በአማኑኤል ይልቃል
በአማራ ክልል፣ ምስራቅ ጎጃም ዞን የምትገኘው የደጀን ወረዳ ፖሊስ አዛዥ እና ምክትላቸው በተከፈተባቸው ተኩስ ሲገደሉ ሁለት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የወረዳው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታወቀ። ለወረዳዋ ፖሊስ አዛዦች ህልፈት ምክንያት የሆነውን ተኩስ ከፍቷል የተባለ ተጠርጣሪን ለመያዝ ፍለጋ እየተከናወነ መሆኑንም ጽህፈት ቤቱ ገልጿል።
የደጀን ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ዘውዱ ታደለ እና ምክትላቸው ኢንስፔክተር ወርቁ ሽመልስ ጥቃት የተፈጸመባቸው ዛሬ ሰኞ ሰኔ 26፤ 2015 ከቀኑ ስምንት ሰዓት ገደማ እንደሆነ የወረዳው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታሁን ጋሻዬ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የፖሊስ አዛዦቹ ላይ ተኩስ የተከፈተባቸው፤ በዛሬው ዕለት በተለያዩ አካባቢዎች እየተሰጠ ያለውን “የስምንተኛ ክፍል ፈተና ደህንነት ለመከታተል ወደ አባይ ሸለቆ ትምህርት ቤት በመኪና እየተጓዙ በነበረበት ወቅት” መሆኑን የኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊው አስረድተዋል።
ሁለቱ የፖሊስ አዛዦች “ግልገሌ” የተባለች ቀበሌ ላይ ሲደርሱ “መንገድ ላይ ሲጠብቃቸው ነበር” በተባለ ግለሰብ ተኩስ እንደተከፈተባቸው አቶ ጌታሁን ተናግረዋል። በዚህ ጥቃት በጥይት የተመቱት የፖሊስ አዛዡ ኢንስፔክተር ዘውዱ እና ምክትላቸው ኢንስፔክተር ወርቁ ወዲያው ህይወታቸው ሲያልፍ፤ ሹፌራቸው “እግሩ ላይ ተመትቶ” ጉዳት እንደደረሰበት ኃላፊው አክለዋል።
ጥቃቱን የፈጸመው ግለሰብ፤ ከአዲስ አበባ በመነሳት ወደ ደጀን ከተማ ሲጓዝ የነበረን “ገልባጭ” መኪና በማስቆም ከአካባቢው ማምለጡን አቶ ጌታሁን ገልጸዋል። “ከፍ ብሎ ኪዳነ ምህረት የሚባል [አካባቢ] አለ። እዚያ ሲደርስ ወርዶ የገልባጩን ሹፌር ደግሞ መታው” ሲሉም ጥቃት ፈጻሚው ግለሰብ ሁለተኛ ሰው “እግሩ ላይ” በጥይት መትቶ ማቁሰሉን አብራርተዋል። የጸጥታ ኃይሎች ጥቃት ያደረሰውን ግለሰብ ለመያዝ መሰማራታቸውን ጠቁመዋል።
በዛሬው ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸው ሁለቱ ሹፌሮች ወደ “ደጀን የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል” ተወስደው በህክምና ላይ እንደሚገኙ የገለጹት አቶ ጌታሁን፤ ህይወታቸው ያለፈው የፖሊስ አዛዦች አስከሬን ደግሞ ምርመራ ተደርጎ ወደ የቤተሰቦቻቸው መሸኘቱን አመልክተዋል። አንድ የደጀን ከተማ ነዋሪ፤ የሁለቱ የፖሊስ አዛዦች አስከሬን “ከጤና ጣቢያ” ሲወጣ እንደተመለከቱ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የአይን እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።
የዛሬውን ጥቃት በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የደጀን ወረዳ ሚሊሺያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ካሳው አስፋው፤ “ይሄ የግለሰብ ጉዳይ ነው” በሚል ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)