የራያ አካባቢዎች በጀት ለትግራይ ክልል እንዳይተላለፍ የሚጠይቅ የ145ሺህ ሰዎች ፊርማ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀረበ

በአማኑኤል ይልቃል

የፌደራል መንግስት ለሚቀጥለው በጀት ዓመት “በራያ እና አካባቢው ለሚገኙ መዋቅሮች የሚመድበው ድጎማ”፤ ወደ ትግራይ ክልል እንዳይተላለፍ የቀረበን ጥያቄ የደገፉ የ145 ሺህ ሰዎች ገደማ ፊርማ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀረበ። በአካባቢው የሚገኙ ሶስት ወረዳዎች እና አንድ የከተማ አስተዳደርን የተመለከተው ጥያቄ የቀረበለት የፌዴሬሽን ምክር ቤት፤ ጉዳዩን ለመመልከት ቃል ገብቷል ተብሏል።

ይህንን ጥያቄ የሚደግፉ ሰዎችን ፊርማ አሰባስቦ ከትላንት በስቲያ ሰኞ ሰኔ 12፤ 2015 ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያስረከበው፤ የወሎ ራያ አማራ ማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ ነው። ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በደብዳቤ የቀረበው ይህ ጥያቄ፤ የሰሜኑ ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት በትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን ስር የነበሩ አራት መዋቅሮችን የተመለከተ ነው። 

እነዚህ መዋቅሮች በትግራይ ክልል ስር በነበሩበት ወቅት “የማንነት ጥያቄ ይነሳባቸው” እንደነበር የጠቀሰው ደብዳቤው፤ ሆኖም የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ተከትሎ የአካባቢው ህዝብ “ራሱን በራሱ ለማስተዳደር” መቻሉን አትቷል። ጥያቄውን ያቀረቡት አመልካቾች፤  የአካባቢው ህዝብ “ከፌደራል መንግስቱ ሊያገኝ ይገባ የነበረው በጀት” የሚላከው “በትግራይ ክልል በኩል ነው” በመባሉ ምክንያት እስካሁን የገንዘብ ድጎማ አለማግኘታቸውን ያስረዳል።

“ይህ አይነቱ አካሄድ ላይ ላዩን ሲታይ ከህጋዊነት ጋር የሚገናኝ ቢመስልም፤ በይዘት እና በውጤት ደረጃ ሲታይ ግን የአንድን ህዝብ መሰረታዊ ሕገ መንግስታዊ መብት የሚጥስ ነው። [አካሄዱ] ነጻነትህን የምትመርጥ ከሆነ ምግብ፣ መጠጥ፣ ትምህርት፣ ህክምና፣ አጠቃላይ የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያው አገልግሎቶችን ማግኘት አትችልም እንደማለት ነው” ሲሉ አመልካቾቹ በደብዳቤው ተቃውሟቸውን አቅርበዋል። በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት መሰረት ዜጎች “በመንግስት ገንዘብ የሚካሄዱ ማህበራዊ አገልግሎቶችን በእኩልነት የመጠቀም መብት አላቸው” ያሉት አመልካቾቹ፤ አካሄዱ “ይህን የጣሰ ነው” ሲሉ ተችተዋል። 

አመልካቾቹ “የአካባቢው ህዝብ ራሱን በራሱ ማስተዳደር በመምረጡ እና በትግራይ ክልል ስር አልተዳደርም በማለቱ ምክንያት፤ መንግስታዊ አገልግሎት እንዳያገኝ መደረግ የለበትም” በማለት “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በተመለከተችው ደብዳቤ ላይ አስፍረዋል።    በመሆኑም የፌደራል መንግስት በበጀት ድጎማ ቀመር መሰረት፤ ለራያ አላማጣ፣ ራያ ባላ፣ ራያ ወፍላ ወረዳዎች እንዲሁም ለአላማጣ ከተማ የመደበውን በጀት “ለየአካባቢው አስተዳደሮች በቀጥታ ሊሰጥ ይገባል” ሲሉ አቋማቸውን አስታውቀዋል። 

ይህ አቋም የተንጸባረቀበትን ደብዳቤ ደግፈው ፊርማቸውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያስተላለፉ የአካባቢው ነዋሪዎች ብዛት 145,122 መሆኑን የወሎ ራያ አማራ ማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ሃይሉ አበራ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። እነዚህ ፊርማዎች የተሰባሰቡት በአሁኑ ወቅት ተጠሪነታቸው ለአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን በሆኑት ራያ አላማጣ፣ ራያ ባላ፣ ራያ ወፍላ እና ዛታ ወረዳዎች እንዲሁም ከኮረም ከተማ መሆኑን አቶ ሃይሉ ገልጸዋል። አብዛኞቹ ፊርማዎች የተሰበሰቡት ከአላማጣ ከተማ መሆኑም ተነግሯል። 

