በፌዴሬሽን ምክር ቤት በጸደቀ ቀመር መሰረት በጀት ለወረዳዎች የሚያሰራጩት ሶስት ክልሎች መሆናቸው ተገለጸ

በሃሚድ አወል

የፌደራል መንግስት ለክልሎች ከሚሰጠው የበጀት ድጋፍ ውስጥ፤ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የጸደቀውን የማከፋፈያ ቀመር ተከትለው ለወረዳዎች የድጎማ ገንዘብ የሚያሰራጩት ሶስት ክልሎች መሆናቸውን የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ። አፈ ጉባኤው የድጎማ በጀት ለወረዳዎች “በትክክል ያሰራጫሉ” ያሏቸው ክልሎች፤ ደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብ እና ሲዳማ ክልሎች ናቸው።

በ1987 ዓ.ም. የወጣው ኢትዮጵያ ሕገ መንግስት፤ የፌደራል መንግስት ለክልሎች ድጎማ የሚሰጥበትን ቀመር የመወሰን ስልጣን የሰጠው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው። በ2010 ተግባራዊ መሆን የጀመረው እና አሁን በስራ ላይ ያለው የድጎማ በጀት ማከፋፈያ ቀመር፤ የክልሎችን የህዝብ ብዛት፣ የዕድገት ደረጃ፣ የድህነት ሁኔታ፣ ገቢ የመሰብሰብ አቅም እና የወጪ ፍላጎትን ታሳቢ በማድረግ የተሰላ ነው።

የፌደራል መንግስት በ2016 በጀት ዓመት ለክልሎች የመደበው የበጀት ድጋፍ 214 ቢሊዮን ብር መሆኑን፤ የዛሬ ሁለት ሳምንት ገደማ ለፓርላማ ባቀረበ የበጀት ረቂቅ ሰነድ ላይ ይፋ ተደርጓል። የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የተካተቱበት ይህ የገንዘብ ድጋፍ መጠን፤ ከዘንድሮው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ2.24 በመቶ ጭማሪ ያለው ነው። 

ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ በመጪው የበጀት ዓመት ለክልሎች እንዲከፋፈል የተመደበው የገንዘብ መጠን 14 ቢሊዮን ብር መሆኑም በበጀት ሰነዱ ተመላክቷል። በ2016 በጀት ዓመት ለክልሎች የሚደረገው የዘላቂ ልማት ግቦች ድጋፍ፤ “የተጀመሩ የአግሮ ኢንዱስትሪ ግንባታዎችን ለማጠናቀቅና በአነስተኛ መስኖ ስራዎች ድጋፍ ላይ ብቻ እንዲያተኩር ታሳቢ በማድረግ የተመደበ” መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የበጀት መግለጫውን ለፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት ተናግረው ነበር።

ከፌደራል መንግስት እና ከዓለም አቀፍ አካላት ለክልሎች የሚተላለፉ በጀቶች “ውስን ዓላማ ያላቸው” መሆኑ ትላንት ሰኞ ሰኔ 12፤ 2015 በተካሄደ የፌደሬሽን ምክር ቤት እና የክልሎች የጋራ የምክክር መድረክ ላይ ተነስቷል። በዚህ አይነት መልኩ ለክልሎች የሚከፋፈሉት በጀቶች ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለውሃ እና ለመሳሰሉት አገልግሎቶች ሊውል እንደሚገባው በስብሰባው ላይ የጠቆሙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር፤ እነዚህ በጀቶች “በስርዓቱ መሰረት፤ ለተባለለት ዓላማ ነው ወይ የሚሰራጩት?” ሲሉ ጠይቀዋል። 

“ከፌደራል የሚመደበው በጀት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ክልሎች ለወረዳዎች የሚያሰራጩት በጀት ምን ያህል ፍትሃዊ ነው?” ሲሉ ቀደም ሲል ያነሱትን ጥያቄ በአጽንኦት ደግመውታል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይህ በተመለከተ ጥናት ማድረጉን የገለጹት አቶ አገኘሁ፤ “በትክክል በቀመሩ መሰረት” ለወረዳዎች በጀት የሚያሰራጩት የደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብ እና ሲዳማ ክልሎች መሆናቸውን ለተሰብሳቢው አስታውቀዋል።

ፎቶ፦ የፌዴሬሽን ምክር ቤት

አቶ አገኘሁ የጠቀሱት ጥናት፤ የፌደራል የድጎማ በጀት ወደ ክልል የሚተላለፍበትን እንዲሁም ከክልል ወደ ዞን እና ወረዳ የሚሰራጭበትን አካሄድ የፈተሸ እንደሆነ በፌደሬሽን ምክር ቤት የፊስካል ጉዳዮች እና የክልሎች የተመጣጠነ ዕድገት ጥናት ዳይሬክተር አቶ ዋቅቶሌ ዳዲ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ጥናቱ ገና ይፋ ባለመደረጉ፤ በፍተሻው የተደረሰባቸውን ግኝቶች አሁን በዝርዝር መናገር እንደማይችሉ ገልጸዋል።

