የመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ጭማሪ “ለወደፊት በሂደት የሚታይ” መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አስታወቁ 

በአማኑኤል ይልቃል

የመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ጭማሪ “ለወደፊት በሂደት የሚታይ” መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 27፤ 2015 በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ተናገሩ። መንግስት የደመወዝ ጭማሪን “ወደፊት የሚያየው”፤ ሊተገብር ካሰበው “የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም” ጋር በተያያዘ መሆኑንም አቶ አህመድ ገልጸዋል። 

የገንዘብ ሚኒስትሩ ዛሬ በፓርላማ የተገኙት፤ የፌደራል መንግስት ባቀረበው የ2016 በጀት ረቂቅ ሰነድ ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ነበር።  በዚህም መሰረት ሚኒስትሩ ከፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም ከሌሎች የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል። 

ከፓርላማ አባላት የተነሱ አብዛኛዎቹ ጥያቄዎች፤ የቀጣዩ ዓመት በጀት ረቂቅ ለምክር ቤቱ ከቀረበበት ጊዜ አንስቶ በተደጋጋሚ ሲነሱ ከነበሩት ከካፒታል በጀት መቀነስ፣ ከመንገድ ፕሮጀክቶች በጀት ማነስ እንዲሁም ለክልሎች ከሚደረግ የፌደራል መንግስት ድጎማ ጋር የተያያዙ ናቸው። በአባላቱ የተዘጋጀውን እና ከህዝብ የተቀበላቸውን ጥያቄዎች ለገንዘብ ሚኒስትሩ ያቀረበው የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአንጻሩ፤ የመንግስት ሰራተኞችን ደመወዝ ጭማሪ ጉዳይ አንስቷል። 

የቋሚ ኮሚቴውን ጥያቄዎች በንባብ ያቀረቡት ዶ/ር ሚልኪያስ አየለ የተባሉ የምክር ቤት አባል፤ “ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ” ያለው የዋጋ ግሽበት “ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የከተማ ነዋሪ እና የመንግስት ሰራተኛውን በእጅጉ እየጎዳ” መሆኑን በጥያቄያቸው ላይ ጠቅሰዋል። “እነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች የበለጠ እንዳይጎዱ” ሲባል በቀጣዩ ዓመት በጀት ድልድል የታቀደ ነገር መኖሩን የጠየቁት ዶ/ር ሚልኪያስ፤ “ደመወዝ ጭማሪ ለማድረግ እና ሌሎች አማራጮችን ለመውሰድ ምን ታስቧል?” ሲሉ ተጨማሪ ጥያቄ ሰንዝረዋል። 

የፓርላማ አባሉ ከህዝብ የቀረቡ ጥያቄዎችን በንባብ ሲያቀርቡም፤ የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ ጭማሪ ጉዳይን በድጋሚ አንስተዋል። ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ፤ የ2016 በጀት እና “የማክሮ ኢኮኖሚ fiscal framework” የዋጋ ንረትን “ለማርገብ” ዓላማ ያለው መሆኑን አስረድተዋል። የዋጋ ግሽበት እንዳይንር በቀጣዩ በጀት ዓመት ሊወሰዱ ከታሰቡ እርምጃዎች ውስጥ የበጀት ጉድለትን እንዲጠብ እንዲሁም የሚኖረውን የበጀት ጉድለት “በገበያው ውስጥ ከተፈጠረ ቁጠባ እንዲሞላ” መታቀዱን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

“የዋጋ መረጋጋት እንዲኖር በተወሰነ ደረጃ ዘይት ላይ እያደረግን ያለነው ኢንቨስትመንት አለ። የስንዴ ምርት በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ እየተደረገ ያለው ስራ ውጤታማ ከመሆኑ አንጻር ይህ በግብርና ምርት መረጋጋት ላይ ተጨማሪ ውጤት ያመጣል የሚል ሀሳብ አለ” ሲሉም የዋጋ ንረትን ከማረጋጋት አንጻር ተስፋ የተጣለባቸውን ጉዳዮች አንስተዋል። ይህም ቢሆን ግን የመንግስት ሰራተኛው በዋጋ ንረት “ተጎጂ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር [የለውም]” ሲሉ በጥያቄው የቀረበው ችግር በእርግጥም ያለ መሆኑን ተቀብለዋል።   

ገቢያቸው ቋሚ የሆነ የማህበረሰብ ክፍሎች በዋጋ ንረት ምክንያት የሚፈጠርባቸውን ጫና መንግስት እንደሚረዳም የገንዘብ ሚኒስትሩ ለፓርላማ  አባላቱ አስገንዝበዋል። ከመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ ጋር በተያያዘ መንግስት “የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም” ለማካሄድ በሂደት ላይ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አህመድ፤ በአሁኑ ወቅትም የሪፎርሙ “ዲዛይን” ተሰርቶ መጠናቀቁን አስታውቀዋል። የተለያዩ ዓላማዎችን ለማሳካት የሚተገበረው ሪፎርም የሚመራበት “የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ፖሊሲ” በቅርቡ እንደሚጸድቅም ሚኒስትሩ አክለዋል። 

ይህ “የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም” የመንግስት “አደረጃጀቶችን መልሶ መፈተሽ” እና “የመስሪያ ቤቶቹን አሰራር በከፍተኛ ደረጃ ለማዘመን” ያለመ መሆኑን አቶ አህመድ ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት አስረድተዋል። በዚህ ሪፎርም “በተወሰነ ሰራተኛ maximum ውጤት የሚመጣበትን አካሄድ” ለመፍጠር መታሰቡንም ተናግረዋል። በዚህ ምክንያት “ከደመወዝ ጋር የተገናኘ ጉዳይ ለወደፊት በሂደት የሚታይ ነው የሚሆነው” ያሉት የገንዘብ ሚኒስትሩ፤ “በዋነኛነት እነዚህ ጉዳዮች በተሟላ መልኩ ከተሰሩ በኋላ የሚታይ ይሆናል” ሲሉ በቅድሚያ “የሪፎርም ስራው” መጠናቀቅ እንዳለበት ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)