የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዋና ስራ አስፈጻሚ አንዋር ሶሳ በመጪው ሐምሌ ከኃላፊነታቸው እንደሚለቅቁ ኩባንያው አስታወቀ። ለሁለት ዓመታት ገደማ ኩባንያውን የመሩት ግሪካዊው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከኃላፊነታቸው የሚሰናበቱት፤ በኢትዮጵያ እንዲሰሩ የተመደቡበት የዝውውር ጊዜ በመጠናቀቁ መሆኑን መቀመጫውን በኬንያ ያደረገው ሳፋሪኮም አስታውቋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያን በነሐሴ 2013 የተቀላቀሉት የድርጅቱን ምስረታ በበላይነት ለመምራት እንደነበር ኩባንያው ገልጿል። የሳፋሪኮም ኢትዮጵያን የንግድ ስራዎች እና ከፍተኛ ጥራት ያለው ኔትወርክ መዘርጋት፤ አንዋር ሶሳ በኢትዮጵያ በተመደበቡባቸው ሁለት ዓመታት የተጣሉባቸው ኃላፊነቶች ነበሩ።
አንዋር ሶሳ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነውን የግል የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ በዋና ስራ አስፈጻሚነት በመሩባቸው ያለፉት ሁለት ዓመታት፤ ሳፋሪኮም አራት ሚሊዮን ደንበኞች አፍርቷል። ኩባንያው አገልግሎት የሚሰጥባቸው ከተሞች ቁጥርም 50 ደርሷል።
በአንዋር የአመራርነት ዘመን ኩባንያው በተንቀሳቃሽ ስልክ የፋይናንስ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን ፈቃድ ማግኘቱ ሳፋሪኮም ስንብታቸውን ይፋ ሲያደርግ ከጠቀሳቸው ስኬቶች አንዱ ነው። ሳፋሪኮም 150 ሚሊዮን ዶላር በመክፈል ከብሔራዊ ባንክ የተቀበለው ፈቃድ ኬንያን በመሳሰሉ አገሮች ስኬታማ የሆነበትን ኤምፔሳ በኢትዮጵያ ለመጀመር መንገድ ጠርጎለታል።
አንዋር ሶሳ፤ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያን የማደራጀት ኃላፊነት ተረክበው ወደ አዲስ አበባ ከመምጣታቸው በፊት፤ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የቮዳኮም ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ነበሩ። ከቮዳኮም በፊት፤ በኡጋንዳ እና በቻድ “ኤየርቴል” የተባለውን ኩባንያ በዋና ስራ አስፈጻሚነት መርተዋል። በደቡብ አፍሪካው ኤምቲኤን፣ በጃማይካ እና የካሪቢያን አገራት የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ በሆነው ዲጂሴል ኩባንያዎች ውስጥም በከፍተኛ አመራርነት ያገለገሉ ሰው ናቸው።
ሳፋሪኮም “በስራ ዘመናቸው ሁሉ የማይናወጥ ቁርጠኝነት አሳይተዋል” ያላቸው አንዋር ሶሳ፤ ኩባንያው ላስመዘገባቸው ስኬቶች “ወሳኝ ሚና” እንደነበራቸው ገልጿል። አንዋር ሶሳን የሚተካው የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈጻሚን “በጊዜው” ይፋ እንደሚያደርግ ኩባንያው አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)