በአማኑኤል ይልቃል
በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን በዛሬው ዕለት በድጋሚ ሲካሄድ በዋለው ህዝበ ውሳኔ፤ “በርከት ያሉት” መራጮች የያዙት መታወቂያ ከተሰጠ ስድስት ወር ያልሞላው ሆኖ መገኘቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። እነዚህ መራጮች በዞኑ ነዋሪ መሆናቸውን የሚያረጋግጡ ሌሎች አማራጮችን ተግባራዊ ማድረጉን ቦርዱ ገልጿል።
ምርጫ ቦርድ ይህንን ያለው የ“ደቡብ ኢትዮጵያ” ክልልን ለመመስረት በወላይታ ዞን እየተደረገ ያለውን ህዝበ ውሳኔ አስመልክቶ ዛሬ ሰኞ ሰኔ 12፤ 2015 ባወጣው መግለጫ ነው። ምርጫ ቦርድ በዚሁ መግለጫው፤ በህዝበ ውሳኔው ከተሳተፉ ድምጽ ሰጪዎች ውስጥ “በርከት ያሉት” ቦርዱ መራጮችን ለመመዝገብ ያስቀመጠውን መስፈርት የማያሟሉ ናቸው ብሏል።
በ2012 ዓ.ም የወጣው የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ፤ “ማንኛውም ሰው በምርጫ ክልሉ ቢያንስ ስድስት ወር የኖረ ከሆነ በመራጭነት ሊመዘገብ ይችላል” ሲል ደንግጓል። በዛሬው ህዝበ ውሳኔ ላይ ድምጻቸውን ለመስጠት የወጡ “በርካታ” የዞኑ ነዋሪዎች የያዙት መታወቂያ፤ “ከተሰጣቸው ስድስት ወር ያልሞላው” ሆኖ መገኘቱን ምርጫ ቦርድ በመግለጫው አመልክቷል።
ቦርዱ ይህን ያረጋገጠው፤ ድምጽ ለመስጠት የሚመጡ ነዋሪዎችን ምዝገባ ለመፈጸም መታወቂያቸው በሚታይበት ጊዜ መሆኑን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከተቋሙ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል። ምርጫ ቦርድ ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት የድምጽ አሰጣጦች በተለየ ሁኔታ፤ በዛሬው ህዝበ ውሳኔ የመራጮች ምዝገባ እና የድምጽ የመስጠት ሂደትን ያከናወነው በአንድ ቀን ነው።
ምርጫ ቦርድ ይህንን አሰራር የተከተለው ጥር 29፤ 2015 በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ ወቅት፤ ከመራጮች ምዝገባ ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ የህግ ጥሰቶች በድጋሚ እንዳይፈጸሙ ለማድረግ እንደሆነ ማስታወቁ ይታወሳል። በዛሬው ዕለት በድጋሚ በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ፤ ከመታወቂያ ጋር በተያያዘ ችግር ለታየባቸው መራጮች የተለየ አሰራር በመጠቀም ድምጽ እንዲሰጡ መደረጉን ምርጫ ቦርድ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
ከተሰጠ ስድስት ወር ያልሞላው መታወቂያ የያዙ የወላይታ ዞን ነዋሪዎች ዛሬ ድምጽ እንዲሰጡ የተደረገው፤ “የሶስት ሰዎች ምስክርነት ወይም ሌሎች ሕጋዊ የሰነድ ማስረጃዎችን” እንዲያቀርቡ በማድረግ እንደሆነ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል። በዚህ አይነት መልኩ የተስተናገዱትን መራጮች ጨምሮ በዛሬው ህዝበ ውሳኔ በግማሽ ቀን ውስጥ ብቻ 370,552 ሰዎች ድምጽ እንደሰጡ ቦርዱ ገልጿል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዚህ ህዝበ ውሳኔ አንድ ሚሊዮን ገደማ ነዋሪዎች ይሳተፋሉ የሚል ግምት እንደነበረው ማስታወቁ አይዘነጋም።
ምርጫ ቦርድ በዛሬው ምዝገባ እና የድምጽ የመስጠት ሂደት መራጮችን ያስተናገደባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ብዛት፤ ባለፈው ጥር ወር በዞኑ ህዝበ ውሳኔ ሲካሄድ ከነበሩት ጣቢያዎች ቁጥር በ62.9 በመቶ ማደጉን በዛሬው መግለጫው ጠቅሷል። በእነዚህ ምርጫ ጣቢያዎች ሲካሄድ የዋለው ህዝበ ውሳኔ፤ የድምጽ መስጫ ጊዜው ሊጠናቀቅ ይገባው ከነበረው በአንድ ሰዓት ያህል እንዲራዘም መደረጉን ቦርዱ ምሽቱን ባሰራጨው መረጃ ገልጿል። ምርጫ ቦርድ ከዚህ በተጨማሪም የምርጫ ወረቀት ባለቀባቸው “አንዳንድ” የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የሚገኙ መራጮች፤ “በሌሎች አጎራባች ጣቢያዎች” ድምጽ እንዲሰጡ መደረጉን አስታውቋል።
ዛሬ በድጋሚ ህዝበ ውሳኔ ያስተናገደው የወላይታ ዞን፤ የ“ደቡብ ኢትዮጵያ” ክልልን እንዲመሰርቱ ከሚጠበቁ የነባሩ ደቡብ ክልል 11 መዋቅሮች ውስጥ አንዱ ነው። ከወላይታ ዞን ውጭ ያሉት አምስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች፤ ባለፈው ጥር ወር በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ በጋራ ክልል የመመስረት ሀሳብን በአብላጫ ድምጽ ማጽደቃቸው አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)