በሃሚድ አወል
በፌደራል መንግስት በኩል 2016 በጀት ዓመት የአዳዲስ ሰራተኛ ቅጥር እንዳይኖር የተደረገው፤ የሀገሪቱን ሲቪል ሰርቪስ ለማሻሻል በመታሰቡ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታው ዶ/ር እዮብ ተካልኝ ተናገሩ። መንግስት በጀት ሲያዘጋጅ፤ “የግሉን ዘርፍ በማነቃቃት” እና “ስራ ፈጠራን ማዕከል ባደረገ” መልኩ መሆኑንም ሚኒስትር ዲኤታው ገልጸዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት ሰኔ 1፤ 2015 በፓርላማ በተካሄደ መደበኛ ስብሰባ፤ የ2016 በጀት ዝግጅት የተደረገው የአዳዲስ ሰራተኛ ቅጥር እንደማይኖር ታሳቢ ተደርጎ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ተናግረው ነበር። በኢትዮጵያ የመንግስት ሰራተኛው ቁጥር “እጅግ በጣም ከፍተኛ” መሆኑን በወቅቱ ያነሱት አቶ አህመድ፤ “እንኳን አዳዲስ ሰራተኛ ለመቅጠር ያሉትን ሰራተኛም ጭምር አንዳንድ መዋቅር ማስተካከያ አድርገናል” ብለዋል።
በዚህም ምክንያት የ2016 በጀት ሲዘጋጅ በየመስሪያ ቤቱ ያለው “አዲሱ አደረጃጀት” እንዲሁም “የበጀት አጠቃቀም በቁጥባና በውጤታማነት ላይ ያተኮረ እንደሚሆን” ታሳቢ ተደርጎ መሆኑን ሚኒስትሩ አስገንዝበው ነበር። ከዚህ የሚኒስትሩ ማብራሪያ በኋላ አነጋጋሪ ሆኖ የሰነበተው የአዳዲስ ሰራተኞች ቅጥር ጉዳይ፤ ዛሬ ረቡዕ ሰኔ 14፤ 2015 በፓርላማ በተካሄደ የአስረጂ መድረክ ስብሰባ ላይም በድጋሚ ተነስቷል።
የፌዴራል መንግስት የ2016 የበጀት ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ የገንዘብ ሚኒስቴር ኃላፊዎችን ወደ ፓርላማ በመጋበዝ የዛሬውን የአስረጂ መድረክ ያዘጋጀው፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ነው። አቶ ወንድወሰን አድማሴ የተባሉ የዚሁ ቋሚ ኮሚቴ አባል፤ “እንደ ሀገር በርካታ ስራ አጥ ባለበት እና አሁን ያለውን ስራ አጥ መሸከም የሚችል የግል ዘርፍ ባልተፈጠረበት በአዋጅ አዲስ ቅጥር አይኖርም ብሎ ማወጁና ዝግ ማድረጉ ተገቢ ነው ወይ?” ሲሉ ጠይቀዋል።
የፓርላማ አባሉ አክለውም “አስፈላጊነቱ እየተገመገመና በሚመለከተው አካል ውሳኔ እየተሰጠበት የሚቀጠር ይሆናል በሚል ቢስተካከል አይሻልም ወይ?” ሲሉ ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል። በአስረጂ መድረኩ ላይ የተገኙት ዶ/ር እዮብ፤ “ትልቁ ስራ ፈጣሪ መንግስት ነው” የሚል “የተሳሳተ እሳቤ መኖሩን” ተናግረዋል። “ትልቁ የመንግስት ሚና ስራ ለመፍጠር የሚያስችል ከባቢ መፍጠር ነው” ያሉት ዶ/ር እዮብ፤ የግሉ ዘርፍ ሲነቃቃ በርካታ የስራ ዕድል እንደሚፈጠር ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ገልጸዋል።
ለ2016 በጀት ዓመት የግሉን ዘርፍ ማነቃቃትን “ከግምት ያስገባ የበጀት ዝግጅት” መደረጉንም ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል። መንግስት የ2016ን በጀት ሲያዘጋጅ “ስራ ፈጠራን ማዕከል አላደረገም በሚል መታየት የለበትም” ያሉት ዶ/ር እዮብ፤ “ሃሳቡ ሰራተኞቻችንን ምርታማ እናድርጋቸው፣ እስኪ ቆም ብለን ሲቪል ሰርቪሱን እንይ የሚል ነው” ሲሉ ከውሳኔው ጀርባ ያለውን ምክንያት አመልክተዋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ እስከ 2.4 ሚሊዮን ሰራተኞችን ያቀፈው የሲቪል ሰርቪስ የተቃኘበት ሁኔታ ችግር ያለበት መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በዚህም ምክንያት አዳዲስ ቅጥር አቁሞ ባሉት ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ከውሳኔ ላይ መደረሱን አብራርተዋል።
በቀጣዩ ዓመት የአዳዲስ ሰራተኞች ቅጥር በመንግስት እንደማይካሄድ መገለጹ በፓርላማ ሲያነጋግር የዛሬው የመጀመሪያው አይደለም። በጀቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፓርላማ በቀረበበት ወቅት፤ ለገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ስጋት አዘል ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ነበር። አንዲት የፓርላማ አባል፤ በውሳኔው ምክንያት “ምሁራንን ለአላስፈላጊ ስደት ልንዳርጋቸው እንችላለን” ሲሉ በወቅቱ ተደምጠዋል። የአዳዲስ ሰራተኞች አለመቀጠር ጉዳይ “የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ ሊቀጥል ይችላል” ሲሉም ትንበያቸውን አስቀምጠዋል።
መንግስት ከስራ ፈጠራ ጋር በተያያዘ የሚኖረውን ሚና በተመለከተ የገንዘብ ሚኒስትሩ በዚሁ ምላሻቸው ያቀረቡት ማብራሪያ፤ በዛሬው ስብሰባ ዶ/ር እዮብ ያነሱትን ሃሳብ ያስተጋባ ነበር። “መንግስት የስራ ዕድል መፍጠሪያ ማሽነሪ አይደለም” ሲሉ በወቅቱ የተናገሩት አቶ አህመድ፤ “ዋናው ቀጣሪ መሆን ያለበት የግሉ ዘርፍ ነው። ስለዚህ የግል ዘርፍ እድገትን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ የሁለተኛው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ዋነኛ ማጠንጠኛ ስለሆነ በዚያ አይን ቢታይ ጥሩ ነው” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)