በአማኑኤል ይልቃል
በትግራይ ክልል በትምህርት ገበታቸው ይገኛሉ ተብሎ ከሚጠበቁ ተማሪዎች ውስጥ፤ እስካሁን ወደ ትምህርት ቤት የተመለሱት 23.3 በመቶው ብቻ መሆናቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ። በክልሉ ካሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ግማሽ ገደማ የሚሆኑት፤ “በአማራ ታጣቂዎች እና በኤርትራ ሰራዊት” በተያዙ አካባቢዎች የሚገኙ በመሆናቸው እና ተፈናቃዮችን በማስጠለላቸው እስካሁን ትምህርት አለመጀመራቸውን ቢሮው ገልጿል።
የኮሮና ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ በ2012 ዓ.ም ስራ ያቋረጡት በትግራይ ክልል የሚገኙ ትምህርት ቤቶች፤ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት መነሳት ሳቢያ በተሟላ ሁኔታ ትምህርት ሳይጀምሩ ለሶስት ዓመታት ገደማ እንደተዘጉ ቀጥለዋል። የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ እነዚህ ትምህርት ቤቶች በድጋሚ ተከፍተው መደበኛ ትምህርት እንዲጀምሩ ያደረገው ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይ ነበር።
በትግራይ ክልል ከተጀመረ 50 ገደማ ቀናት ባሳለፈው የመማር ማስተማር ሂደት፤ ትምህርት ቤቶቹ ከመደበኛው የትምህርት አሰጣጥ በተለየ መልኩ የተፋጠነ የትምህርት ስርዓትን (accelerated learning program) እንዲከተሉ መደረጉን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ኪሮስ ጉዕሽ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ይህ አሰራር ተማሪዎች በአንድ ዓመት ሁለት የክፍል ደረጃዎችን እንዲያጠናቅቁ የሚያደርግ መሆኑንም አስረድተዋል።
በተፋጠነ የትምህርት ስርዓት አካሄድ መሰረት፤ በአሁኑ ወቅት የትምህርት አሰጣጡ የአንድ ሴሚስተር አጋማሽ ላይ መድረሱን መሆኑን ዶ/ር ኪሮስ ገልጸዋል። የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ በዚህ አይነት መልኩ ትምህርት ሲያስጀምር 2.4 ሚሊዮን ተማሪዎች ወደ ትምህርት እንዲመለሱ ይጠብቅ እንደነበር የጠቆሙት የክልሉ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ፤ ይሁንና በአሁኑ ወቅት ወደ ትምህርት የተመለሱ ተማሪዎች ብዛት 564 ሺህ ገደማ ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል።
በትግራይ ክልል ከሚገኙት 2,492 ትምህርት ቤቶች ውስጥ በአሁኑ ወቅት ትምህርት እየሰጡ ያሉት 55.2 በመቶዎቹ ብቻ መሆናቸው፤ ወደ ትምህርት ገበታ ይመለሳሉ ተብለው ለተገመቱ ተማሪዎች መቀነስ አንድ ምክንያት መሆኑን ዶ/ር ኪሮስ አመልክተዋል። በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ስራ መግባት ካልቻሉት በክልሉ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ፤ 552ቱ ክልሉን በመምራት ላይ ባለው ጊዜያዊ አስተዳደር ስር አለመሆናቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ከእነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ አብዛኛዎቹ በምዕራብ፣ ደቡብ እና ሰሜን ምዕራብ ትግራይ አካባቢዎች እንደሚገኙ የሚገልጹት ዶ/ር ኪሮስ፤ እነዚህ አካባቢዎች ደግሞ “በአማራ ታጣቂዎች የተያዙ ናቸው” ይላሉ። በማዕከላዊ እና ምስራቃዊ ትግራይ ዞኖች እና በታህታይ አዴቦ አካባቢ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ደግሞ “በኤርትራ ሰራዊት” ቁጥጥር ስር የሚገኙ መሆናቸውንም ይናገራሉ።
