በሃሚድ አወል
የፌደሬሽን ምክር ቤት በመጪው ሳምንት ማክሰኞ እና ረቡዕ በሚያደርገው መደበኛ ስብሰባው፤ “ደቡብ ኢትዮጵያ” የሚል ስያሜ የተሰጠውን ክልል ለመመስረት የተካሄደውን ህዝበ ውሳኔ ውጤት እንደሚያጸድቅ የምክር ቤቱ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ የህዝበ ውሳኔውን አጠቃላይ ሪፖርት ከነገ በስቲያ ሰኞ ሰኔ 26፤ 2015 ለፌደሬሽን ምክር ቤት በጹሁፍ ያቀርባል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት፤ ከማንነት እና ራስን በራስ ከማስተዳደር ጋር በተያያዙ የሚነሱ ጥያቄዎችን የመመልከት ስልጣን የሰጠው ለፌደሬሽን ምክር ቤት ነው። የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ስልጣን እና ተግባር ለመዘርዘር የወጣው አዋጅ፤ ምክር ቤቱ የህዝብ ፍላጎትን በህዝበ ውሳኔ እንዲረጋገጥ የማድረግ ኃላፊነትንም ሰጥቶታል።
በነባሩ የደቡብ ክልል ስር የሚገኙ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች በጋራ የራሳቸውን ክልል ለመመስረት ያቀረቡትን ጥያቄ በአዋጁ መሰረት የተቀበለው ምክር ቤቱ፤ በእነዚህ መዋቅሮች ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ባካሄደው ስብሰባ በአብላጫ ድምጽ ወስኖ ነበር። በዚሁ ስብሰባ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ህዝበ ውሳኔ እንዲያደራጅም ውሳኔ ተላልፏል።
ይህን ውሳኔ መሰረት በማድረግ፤ ምርጫ ቦርድ በአስራ አንዱ የደቡብ ክልል መዋቅሮች ጥር 29፤ 2015 ህዝበ ውሳኔ አካሄዷል። ህዝበ ውሳኔው ከተካሄደባቸው መዋቅሮች ውስጥ፤ የአምስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ውጤት በቦርዱ ተረጋግጦ ይፋ ተደርጓል። የህዝበ ውሳኔው ውጤት፤ የጋሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ እና ጌዲኦ ዞኖች እንዲሁም የደራሼ፣ ቡርጂ፣ አሌ፣ አማሮ እና ባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች፤ ከነባሩ ደቡብ ክልል ወጥተው አንድ የጋራ ክልል ለመመስረት ይሁንታቸውን መስጠታቸውን ያሳየ ሆኗል።
ህዝበ ውሳኔው በተካሄደበት ዕለት እና በመራጮች ምዝገባ ወቅት ተፈጽመዋል በተባሉ “መጠነ ሰፊ ጥሰቶች” ሳቢያ ግን በወላይታ ዞን የተደረገው ህዝበ ውሳኔ ውጤት ውድቅ መደረጉን ምርጫ ቦርድ በወቅቱ አስታውቋል። በዚህ ምክንያትም በዞኑ የተደረገው ህዝበ ውሳኔ፤ ሰኔ 12፤ 2015 በድጋሚ እንዲካሄድ ተደርጓል። ከሁለት ሳምንት በፊት በድጋሚ በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ፤ አዲስ የጋራ ክልል ለመመስረት የቀረበው አማራጭ አብላጫ ድምጽ ማግኘቱን ምርጫ ቦርድ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ይፋ አድርጓል።
በምርጫ ቦርድ የተከናወነውን ህዝበ ውሳኔ ውጤት የማጽደቅ ኃላፊነት በአዋጅ የተሰጠው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው። በመጪው ማክሰኞ ሰኔ 27፤ 2015 ከሰዓት በኋላ ተጀምሮ በማግስቱ በሚቀጥለው የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ፤ ምርጫ ቦርድ “የደቡብ ኢትዮጵያ” ክልል ህዝበ ውሳኔ ሪፖርትን በንባብ እንዲያቀርብ ቀጠሮ መያዙን የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች ተናግረዋል። በሁለቱ ቀናት ስብሰባም የህዝበ ውሳኔው ውጤት፤ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት እንደሚጸድቅ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሌላ ምንጭ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል።
የፌደሬሽን ምክር ቤት ተመሳሳይ የህዝበ ውሳኔን ውጤት ለማጽደቅ፤ ከዚህ ቀደም ስብሰባ ያካሄደው ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ነበር። ምክር ቤቱ በዚሁ ስብሰባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን ለመመስረት የተካሄደውን የህዝበ ውሳኔ ውጤት ማጽደቁ ይታወሳል። ፌዴሬሽኑን በመቀላቀል 11ኛ የሆነው ይህ ክልል የተመሰረተው፤ በተመሳሳይ መልኩ በነባሩ ደቡብ ክልል ስር የነበሩ አምስት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ የራሳቸውን ክልል መመስረት የሚያስችላቸውን ህዝበ ውሳኔ በመስከረም 2014 ካካሄዱ በኋላ ነበር።
ሁለት ዓመት ቀደም ብሎ በህዳር 2012 በተካሄደ ህዝበ ውሳኔ፤ በነባሩ የደቡብ ክልል ስር የነበረው የሲዳማ ዞንም እንዲሁ በህዝበ ውሳኔ አማካኝነት ፌዴሬሽኑን የተቀላቀለ 10ኛ ክልል ሆኗል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከቀናት በኋላ በሚያካሄደው ስብሰባው ያጸድቀዋል ተብሎ በሚጠበቀው ህዝበ ውሳኔ ውጤት መሰረት ደግሞ፤ “ደቡብ ኢትዮጵያ” የሚል ስያሜ የሚኖረው 12ኛ ክልል የፌዴሬሽኑ አካል ይሆናል።
ከዚህ ስብሰባ በኋላ “ደቡብ ኢትዮጵያ” በክልልነት ለመታወቅ የሚቀረው ሂደት፤ ከነባሩ የደቡብ ክልል የሚደረገው ይፋዊ የስልጣን ርክክብ ነው። በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት መሰረት በዚህ መልኩ የሚመሰረት አዲስ ክልል፤ ጥያቄ ማቅረብ ሳያስፈልገው በቀጥታ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አባል ይሆናል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)