ላይ  በሁለተኛነት የተጠቀሰችው “ኢትዮ ንቃት” የተሰኘው የዩቲዩብ መገናኛ ብዙሃን መስራች መስከረም አበራ ነች። 

መስከረም “ህቡዕ ዓላማ” አለው የተባለውን “የአማራ ፋኖ አንድነት” ምክር ቤትን በመመስረት፣ እንዲደራጅ በማድረግ እንዲሁም “ራሷን የምክር ቤቱ ምክትል አስተባባሪ አድርጋ ሰይማለች” ተብላ ተወንጅላለች። የራሷን ጨምሮ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በምታቀርባቸው የፖለቲካ ትንታኔዎቿ የምትታወቀው መስከረም፤ “የአማራ ፋኖ አንድነት” ምክር ቤት የተባለው አደረጃጀት “የፕሮፓጋንዳ ቡድን መሪ” መሆኗን ዐቃቤ ህግ በክስ ሰነዱ ላይ በተደጋጋሚ አስፍሯል።

ከመስከረም አበራ በተጨማሪ ሌሎች አራት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችም፤ ፈጽመዋቸዋል የተባሉ “የሽብር ድርጊቶች” በዐቃቤ ህግ የክስ ሰነድ ላይ በዝርዝር ቀርቧል። “አራት ኪሎ ሚዲያ” የተሰኘው የዮቲዩብ መገናኛ ብዙሃን መስራች በሆነው ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው ላይ ዐቃቤ ህግ ካቀረበው የወንጀል ዝርዝር ውስጥ “የህቡዕ አደረጃጀት በማዋቀር እና በመምራት ሲንቀሳቀስ ነበር” የሚለው ይገኝበታል። ጋዜጠኛ ዳዊት “መንግስትን በኃይል ከስልጣን ለማስወገድ በማሰብ፣ የምሁራን ክንፍ አባል በመሆን፣ የአደረጃጀት ሰነዶችን ሲያዘጋጅ” እንደነበር ዐቃቤ ህግ ወንጅሏል። 

ከዳዊት ጋር የተመሳሰለ ውንጀላ በዐቃቤ ህግ የቀረበባት ሌላኛዋ ጋዜጠኛ ገነት አስማማው ናት። ገነት “የፕሮፓጋንዳ እና ሚዲያ ቡድን አባል በመሆን” በደብረብርሃን ከተማ ለሁለት ቀናት ስልጠና መውሰዷን ዐቃቤ ህግ በማስረጃነት ጠቅሷል። ጋዜጠኛዋ በአንደኛ ተከሳሽ ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ የተጻፈ ነው የተባለ፤ “የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት እና አመራሮች እንዲኮበልሉ የሚጠይቅ ደብዳቤ አሰራጭታለች” የሚል ክስም በዐቃቤ ህግ ቀርቦባታል። 

ከጋዜጠኛ ዳዊት እና ገነት ጋር ተመሳሳይ አይነት ውንጀላ የቀረበባቸው ቀሪዎቹ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ እና በሌለበት የተከሰሰው ሙሉጌታ አንበርብር ናቸው። ሁለቱ ጋዜጠኞች የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ከአንድ ወር ከአስራ አምስት ቀን በፊት “ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለማፍረስ እና በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው የሚፈለጉ” በሚል ስማቸውን ይፋ ካደረጋቸው ግለሰቦች ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ ነበሩ። 

በዚሁ ዝርዝር ስማቸው የተጠቀሰው አንጋፋው ፖለቲከኛ ልደቱ አያሌው ዐቃቤ ህግ ባለፈው ሳምንት በመሰረተው ክስ ሳይካተቱ ቀርተዋል። እንደ እርሳቸው ሁሉ በጋራ ግብረ ኃይሉ ዝርዝር ውስጥ በተፈላጊነት ተጠቅሰው የነበሩት፤ “ኢትዮ 360” በተሰኘው የዩ ቲዩብ መገናኛ ብዙሃን የሚሰሩት ሀብታሙ አያሌው፣ ምናላቸው ስማቸው፣ ብሩክ ይባስ እና ኢየሩሳሌም ተክለጻዲቅ እንዲሁም “አንከር” የተሰኘው የዩ ቲዩብ መገናኛ ብዙሃን መስራች መሳይ መኮንን ከዐቃቤ ህግ ክስ ውጭ ሆነዋል።

