የኢትዮጵያ የ11 ወራት የወጪ ንግድ አፈጻጸም የ12 በመቶ ገደማ ቅናሽ አስመዘገበ  

በአማኑኤል ይልቃል

የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ (export) ባለፈው 11 ወራት የነበረው አፈጻጸም፤ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ11.8 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ። በዚህ ጊዜ ውስጥ ከወጪ ንግድ ለማስገባት ታቅዶ ከነበረው የገንዘብ መጠን ውስጥ፤ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ያህሉን ማግኘት እንዳልተቻለም መስሪያ ቤቱ ገልጿል። 

ባለፈው ጥር ወር ላይ 6.9 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱ ተገልጾ የነበረው የሀገሪቱ የወጪ ንግድ አፈጻጸም ጉድለት፤ ይበልጥኑ ከፍ እያለ መምጣቱ የተነገረው ዛሬ አርብ ሰኔ 23፤ 2015 በፓርላማ በተካሄደ የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ነው። በተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የዛሬውን ስብሰባ የጠራው፤ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርን የ11 ወራት የእቅድ አፈጻጸም ለመገመገም ነበር። 

የሚኒስቴሩን የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ለፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ ያቀረቡት፤ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስትራቴጂክ ጉዳዮች ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ኡርጌሳ ባይሳ ናቸው። በ11 ወራት ውስጥ ከወጪ ንግድ ለማግኘት ታቅዶ ከነበረው 4.74 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ፤ 3.24 ቢሊየን ዶላር ያህል ማግኘት መቻሉን ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል። 

ፎቶ፦ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀጥታ ስርጭት የተወሰደ

ኢትዮጵያ ከወጪ ንግድ ካስገባችው ገቢ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው፤ ከግብርና ምርቶች ሽያጭ የተገኘው እንደሆነ በሚኒስቴሩ ሪፖርት ተጠቅሷል። ኢትዮጵያ ከግብርና ምርቶች የወጪ ንግድ ያስገባቸው ገቢ 2.55 ቢሊዮን ዶላር መሆኑም በሪፖርቱ ሰፍሯል። ባስገኙት ገቢ መጠን በሪፖርቱ የሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ የያዙት የማዕድን እና የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች ናቸው።

ዛሬ ለፓርላማ የቀረበው ሪፖርት፤ በንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ክትትል ከሚደረግባቸው ሰባት የወጪ ንግድ ምርቶች ውስጥ ስድስቱ የገቢ ቅናሽ ማስመዝገባቸውንም አመልክቷል። ከእነዚህ የምርት አይነቶች በገቢ ረገድ ከእቅድ በላይ ማሳካት የቻለው፤ የጥራጥሬ ሰብሎች ወጪ ንግድ ብቻ ነው። ለወራት የዘለቀ ቅናሽ የታየበት የወጪ ንግድ አፈጻጸም፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ከሚገመግመው የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጥያቄ አስነስቷል።

ቋሚ ኮሚቴው ያዘጋጃቸውን ጥያቄዎች በንባብ ያቀረቡት አቶ አስቻለው አላምሬ የተባሉ የፓርላማ አባል፤ ከወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ የቀነሰበት ምክንያት ምን እንደሆነ ጠይቀዋል። “ባለፈው ዓመት በጦርነት እና በተለያዩ ጫናዎች ውስጥ ሆነን ካስገኘነው ገቢ በ11.8 በመቶ ቀንሷል። ችግሩ ምንድነው?” ሲሉ የሚኒስቴሩ አመራሮች ማብራሪያ እንዲሰጡበት ጥያቄ አቅርበዋል። 

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ፤ በስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ወቅት የተነሱ ምክንያቶችን በመጥቀስ ተመሳሳይነት ያላቸው ችግሮች አሁንም የወጭ ንግዱን እየፈተኑ መሆናቸውን አመልክተዋል። የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የስድስት ወራት አፈጻጸም በጥር ወር ላይ ለፓርላማ በቀረበበት ወቅት፤ በግማሽ ዓመቱ ከወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ 1.7 ቢሊዮን ዶላር መሆኑ ተገልጾ ነበር። ይህ የወጪ ንግድ አፈጻጸም፤ በመንፈቅ ዓመት ውስጥ ይገኛል ተብሎ ታቅዶ ከነበረው ገቢ ጋር ሲነጻጸር የ26 በመቶ ገደማ ቅናሽ ያለው ነበር።

ለስድስት ወራት ከታቀደውም ሆነ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ከነበረው ገቢ ሲነጻጸር ቅናሽ ላሳየው የወጪ ንግድ አፈጻጸም በወቅቱ የተነሱ ምክንያቶች፤ “የቅባት እህሎች ምርት እጥረት እና የዓለም ገበያ መዋዠቅ” የሚሉ ነበሩ። በዛሬው የግምገማ መድረክ አቶ ካሳሁን ጎፌ፤ ኮንትሮባንድን በተመለከተ “ሰፊ ትንቅንቅ ውስጥ ነው ያለነው” ሲሉ ችግሩ አሁንም መቀጠሉን ጠቅሰዋል። ይህ ችግር በቁም እንስሳት ንግድ በተለይም በወርቅ ምርት ላይ መታየቱን ሚኒስትር ዴኤታው አንስተዋል። 

“የማዕድን ምርቶች ለሀገር አቀፍ ኤክስፖርት የነበራቸው ድርሻ ከ12፣ 13 ፐርሰንት ወደ ስድስት ፐርሰንት የወረደበትን ሁኔታ ማየት ይቻላል” ሲሉ አቶ ካሳሁን ችግሩን በቁጥር አስደግፈው አስረድተዋል። ሚኒስትር ዴኤታው በወጪ ንግድ ተግዳሮትነት የጠቀሱት ሌላኛው ጉዳይ፤ በዋጋ ንረት ምክንያት በዓለም ኢኮኖሚ እየተፈጠረ ነው ያሉትን “ቀውስ” ነው። “የቡና ታላላቅ ገዢዎች ናቸው ተብለው የሚታወቁት ጀርመን እና ቤልጂየም፤ የዘንድሮ ግዢ ፍላጎት በ43 ፐርሰንት ቀንሰዋል። ምክንያቱም እነሱም ጋር የኑሮ ውድነት አለ” ሲሉ የአውሮፓ ሀገራቱን የኢኮኖሚ ሁኔታ በማሳያነት አንስተዋል።  

ከዓለም አቀፍ ሁኔታ ባሻገር ሀገራዊ ሁኔታዎችም በወጪ ንግድ ለታየው ቅናሽ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ሚኒስትር ዴኤታው አክለዋል። በጫት ምርት ላይ በተለያዩ ክልሎች ተደጋጋሚ ቀረጥ በመጣሉ ምክንያት፤ ከጫት የወጪ ንግድ ሊገኝ ታቅዶ የነበረው 228 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ገቢ መታጣቱን አቶ ካሳሁን ለፓርላማ አባላቱ ተናግረዋል። “በአንድ ኪሎ እስከ 63 እስከ 64 ብር ቀረጥ በመጣሉ ምክንያት ጫቱ ተሽጦ ገቢ ማግኘት አልተቻለም” ሲሉም በጫት ላይ የሚጣለው ተደራራቢ ቀረጥ አሁንም ችግር ሆኖ መቀጠሉን ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)