የፌዴሬሽን ምክር ቤት “የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” የኢፌዲሪ 12ኛ ክልል ሆኖ እንዲደራጅ በሙሉ ድምጽ ወሰነ። የነባሩ የደቡብ ክልል፤ በህዝበ ውሳኔ መሰረት ለሚመሰረተው ለአዲሱ ክልል የስልጣን ርክክብ እንዲያደርግ እና ሂደቱንም እንዲያስፈጽም ምክር ቤቱ ዛሬ ረቡዕ ሰኔ 28፤ 2015 ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ ውሳኔ አሳልፏል። በነባሩ ክልል የቀሩ መዋቅሮች፤ ራሳቸውን መልሰው በማደራጀት ባሉበት እንዲቀጥሉም ውሳኔ ተላልፏል።
በዛሬው ዕለት በፌዴሬሽን ምክር ቤት በጸደቀው የህዝበ ውሳኔ ውጤት መሰረት አዲስ ክልል በጋራ የሚያቋቋሙት፤ በነባሩ የደቡብ ክልል የሚገኙት የጌዲኦ፣ የወላይታ፣ የጋሞ፣ ጎፋ፣ የኮንሶ፣ የደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም የቡርጂ፣ የአማሮ፣ የደራሼ፣ የባስኬቶ እና የአሌ ልዩ ወረዳዎች ናቸው። እነዚህ መዋቅሮች በየምክር ቤቶቻቸው ባደረጉት ስብሰባ ያሳለፉትን በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ፤ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀረቡት ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ነበር።
የመዋቅሮቹን ጥያቄ በወቅቱ ባካሄደው ጉባኤ በአብላጫ ድምጽ ያጸደቀው የፌዴሬሽን ምክር ቤት፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ህዝበ ውሳኔ እንዲያደራጅ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል። በዚህ ውሳኔ መሰረት ምርጫ ቦርድ በአስራ አንዱም የነባሩ የደቡብ ክልል መዋቅሮች ባለፈው ጥር ወር ህዝበ ውሳኔ አካሄዷል። ምርጫ ቦርድ በወቅቱ ይፋ ባደረገው የተረጋገጠ የህዝበ ውሳኔ ውጤት፤ ከወላይታ ዞን ውጭ ያሉት መዋቅሮች ከነባሩ ደቡብ ክልል ወጥተው አንድ የጋራ ክልል ለመመስረት ይሁንታቸውን ሰጥተዋል።
በመራጮች ምዝገባ እና በድምጽ መስጪያ ዕለት ተፈጽመዋል በተባሉ “መጠነ ሰፊ ጥሰቶች” ምክንያት ሰኔ 12፤ 2015 በወላይታ ዞን በድጋሚ እንዲካሄድ በተደረገው ህዝበ ውሳኔም፤ ተመሳሳይ ውጤት መመዝገቡን ምርጫ ቦርድ ከሁለት ሳምንት በፊት ማስታወቁ አይዘነጋም። የምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ በዛሬው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ተገኝተው፤ አጠቃላይ የህዝበ ውሳኔውን ሪፖርት አቅርበዋል።
በዚህ ሪፖርት ላይ በመንተራስ የአዲሱን ክልል ማደራጀት የያዘ የውሳኔ ሃሳብ፤ በምክር ቤቱ የማንነት፣ የአስተዳደር ወሰንና የሰላም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ ቀርቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ ይታከልበታል]