በአማኑኤል ይልቃል
በደቡብ ክልል የወላይታ ዞን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) አስተባባሪ የሆኑት አቶ እስራኤል ካሳ ከዞኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጋር “በተያያዘ ውዝግብ” በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ። ኢዜማ፤ የፓርቲው የወላይታ ዞን አስተባባሪ እንዲፈቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።
በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን የኢዜማ አስተባባሪ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት፤ ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ሰኔ 7፤ 2015 መሆኑን የፓርቲው የህግ እና የአባላት ደህንነት ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ አቶ ስዩም መንገሻ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። አቶ እስራኤል በፖሊስ በቁጥጥር ሲያዙ የተጠረጠሩበት ምክንያት እንዳልተገለጸላቸውም የፓርቲው የመምሪያ ኃላፊ አስረድተዋል።
የወላይታ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በበኩሉ፤ የኢዜማ አስተባባሪው በፖሊስ የተያዙት ቀድሞ በኃላፊነት ሲመሩት ከነበረው ከዚሁ ምክር ቤት ጋር በተያያዘ ነው ብሏል። ከህዳር ወር ጀምሮ በወላይታ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ የነበሩት አቶ እስራኤል፤ በሚያዝያ ወር ውስጥ “አዲስ አመራሮች በመመረጣቸው” ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን የምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ አብርሃም ጦና ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
ይሁንና አቶ እስራኤል በኃላፊነት ላይ በነበሩበት ጊዜ በእጃቸው ላይ የነበሩትን ማህተሞች እስካሁን ድረስ ለአዲሶቹ የምክር ቤቱ አመራሮች “አለማስረከባቸውን” ምክትል ሰብሳቢው አስረድተዋል። የኢዜማ አስተባባሪው “ማህተሞቹን ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑት” ፤ አዲሶቹ የምክር ቤቱ አመራሮች “በህጋዊ መንገድ ያልተመረጡ ናቸው” በሚል እንደሆነም አክለዋል።
የወላይታ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ማህተሞቹን ለመቀበል በተለያዩ ጊዜያት “ደብዳቤ መጻፉን” እና “ሽማግሌዎች መላኩን” የሚናገሩት ምክትል ሰብሳቢው፤ እነዚህ ሙከራዎች አለመሳካታቸውን አመልክተዋል። ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት “በህግ አግባብ” ለመጠየቅ ከተወሰነ በኋላ፤ ንብረቱን እንዲመለስ የጋራ ምክር ቤቱ ባለፈው ሳምንት አርብ ዕለት ለወላይታ ዞን ፖሊስ መምሪያ ደብዳቤ መጻፉን አስታውሰዋል።
የኢዜማ የህግ እና የአባላት ደህንነት ጉዳይ መመሪያ ኃላፊ አቶ ስዩም ግን የወላይታ ዞን አስተባባሪውን ለእስር የዳረጋቸው ጉዳይ ይህ ቢሆን እንኳ አካሄዱ “ሂደቱን የጠበቀ አይደለም” ባይ ናቸው። አቶ እስራኤልን ከጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢነታቸው “ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ ከኃላፊነት ለማንሳት ሙከራዎች ተደርገዋል” የሚሉት የመምሪያ ኃላፊው፤ ይህን ጉዳይ የ“ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ” እና የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እንደሚያውቁት እና “በሂደት ላይ መሆኑን” ገልጸዋል።
