የፌደራል መንግስት የበጀት ቅነሳ፤ የ12ተኛ ክፍል የፈተና አሰጣጥ ሂደት ላይ “ጉድለት ያመጣል” ተባለ    

በአማኑኤል ይልቃል

የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት ለ2016 በጀት ዓመት ከጠየቀው ገንዘብ ውስጥ 476 ሚሊዮን ብር ገደማ ተቀንሶ መያዙ፤ በዘንድሮ የ12ተኛ ክፍል ፈተና ላይ ጉድለት እንደሚያስከትልበት አስታወቀ። ለ12ተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የተጠየቀውን ገንዘብ በተመለከተ፤ “ከመንግስት ውሳኔ መተላለፍ” እንዳለበት የገንዘብ ሚኒስቴር ምላሽ ሰጥቷል። 

የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት ይህንን ጥያቄ ያነሳው፤ የ2016 ረቂቅ በጀትን አስመልክቶ ዛሬ ሰኞ ሰኔ 19፤ 2015 ዓ.ም በተካሄደ የህዝብ ይፋዊ ውይይት ላይ ነው። የተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባዘጋጀው በዚህ ውይይት ላይ፤ የተቋማት ተወካዮች፣ የፓርላማ አባላት እና ሌሎች ተሳታፊዎች በጀቱን የተመለከቱ ጥያቄዎች አቅርበዋል።

ከእነዚህ ተቋማት ውስጥ አንዱ በሆነው በትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት በኩል የተነሳው ጥያቄ፤ የ12ተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ለማከናወን ከሚያስፈልገው በጀት ጋር የተያያዘ ነበር። ከዚህ ዓመት ጀምሮ በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ መሰጠት የጀመረውን የ12ተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ለማስፈጸም፤ ዘንድሮ 2.4 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት የስትራቴጂክ ጉዳዮች ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ግርማ መኮንን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።    

የዘንድሮውን የ12ተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና 870 ሺህ ገደማ ተማሪዎች እንደሚወስዱ ዛሬ በተካሄደው የበጀት ውይይት ላይ የጠቀሱት ዶ/ር ግርማ፤ ለእነዚህ ተማሪዎች ለሚቀርብ ቀለብ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚስፈልግ አስረድተዋል። ለእነዚህ ለተፈታኞች ቀለብ ለማቅረብ፤ በመደበኛው የዩኒቨርስቲዎች አሰራር ለአንድ ተማሪ በቀን የሚመደበው 22 ብር በቂ አለመሆኑንም ጠቁመዋል። አሁን ባለው የገበያ ዋጋ ለተፈታኞቹ የሚሆን ቀለብ ለማቅረብ በቀን የሚያስፈልገው ገንዘብ ምን ያህል እንደሆነ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው ዶ/ር ግርማ፤ በነፍስ ወከፍ 50 ብር መሆኑን ገልጸዋል። 

ከተፈታኞች ቀለብ በተጨማሪ፤ የተማሪዎች፣ ፈታኞች፣ የፈተና ጣቢያ ኃላፊዎች እና የሱፐርቫይዘሮች ማጓጓዣ ወጪም በትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት አማካኝነት እንዲሸፈኑ የሚጠበቁ መሆናቸው በዛሬው የፓርላማ ውይይት ላይ ተጠቅሷል። የፌደራል መንግስት ለፈተናዎች አስፈጻሚ መስሪያ ቤቱ የያዘለት በጀት ግን እነዚህን ወጪዎች “የሚሸፍን እንዳልሆነ” ዶ/ር ግርማ በውይይቱ ላይ ለተገኙት የገንዘብ ሚኒስቴር ኃላፊዎች አስታውቀዋል። 

ከሶስት ሳምንት ገደማ በፊት ለተወካዮች ምክር ቤት በቀረበው በ2016 በጀት፤ ለትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት የተያዘው የገንዘብ መጠን 2.17 ቢሊዮን ብር ነው። የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት ጠይቆ የነበረው በጀት 2.65 ቢሊዮን ብር ገደማ እንደነበር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተናገሩት ዶ/ር ግርማ፤ በጀቱ ሲያዝ የ476 ሚሊዮን ብር ገደማ ቅናሽ መደረጉን አመልክተዋል።

ዶ/ር ግርማ በዛሬው የህዝብ ውይይት ላይም እርሳቸው በኃላፊነት የሚሰሩበት ተቋም፤ የበጀት ጉድለት እንደሚያጋጥመው በአጽንኦት ተናግረዋል። “እንደ ሌላው በሌላ ይሸፈናል የምንለው ነገር አይደለም። የአውሮፕላን [ጉዞ ወጪ] አይሸፈንም፣ የክፍያ አይሸፈንም፣ የተማሪ ምግብ አይሸፈንም። ከየትም ማጠጋጋት እንደማይቻል ታሳቢ ተደርጎ… እዚህም ምላሽ ባይሰጠው እንደ አግባቡ ትኩረት ቢሰጠው የሚል ሃሳብ አለኝ” ብለዋል። 

ይህን ጉዳይ በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስቴር የበጀት ጉዳዮች አማካሪ አቶ ተፈሪ ደመቀ፤ በዘንድሮው ዓመት የተጀመረው የ12ተኛ ክፍል ፈተና አሰጣጥ የሚያመጣው ውጤት “ጥሩ” ቢሆንም የሚያስከትለው ወጪ ግን “ውድ” (expensive) መሆኑን ተናግረዋል። አቶ ተፈሪ የፈተና አሰጣጡን ወጪ “ከፍተኛ” እንደሚያደርጉ ከጠቀሷቸው ጉዳዮች ውስጥ፤ ለፈተና አስፈጻሚዎች የሚውል “የሆቴል ወጪ” እና “60 በመቶ ጭማሪ ተደርጎ” ይፈጸማል ያሉት የአበል ክፍያ ይገኙበታል።

ከዚህ ቀደም የነበረው የፈተና አሰጣጥ የሚጠይቀው ወጪ ከ700 ሚሊዮን ብር የማይበልጥ እንደነበር በውይይቱ ላይ ያነሱት የገንዘብ ሚኒስቴር የበጀት ጉዳዮች አማካሪ፤ የአሁኑ አሰራር የሚያስወጣቸው ወጪዎች “በደንብ መታየት አለበት” በሚል ንግግር እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል። የተማሪዎች ቀለብን በተመለከተ ግን ዩኒቨርስቲዎች የሚመድቡት 22 ብር “አሁን ካለው ዋጋ አኳያ በጣም አስቸጋሪ” እንደሚሆን የገንዘብ ሚኒስቴር እንደሚረዳ አቶ ተፈሪ ተናግረዋል።  

ይሁንና በዚህ ጉዳይ ላይ ማሻሻያ ለማድረግ “ተጠንቶ፣ መንግስት ጋር ቀርቦ ውሳኔ ማለፍ አለበት። ያ ባልተወሰነበት ሁኔታ እኛ በጀት ልንመልስ አንችልም” ሲሉ የገንዘብ ሚኒስቴር በተናጠል መወሰን እንደማይችል አስታውቀዋል። ከፈተና አሰጣጡ ጋር የተያያዙ ሌሎች ጉዳዮችም በተመሳሳይ “የመንግስትን ውሳኔ የሚጠይቁ” መሆናቸውን አስገንዝበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)