በተሰናባቹ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ስራ አስፈጻሚ ምትክ አዲስ ኃላፊ ተሾመ 

ሳፋሪኮም በኢትዮጵያ ለሚገኘው ኩባንያው ቤልጅየማዊውን ዊም ቫንሔለፑትን አዲስ ዋና ስራ አስፈጻሚ አድርጎ ሾመ። ላለፉት ሁለት ዓመታት ሳፋሪኮም ኢትዮጵያን የመሩት አንዋር ሶሳን የሚተኩት አዲሱ ስራ አስፈጻሚ፤ ከነሐሴ 26፤ 2015 ጀምሮ መሾማቸውን መቀመጫውን በናይሮቢ ያደረገው ሳፋሪኮም አስታውቋል።

አዲሱ የሳፋሪኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት የቴሌኮም ገበያ ከ25 ዓመታት በላይ የስራ ልምድ እንዳላቸው  ኩባንያው ዛሬ ሹመታቸውን ይፋ ሲያደርግ ገልጿል። ዊም ቫንሔለፑት ሳፋሪኮም ኢትዮጵያን የተቀላቀሉት ሌላኛውን ግዙፍ የቴሌኮም ኩባንያ ኤምቲኤን ግሩፕን በመልቀቅ ነው። 

ዊም በኤምቲኤን ውስጥ የገበያዎች ኦፕሬሽን ስራ አስፈጻሚ የነበሩት ቫንሔለፑት፤ በምዕራብ እና መካከለኛው አፍሪካ የሚገኙ አራት ኩባንያዎችን የስራ አፈጻጸም እና አስተዳደር የመምራት ኃላፊነት ሲወጡ ቆይተዋል ተብሏል። አዲሱ ተሿሚ በኡጋንዳ እና በኮትዲቯር የኤምቲኤን ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው የሰሩ ሲሆን በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ሴኔጋል፣ ቻድ እና ጋቦን የሚገኙ የቴሌኮም ኩባንያዎችን ደግሞ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች መምራታቸውን ሳፋሪኮም በዛሬው ዕለት ያወጣው መግለጫ ይጠቁማል።

የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አንዋር ሶሳ በመጪው ሐምሌ ከኃላፊነታቸው እንደሚለቅቁ ኩባንያው ባለፈው ሳምንት አስታውቆ ነበር። አንዋር ሶሳ ከኃላፊነታቸው የሚሰናበቱት፤ በኢትዮጵያ እንዲሰሩ የተመደቡበት የዝውውር ጊዜ በመጠናቀቁ መሆኑን ሳፋሪኮም በወቅቱ አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)