ኢዜማ በወላይታ ዞን ካሉ ሌሎች ስራ አስፈጻሚዎች ባገኘው መረጃ አቶ እስራኤል ከጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢነት እንዲነሱ የተደረገው፤ ሰብሳቢ በነበሩበት ጊዜ በዞኑ የሚካሄደውን “ህዝበ ውሳኔ አካሄድ በመቃወም” መግለጫ በመስጠታቸው እንደሆነ መረዳቱን አቶ ስዩም አብራርተዋል። በወቅቱ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ የነበሩት አቶ እስራኤል ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ጋር በመሆን ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን ለመመስረት ጥር 29፤ 2015 ከተደረገው ህዝበ ውሳኔ አንድ ሳምንት ገደማ አስቀድሞ ነበር።
በአዲስ አበባ ከተማ በተሰጠው በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፤ ህዝበ ውሳኔው “የዜጎችን የመምረጥ መብት የነፈገ የምርጫ ሂደት” እንደሆነ በመግለጽ የወላይታ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ ተቃውሞ አሰምቶ ነበር። ምክር ቤቱ “ህዝቡ ለመምረጥ የሚፈልገው አማራጭ” በህዝበ ውሳኔ ውስጥ እንዳልቀረበመ በወቅቱ ገልጾ ነበር። ኢዜማ አሁን በእስር ላይ የሚገኙት አቶ እስራኤል በዚህ መግለጫ ምክንያት “ቂም ተይዞባቸው” ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጋቸውን የሚገልጽ መረጃ እንደደረሰው ቢገልጽም፤ የሌሎች የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ግን ከዚህ የተለየ ምክንያት ያቀርባሉ።
የወላይታ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ አብርሃም፤ አዲስ አመራር የተመረጠው አቶ እስራኤል በሰብሳቢነት የተመረጡበት የምርጫ ሂደት የምክር ቤቱን “ህግ እና የቃል ኪዳን ሰነድ ያልጠበቀ ስለነበር ነው” ባይ ናቸው። በወቅቱ የአመራር ምርጫ ሲደረግ፤ የጋራ ምክር ቤቱ አባል የሆኑ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ባልተገኙበት እና “ምልአተ ጉባኤ” ባልተሟላበት እንደነበር አስረድተዋል።
የደቡብ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ጎበዜ ጎአም በተመሳሳይ ለወላይታ ዞን የጋራ ምክር ቤት አዲስ አመራር የተመረጠው፤ ሂደቱን የሚቃወሙ ፓርቲዎች “ፒቲሽን” ፈርመው ጥያቄ ካቀረቡ በኋላ መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል፡፡ ይህ አይነቱ ጥያቄ ሲመጣ ጠቅላላ ጉባኤ ተጠርቶ አዲስ አመራር የሚመረጥበት አሰራር እንዳለ ያነሱት አቶ ጎበዜ፤ እርሳቸው የሚመሩት ምክር ቤትም በዚህ ምርጫ ላይ በታዛቢነት መገኘቱን አስታውሰዋል፡፡
ይሁንና ከዚህ ምርጫ በኋላ “ማህተሞች አልተመለሱም” የሚል ቅሬታ ወደ ደቡብ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አለመምጣቱን እና አቶ እስራኤል በምን ምክንያት በቁጥጥር ስር እንደዋሉ እንደማያውቁ አክለዋል። የወላይታ ዞን አስተባባሪው የታሰሩበት ኢዜማ በበኩሉ አቶ እስራኤል እስከ ዛሬ አርብ ሰኔ 9፤ 2015 ረፋድ ድረስ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን አስታውቋል። ኢዜማ የወላይታ ዞን አስተባባሪውን እስር አስመልክቶ፤ ለምርጫ ቦርድ እና ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በትላትናው ዕለት ደብዳቤ መጻፉን የህግ እና የአባላት ደህንነት ጉዳይ መመሪያ ኃላፊው አቶ ስዩም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ የኢዜማ የወላይታ ዞን አስተባባሪ ከእስር ይፈቱ ዘንድ ቦርዱ “እርምጃ እንዲወስድ” የሚጠይቅ ደብዳቤ እንደደረሰው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጧል። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትም፤ የአቶ እስራኤልን እስርን በተመለከተ ከኢዜማ “ቅሬታ” እንደቀረበለት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቋል። የኢዜማ የወላይታ ዞን አስተባባሪ እስርን በተመለከተ ከወላይት ዞን አስተዳደርም እንዲሁም ከዞኑ ፖሊስ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[ማረሚያ፦ በዚህ ዘገባ ላይ ቀደም ሲል የተጠቀምነው የአቶ እስራኤል ካሳ ፎቶ በስህተት የገባ እና አሁን የተስተካከለ መሆኑን እንገልጻለን። ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ እንጠይቃለን።]