በአማኑኤል ይልቃል
በ2016 የበጀት ሰነድ ላይ በርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶች የተመደበላቸው ገንዘብ ከአስር ሚሊዮን ብር በታች መሆኑ፤ በፓርላማ ውይይት “አነስተኛ ነው” የሚል ቅሬታ አስነሳ። የፌደራል መንግስትን በጀት ያዘጋጀው የገንዘብ ሚኒስቴር፤ የእነዚህ የመንገድ ፕሮጀክቶች ጉዳይ “በበጀት አስተዳደር” ሊታይ እንደሚችል አስታውቋል።
የገንዘብ ሚኒስቴር በተያዘው ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ ለፓርላማ ያቀረበው የ2016 በጀት አጠቃላይ መጠን 801.6 ቢሊዮን ብር ነው። ከዚህ በጀት ውስጥ ለመንገድ ፕሮጀክቶች የተመደበው ገንዘብ 68.4 ቢሊዮን ብር ሲሆን፤ ይህም ከፌደራል መንግስት የመደበኛ እና የካፒታል ወጪ ውስጥ 11.93 በመቶውን የሚሸፍን ነው።
በሚቀጥለው ሳምንት መጨረሻ በሚጀምረው የ2016 በጀት ዓመት፤ ለ300 ገደማ የመንገድ ፕሮጀክቶች የካፒታል በጀት እንደተያዘላቸው ለፓርላማ በቀረበው የበጀት ረቂቅ ሰነድ ላይ ሰፍሯል። ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ውስጥ ከፍተኛው በጀት የተያዘው፤ የአርሲ ነገሌ – ሐዋሳ መንገድ ሲሆን፤ ይህ ፕሮጀክት 1.09 ቢሊዮን ብር እንደተበጀተለት በሰነዱ ላይ ተጠቅሷል።
በበጀት ዝርዝሩ መሰረት፤ ከፕሮጀክቶቹ ውስጥ አነስተኛ ገንዘብ የተያዘለት 500 ሺህ ብር የተመደበለት የጎግ – ጆር – አኮቦ (ሎት 2) የመንገድ ፕሮጀክት ነው። ለሚቀጥለው በጀት ዓመት ገንዘብ ከተያዘላቸው ጠቅላላ የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ፤ 100 ገደማው የተመደበላቸው በጀት ከአስር ሚሊዮን ብር በታች መሆኑ በበጀት ሰነዱ ላይ ተቀምጧል።
ለእነዚህ መሰል የመንገድ ፕሮጀክቶች የተመደበው የገንዘብ መጠን “አነስተኛ መሆን”፤ ዛሬ ሰኞ ሰኔ 19፤ 2015 በፓርላማ በተካሄደ የህዝብ ይፋዊ ውይይት ላይ አነጋግሯል። በ2016 የበጀት ረቂቅ ሰነድ ላይ የሚነሱ የህዝብ አስተያየቶችን ለማድመጥ የተጠራውን የዛሬውን ውይይት ያዘጋጀው፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ነው። በውይይቱ ላይ የተገኙ ተሳታፊዎች፤ ተወክለው በመጡበት አካባቢ የሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶች የተያዘላቸውን የገንዘብ መጠን በመጥቀስ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
ቅሬታቸውን ካሰሙት ውስጥ ከአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የመጡ ሶስት ተሳታፊዎች ይገኙበታል። በዚህ ዞን የሚገኝ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክትን በተመለከተ ጥያቄ ለማቅረብ ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸው የተናገሩት ተሳታፊዎቹ፤ 72 ኪሎ ሜትር ለሚሸፍነው ፕሮጀክት የተያዘው በጀት 8.6 ሚሊዮን ብር አነስተኛ መሆኑን አንስተዋል። አቶ ይልማ ሞላ የተባሉ ከዞኑ የመጡ ተሳታፊ፤ መንገዱ በተባለው የገንዘብ መጠን እንዴት ሊሰራ እንደሚችል ጠይቀዋል።
ወ/ሮ የዝባለም ካሴ የተባሉ የተወካዮች ምክር ቤት አባል ይህንኑ የሚያስተጋባ አስተያየት ሰንዝረዋል። የፓርላማ አባሏ ከአንድ ሚሊዮን ብር ጀምሮ ገንዘብ የተመደበላቸው ፕሮጀክቶች በበጀት ዝርዝሩ ውስጥ መካተታቸውን ጠቅሰው፤ መንገዱን ለማሰራት የተጠቀሱት ቁጥሮች “እንዲሁ የተቀመጡ ነው የሚመስሉት” ሲሉ ተደምጠዋል። በበጀት ሰነዱ የተዘረዘሩት የገንዘብ መጠኖች “እውን መንገድ ያሰራሉ ወይ?” ሲሉም ጥያቄ አቅርበዋል።