የፌደራል ዐቃቤ ህግ ክስ በክስ ሰነዱ ላይ ከዘረዘራቸው 51 ግለሰቦች መካከል ሃያ ሰባቱ ክስ የተመሰረተባቸው በሌሉበት ነው። በፌደራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር ሆነው በትላንትናው የፍርድ ቤት ውሎ በአካል ችሎት ፊት የቀረቡት 23 ተከሳሾች ናቸው። ከእነዚህ ተከሳሾች ቤተሰቦች መካከል የትላንትናውን የችሎት ውሎ መታደም የቻሉት በጣት የሚቆጠሩት ብቻ ናቸው። የችሎት ማስቻያ አዳራሹ ጠባብ በመሆኑ ምክንያት በርካታ ሰው የችሎቱን ሂደት መታደም አለመቻሉን በተመለከተ፤ ተከሳሾች እና ጠበቆች ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርበዋል።  

በዐቃቤ ህግ የክስ ሰነድ በአምስተኛ ተራ ቁጥር የተቀመጡት የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ መምህር ሲሳይ አውግቼው፤ “ቤተሰቦቻችን ክሳችንን እንዲሰሙ፣ ሰፋ ባለ አዳራሽ ክሳችን እንዲደመጥ እንጠይቃለን” ሲሉ ለችሎት አቤት ብለዋል። ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይም በተመሳሳይ ይህንኑ ጥያቄ አስተጋብቷል። ከተከሳሽ ጠበቆች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ሰለሞን ገዛኸኝም፤ የፍርድ ሂደቱ ሰፋ ባለ አዳራሽ እንዲደረግ በተጨማሪነት ጥያቄ አቅርበዋል።

በትላንቱ የችሎት ውሎ የቀረበው ሌላው አቤቱታ፤ ተከሳሾች “ደረሰብን” ካሉት “የሰብዓዊ መብት ጥሰት” ጋር የተያያዘ ነው። ሌሎችን ተከሳሾች በመወከል አቤቱታ ያቀረቡት አራተኛ ተከሳሽ ዶ/ር መሰረት ቀለመወርቅ፤ ተከሳሾቹ ጉዳያቸው በጊዜ ቀጠሮ ችሎት ሲታይ በነበረበት ወቅት የሰብዓዊ መብት አያያዝን በተመለከተ አቤቱታ አቅርበው እንደነበር አስታውሰዋል። ለዚህ አቤቱታ በጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ትዕዛዝ ቢሰጥበትም፤ ተከሳሾቹ የደረሰበትን ደረጃ እንደማያውቁ ለችሎቱ አስረድተዋል። 

በ47ኛ ተከሳሽነት የቀረቡት አቶ ማስረሻ እንየው በበኩላቸው፤ ህክምና ማግኘት እንዳልቻሉ ለችሎቱ አቤቱታ አቅርበዋል። የተከሳሾቹን አቤቱታ ያዳመጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሶስተኛ የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት የተለያዩ ትዕዛዞችን አስተላልፏል። በዚህ መሰረት የህክምና የማግኘት ጥያቄ ላቀረቡት አቶ ማስረሻ ጥያቄቸውን ተፈጻሚ እንዲሆን ችሎቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል። የችሎት ሂደቱን ብዙ ታዳሚዎች እንዲከታተሉት እንዲደረግ ተከሳሾች ላቀረቡት ጥያቄም፤ ፍርድ ቤቱ “በቀጣይ ሰፊ ችሎት አዳራሽ ላይ አመቻችተን እናስችላለን” የሚል ምላሽ ሰጥቷል። 

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለሁለት ሰዓታት ገደማ የፈጀውን የትላንቱን የችሎት ውሎ ከማጠናቀቁ በፊት ከዐቃቤ ህግ ክስ ጋር በተያያዘ ለቀረበው ክርክር እና በተከሳሾች የቀረቡ አቤቱታዎች ላይ መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። በዚህም መሰረት ተከሳሾች በመጪው አርብ ሰኔ 9፤ 2015 ረፋድ ላይ በችሎት እንዲገኙ አዝዟል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)