“እነዚህ 552 ትምህርት ቤቶች በታጣቂዎች፣ በአማራ እና በኤርትራ ሰራዊት ስለተያዙ፤ እዚያ ይማሩ የነበሩ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ወደ ትምህርት አልገቡም” ሲሉ በአካባቢዎቹ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ትምህርት ለማስጀመር አለማስቻሉን ዶ/ር ኪሮስ አስረድተዋል። በአማራ ታጣቂዎች እና በኤርትራ ሰራዊት ከተያዙ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ነዋሪዎች፤ “በተወሰኑ” ትምህርት ቤቶች ውስጥ መጠለላቸው ሌላኛው ችግር መሆኑንም የትምህርት ቢሮ ኃላፊው አንስተዋል።
እስካሁንም በተፈናቃዮች የተያዙ ትምህርት ቤቶች በሽራሮ፣ ሽረ፣ አክሱም፣ አድዋ፣ አቢ አዲ፣ ማይጨው፣ አዲግራት እና መቐለ ከተሞች እንደሚገኙ ኃላፊው ተናግረዋል። የክልሉ ትምህርት ቢሮ በተለያዩ የተፈናቃይ መጠለያዎች ውስጥ የሚገኙ ልጆች በአቅራቢያቸው ወደሚገኙ ትምህርት ቤቶች እንዲገቡ ለማድረግ ጥረት እያደረገ መሆኑን ኃላፊው አመልክተዋል። በዚህ እንቅስቃሴ “የተወሰኑ ተማሪዎች” ትምህርት መጀመራቸውን የገለጹት ዶ/ር ኪሮስ፤ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በመጠለያዎቹ የሚቀርበው እርዳታ ከመቋረጡ ጋር በተያያዘ ተማሪዎቹን ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ አስቸጋሪ ሁኔታ መፈጠሩን አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ድንበር አካባቢ በሚገኙ ቦታዎች አሁንም “የጸጥታ ችግር ስጋት” መኖሩ፤ በእነዚያ ስፍራዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ላይ ትምህርት ላለመጀመሩ ምክንያት መሆኑን ዶ/ር ኪሮስ በተጨማሪነት ጠቅሰዋል። ከእነዚህ ውጭ ባሉ አካባቢዎች ደግሞ ትምህርት ቤቶች በጦርነቱ ምክንያት ሙሉ ለሙሉ በመውደማቸው፤ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ አለመመለሳቸውን አክለዋል።
የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ያስከተለውን ጉዳት በተመለከተ የገንዘብ ሚኒስቴር ያዘጋጀው የጥናት ሪፖርት እንደሚያሳየው፤ በትግራይ ክልል ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች ብዛት 1,987 ናቸው። ከእነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ አብዛኛዎቹ ውድመት የደረሰባቸው መሆኑን ያመለከተው ጥናቱ፤ በአጠቃላይ በክልሉ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ላይ የደረሰው ጉዳት 467.63 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት መሆኑን ይፋ አድርጓል።
በትግራይ ክልል በነበረው ጦርነት ከትምህርት ቤቶች በተጨማሪ ጦርነት በተማሪዎች ላይም ጉዳት መድረሱን ዶ/ር ኪሮስ አጽንኦት ይሰጣሉ። ወደ ትምህርት ገበታ ካልተመለሱ ተማሪዎች ውስጥ የተወሰኑቱ፤ ከዚህ ጋር በተገናኘ ምክንያት መሆኑንም ይናገራሉ። “በድሮን፣ በከባድ የጦር መሳሪያ፤ ብዙ አካል ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች አሉ። እነርሱ ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ክራንች፣ ዊልቸርም ያስፈልጋቸዋል። እነሱን አላቀረብንላቸውም” ሲሉ የትምህርት ቢሮ ኃላፊው በዚህ በኩል ክፍተት መኖሩን አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)