በ4,586 ገጾች የተካተቱትን እነዚህን ፊርማዎች ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ከትላንት በስቲያ ያስገቡት የወሎ ራያ አማራ የማንነት እና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ አባላት፤ ትላንት ማክሰኞ ሰኔ 13፤ 2015 ረፋድ ከምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ጋር ውይይት አድርገዋል። የአላማጣ ከንቲባ ጭምር የሆኑት አቶ ሃይሉን ጨምሮ ስምንት የኮሚቴው አባላት ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ቅጽር ግቢ ሲገቡ በስፍራው የነበረው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ተመልክቷል። 

በትላንቱ ውይይት፤ አፈ ጉባኤው አቶ አገኘሁ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የቀረበለትን ጥያቄ ጉዳዩ ከሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ጋር በመሆን ከተመለከተ በኋላ “ምላሽ ለመስጠት” ቃል መግባታቸውን አቶ ሃይሉ ተናግረዋል። የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምንጭ፤ የወሎ ራያ አማራ ማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ አባላት ከአፈ ጉባኤው ጋር መገናኘታቸውን አረጋግጠዋል። ሆኖም በወይይቱ የተነሱ ጉዳዮችን በዝርዝር ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወዲህ ከትግራይ ክልል አስተዳደር ስር ለወጡ አካባቢዎች የሚደረግ የፌደራል መንግስት የበጀት ድጎማ የመተላለፍ ጥያቄ፤ የዛሬ ሁለት ሳምንት ገደማ በፓርላማ አነጋግሮ ነበር። የቀጣዩ በጀት ዓመት መግለጫ በቀረበበት በዚሁ የፓርላማ ስብሰባ፤ የፌደራል መንግስት በ2016 ለክልሎች ሊሰጥ የያዘው ድጋፍ 214 ቢሊዮን ብር መሆኑ ይፋ ተደርጓል። ከዚህ በጀት ውስጥ የትግራይ ክልል 12.59 ቢሊዮን ብር የሚያገኝ ሲሆን፤ ለአማራ ክልል የተመደበው ደግሞ 45.1 ቢሊዮን ብር ነው።

የ2016 የበጀት መግለጫ በቀረበበት በተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ፤ የአማራ ክልል “የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ሰቲት፣ ሁመራ እና ራያ ህዝብን የበጀት እና የልማት ፍላጎት ተሸክሞ ያለ” መሆኑን የፓርላማ አባሉ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ አንስተዋል። የተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አባል የሆኑት ዶ/ር ደሳለኝ፤ የፌደራል መንግስቱ ለክልሎች የሚሰጠውን የበጀት ድጎማ ሲመድብ ይህንን ጉዳይ እንዴት እንደተመለከተው ማብራሪያ ጠይቀው ነበር።

በዚሁ የፓርላማ ውሎ ላይ የበጀት ዝርዝሩን ያቀረቡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፤ “የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ሰቲት፣ ሁመራ ዞን የበጀት ጥያቄን በተመለከተ የህዝቡን ጥያቄ በከፍተኛ ደረጃ እናውቃለን። የህዝቡንም ጥያቄ እናከብራለን” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ ከአማራ ክልል መንግስት እና ከአካባቢዎቹ አስተዳደሮች ጋር ውይይት መደረጉን በወቅቱ የጠቀሱት የገንዘብ ሚኒስትሩ፤ ይሁንና የሚመሩት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሚና “በምክር ቤቱ የጸደቀለትን በጀት ማስተዳደር ብቻ” መሆኑን ተናግረዋል። 

የአማራ እና ትግራይ ክልሎች የድጋፍ በጀት የተሰራው ከፌዴሬሽን ምክር ቤት በቀረበ ቀመር መሆኑን ለምክር ቤቱ ያስረዱት አቶ አህመድ፤ የገንዘብ ሚኒስቴር ለሁለቱ ክልሎች የሚያስተላልፈው በጀት በዚህ ቀመር መሰረት የተዘጋጀ መሆኑን አስገንዝበዋል። ለክልሎቹ የሚመደበው የገንዘብ መጠን መስተካከል የሚችለውም “ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ተከትሎ ቀመሩን ሲያሻሽል” መሆኑን ለምክር ቤቱ ገልጸዋል። የገንዘብ ሚኒስትሩ “ለዞኖች፣ ለወረዳዎች በጀት የማስተላለፍ ስልጣንም፤ ኃላፊነትም የለንም” ሲሉ የሚመሩት መስሪያ ቤት ከተሰጠው “የህግ ማዕቀፍ ውጪ” መስራት እንደማይችል በወቅቱ በሰጡት ማብራሪያ አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)