ለመንግስት ተመላሽ መደረግ ከነበረበት 7 ቢሊዮን ብር ገደማ ውስጥ የተሰበሰበው ከ1 በመቶ በታች መሆኑን የፌደራል ዋና ኦዲተር አስታወቀ

በአማኑኤል ይልቃል

በ2013 በጀት ዓመት እና ከዚያ በፊት በተደረገ ኦዲት ተመላሽ እንዲደረግ አስተያየት ከተሰጠበት 6.88 ቢሊዮን ብር ውስጥ ተመላሽ የተደረገው 0.65 በመቶው መሆኑን የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት አስታወቀ። ይህ የገንዘብ መጠን ባለፈው ዓመት ተመላሽ ከተደረገው ጋር ሲነጻጸርም “በጣም ዝቅተኛ” መሆኑን መስሪያ ቤቱ ገልጿል። 

የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ይህንን ያስታወቀው የፌደራል መንግስት መስሪያ ቤቶችን የ2014 በጀት ዓመት የፋይናንስ ህጋዊነት እና ክዋኔ ኦዲት ሪፖርትን ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 20፤ 2015 ለተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት መደበኛ ስብሰባ ላይ ነው። የመስሪያ ቤቱን ሪፖርት ለፓርላማ አባላት ያቀረቡት ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ፤ ተቋማቸው በ2013 በጀት ዓመት እና ከዚያ በፊት ባከናወናቸው የኦዲት ሪፖርቶች ላይ የታዩ ጉድለቶች ላይ እርምጃ የተወሰደ መሆኑን ለማረጋገጥ ማጣራት ማካሄዱን ተናግረዋል። 

እንደ ዋና ኦዲተሯ ገለጻ መስሪያ ቤቱ በ2013 በጀት ዓመት፤ 86 የመንግስት መስሪያ ቤቶች 6.88 ቢሊዮን ብር “ተመላሽ” እንዲያደርጉ አስተያየት ተሰጥቷቸዋል። በዚህ አስተያየት መሰረት የተወሰደውን ማስተካከያ ያጣራው የፌደራል ዋና ኦዲተር፤ መስሪያ ቤቶቹ ያስመለሱት የገንዘብ መጠን 44.99 ሚሊዮን ብር ሆኖ ማግኘቱን ወ/ሮ መሰረት ለምክር ቤቱ አስታውቀዋል። 

“ይህ አፈጻጸም ተመላሽ ሊደረግ ከሚገባው ሂሳብ ጋር ሲነጻጸር በመቶኛ 0.65 በመቶ ብቻ ሲሆን ቀሪው 6,838,559,886 [ብር] ተገቢው እርምጃ ያልተወሰደበት እና ተመላሽ ያልተደረገ መሆኑ ታውቋል” ሲሉ በንግግራቸው ላይ ጠቅሰዋል። ባለፈው የበጀት ዓመት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ተሰብስቦ እንደነበር የተናገሩት ወ/ሮ መሰረት፤ “ዘንድሮ ግን በጣም ዝቅተኛ ነው። እኔም ራሴ ሳየው በጣም ነው የደነገጥኩት” ሲሉ ይህ የገንዘብ መጠን ያልተጠበቀ መሆኑን አመልክተዋል። 

ተመላሽ እንዲደረግ አስተያየት ከተሰጠበት ገንዘብ ውስጥ የተመለሰው የብር መጠን ቅናሽ እንዳሳየው ሁሉ፤ የፌደራል መንግስት መስሪያ ቤቶች ያልሰበሰቡት ውዝፍ ሂሳብ ደግሞ እንደጨመረ ዋና ኦዲተሯ ተናግረዋል። የኦዲተር መስሪያ ቤቱ ሪፖርት እንደሚያሳየው የ2014 በጀት ዓመት የፋይናንስ ህጋዊነት እና ክዋኔ ኦዲት በተከናወነባቸው 131 የፌደራል መስሪያ ቤቶች ውስጥ፤ 15.12 ቢሊዮን ብር “በወቅቱ ያልተወራረደ (ያልተሰበሰበ)” ሂሳብ እንዳለ ታውቋል። 

ይህ የገንዘብ መጠን ባለፈው በጀት ዓመት ዘጠኝ ቢሊዮን ብር እንደነበር የጠቀሱት ዋና ኦዲተሯ፤ የዘንድሮው “በጣም ከፍተኛ” መሆኑን አስረድተዋል። ይህ ሂሳብ እንደተገኘባቸው ከተጠቀሱ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ከፍተኛ ያልተሰበሰበ ገንዘብ ያለው በጤና ሚኒስቴር መሆኑ በኦዲት ሪፖርት ላይ ሰፍሯል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ 4.5 ቢሊዮን ብር ውዝፍ ተሳብሳቢ ሂሳብ እንዳለው ሪፖርቱ አመልክቷል።

መሰብሰብ ያለበት 2.83 ቢሊዮን ብር ውዝፍ ገንዘብ እንዳለው የተጠቀሰው የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር፤ ሌላው ከፍተኛ ተሰብሳቢ ሂሳብ ያለው የመንግስት ተቋም መሆኑ በዓመታዊው ሪፖርት ላይ ተቀምጧል። ይህ ውዝፍ ሂሳብ “ከዓመት ወደ ዓመት ሳይወራረድ” የሚቆይ ከሆነ “የመንግስትን ገንዘብ ለብክነት እና ለጥፋት ሊዳርግ” እንደሚችል ዋና ኦዲተሯ በሪፖርታቸው ላይ ጠቅሰዋል። 

የፌደራል ዋና ኦዲተር፤ የመንግስት መስሪያ ቤቶች “የቅድሚያ ሂሳቦችን እንዲያወራርዱ” እና “መሰብሰብ የማይችሉትን አጣርተው እርምጃ እንዲወስዱ” ማሳሰቡን ወ/ሮ መሰረት አክለዋል። የተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች፤ የሚከታተሏቸውን መስሪያ ቤቶች የኦዲት ሪፖርቶች ተቀብለው አፈጻጸማቸውን እንዲከታተሉም ዋና ኦዲተሯ ጥሪ አቅርበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)