በትላንትናው መድረክ በፌዴሬሸን ምክር ቤት ቀመር መሰረት “ለወረዳዎች በጀት የማሰራጨት ጥሩ ተሞክሮ አላቸው” ተብለው ከተጠቀሱ ክልሎች አንዱ የሆነው ነባሩ የደቡብ ክልል፤ ይህንኑ መነሻ በማድረግ በየዓመቱ የራሱን ክፍፍል ሲያዘጋጅ የቆየ ነው። የደቡብ ክልል በጀቱን በስሩ ወዳሉት ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ለማሰራጨት ስድስት መለኪያዎችን (indicators) እንደሚጠቀም የክልሉ የገንዘብ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።

ክልሉ ለበጀት ክፍፍል የሚጠቀምባቸው መለኪያዎች ግብርና፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የገጠር መንገድ ተደራሽነት እንዲሁም ገቢ የመሰብሰብ አቅም እና የወጪ ፍላጎት መሆናቸውን አቶ ተፈሪ ዘርዝረዋል። “አንዱ አካባቢ በሆነ አጋጣሚ በንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን የተጎዳ ከሆነ፤ ቀመሩ ድጎማ የሚያደርገው ለተጎዳው ነው” ሲሉ አተገባበሩን ማሳያ በመጥቀስ አብራርተዋል። 

የደቡብ ክልል ለዘንድሮው በጀት ዓመት ካጸደቀው 46.3 ቢሊዮን ብር ውስጥ፤ 82 በመቶው በቀጥታ ለዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች የተሰራጨ መሆኑን አቶ ተፈሪ ጠቅሰዋል። የደቡብ ክልል በፌዴሬሽን ምክር ቤት በተሰራው ቀመር መሰረት የሚያገኘው የድጎማ መጠን፤ የፌደራል መንግስት ለክልሎች ከሚመድበው በጀት 20.1 በመቶ ያህል ነው። ይህ የድርሻ መጠን፤ የደቡብ ክልልን ከኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች በመቀጠል ሶስተኛው ከፍተኛ የድጎማ ተጠቃሚ ያደርገዋል። 

የፌደራል የበጀት ድጎማን ለወረዳዎች በማከፋፈል ረገድ ከደቡብ ክልል ጋር ተመሳሳይ አሰራር እንደሚከተሉ የሲዳማ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። ሁለቱም ክልሎች ራሳቸውን ችለው በህዝበ ውሳኔ በክልልነት ከመደራጀታቸው በፊት የነባሩ የደቡብ ክልል አካል ነበሩ። የሲዳማ ክልል ዘንድሮ ከፌደራል መንግስት ካገኘው የድጎማ በጀት ውስጥ 71 በመቶውን የሐዋሳ ከተማን ጨምሮ በስሩ ላሉ የወረዳ መዋቅሮች እንዳሰራጨ የክልሉ የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አራርሶ ገረመው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።  

ከጸደቀ ስድስት ዓመት ባስቆጠረው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የክፍፍል ቀመር መሰረት፤ ከፌደራል መንግስት አነስተኛ የድጎማ በጀት ሲያገኙ የቆዩት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ሐረሪ፣ ጋምቤላ ክልሎች እንዲሁም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ናቸው። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በዘንድሮው በጀት ዓመት ከፌደራል መንግስት በድጎማ ካገኘው በጀት ውስጥ በስሩ ላሉ ወረዳዎች ያሰራጨው 63 በመቶውን መሆኑን የክልሉ የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዚያድ አብዱላሂ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዚያድ አብዱላሂ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ ዞኖች የተዋቀሩት እንደ አንድ የክልሉ አስፈጻሚ አካል በመሆኑ፤ የክልሉ መንግስት በጀት የሚያሰራጨው በቀጥታ ለወረዳዎች መሆኑንም ኃላፊው አመልክተዋል። አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር የፌዴሬሽን ምክር ቤት ያጸደቀውን ቀመር “በትክክል ተግባራዊ በማድረግ” በምሳሌነት ከጠቀሷቸው ክልሎች ውስጥ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስሙ ባይጠራም፤ ክልሉ ግን ለወረዳዎች በጀት የሚያሰራጨው ይህንኑ የክፍፍል ቀመር መሰረት በማድረግ መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቋል።

ክልሉ በዚህ ቀመር ላይ በመመስረት ባዘጋጀው የራሱ የክፍፍል ቀመር ላይ “በየአመቱ የተሻሻሉ መረጃዎች ሲያክል” መቆየቱን የሚናገሩት አቶ ዚያድ፤ ያም ቢሆን ግን በቀመሩ “መሰረታዊ pillar” ላይ ለውጥ ያስከተለ አለመሆኑን ያስረዳሉ። ክልሉ ከፌደራል መንግስት የሚያገኘውን የድጎማ በጀት ለወረዳዎች የሚያሰራጭባቸው መለኪያዎች “ተመሳሳይ መሆናቸውን” ለዚህ በማሳያነት ያነሳሉ። “የትምህርት ቤት ተደራሽነቱ ከፍ ያለ ወረዳ አስተዳደራዊ በጀቱ ከፍ ይላል። የትምህርት ስርጭቱ ዝቅ ያለ ደግሞ፤ ካፒታል በጀቱ ይጨምራል” ሲሉ ቀመሩን የተከተለ ነው ያሉትን አሰራር አብራርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)