ይህ አይነቱ ሀሳብ አቶ አለሙ ዳምጠው ከተባሉ የተወካዮች ምክር ቤት አባልም ተደምጧል። በቀጣዩ በጀት ዓመት ላይ ከተካተቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ የበጀት ቅናሽ የተደረገባቸው ያሉ መኖራቸውን የጠቀሱት እኚህ የፓርላማ አባል፤ ለዚህም እርሳቸው በተመረጡበት አማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ ያለን የመንገድ ፕሮጀክት በምሳሌነት ጠቅሰዋል።
ይህ የመንገድ ፕሮጀክት “94 ሚሊዮን ብር በጀት” ከተያዘለት በኋላ “ተሸጋሽጓል” በሚል ስራው መቋረጡን ያስታወሱት አቶ አለሙ፤ በ2016 በጀት ዓመት የተያዘለት የገንዘብ መጠን 7.1 ሚሊዮን ብር ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል። “[ይህ የገንዘብ መጠን] እንዴትስ ስራውን ሊያስጀምር ይችላል? የመንገድ ፕሮጀክት ነው። 64 ኪሎ ሜትር ነው። የበጀት ድልድሉ ሲሰራ ምንድናቸው ታሳቢ እየተደረጉ ያሉት?” ሲሉ በጉዳዩ ላይ ዝርዝር ምላሽ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል።
ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታው ዶ/ር እዮብ ተካልኝ፤ በበጀት ሰነዱ ውስጥ የተካተቱት የመንገድ ፕሮጀክቶች በበጀት ዓመቱ እንዲከናወኑ የተመረጡ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን አስረድተዋል። በዚህም ምክንያት የፕሮጀክቶቹ ተግባራዊ መሆን ላይ ጥያቄ ያቀረቡ ተሳታፊዎች “ሀሳብ ሊገባቸው” እንደማይገባ አሳስበዋል። ይሁንና የመንገድ ፕሮጀክቶቹ በበጀት ዝርዝሩ ላይ በተቀመጠው የገንዘብ መጠን “ይሰራሉ” ማለት እንዳልሆነ ገልጸዋል።
“በነገራችን ላይ በስምንትም፤ በ60ም ሚሊዮን [ብር] መካከልም ብዙም ልዩነት የለውም። ምክንያቱም እነዚህ መንገዶች በጣም ብዙ ሃብት ነው የሚፈልጉት። ዋናው ነገር በጀት ውስጥ ተካትተዋል። ቶሎ ወደ ስራ እንገባለን” ሲሉ ዶ/ር እዮብ ለውይይቱ ተሳታፊዎች ተናግረዋል። “ለአንዳንዶቹ” የመንገድ ፕሮጀክቶች የተያዘው የገንዘብ መጠን “ላያሰራ የሚችል ትናንሽ በጀት” መሆኑን ያመኑት የገንዘብ ሚኒስቴር የበጀት ጉዳዮች አማካሪ አቶ ተፈሪ ደመቀ በበኩላቸው፤ “አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የአንዳንዱ [የመንገድ ፕሮጀክት] የፊዚካል ስራው እና የምንይዘው በጀት ላይጣጣም ይችላል። በበጀት አስተዳደሩ ግን ልናያቸው የምንችላቸው ነገሮች አሉ” ብለዋል።
በበጀት አስተዳደር የሚከናወኑ ስራዎች፤ ለሌሎች የካፒታል ፕሮጀክቶች የተያዙ በጀቶችን “ዝውውር” እና “ሽግሽግ” በማድረግ እንደሆነም አማካሪው ጠቁመዋል። በሌሎች መስሪያ ቤቶች የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች “የፊዚካል ስራቸው” እና የተመደበላቸው በጀት የማይጣጣም ሲሆን እንዲሁም “የተረፈ በጀት ካለ” ወደ ሌሎች ፕሮጀክቶች “የበጀት ሽግሽግ” የሚደረግበት አሰራር መኖሩንም አቶ ተፈሪ አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለመጨረስ “አንድ ትሪሊዮን ብር” እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከወራት በፊት በፓርላማ በነበራቸው የጥያቄ እና መልስ ቆይታ ወቅት ተናግረው ነበር። የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ፤ በሰኔ ወር መጀመሪያ የ2016 በጀት መግለጫን ለፓርላማ አባላት ሲያቀርቡ ይህንኑ የገንዘብ መጠን ጠቅሰዋል። አቶ አህመድ በአሁኑ ወቅት በግንባታ ላይ ያሉ የመንገድ፣ የመስኖ እንዲሁም ዩኒቨርስቲዎች የጀመሯቸውን ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅ “በጣም ከፍተኛ በጀት” እንደሚጠይቅ አጽንኦት ሰጥተው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)