የፌደራል መንግስት፤ ለአዲስ ቤተ መንግስት ግንባታ “ያቀረበው የበጀት ጥያቄ” እንደሌለ የገንዘብ ሚኒስትሩ ገለጹ 

በአማኑኤል ይልቃል

የፌደራል መንግስት “ለአዲስ ቤተ መንግስት ግንባታ ያቀረበው የበጀት ጥያቄም ሆነ እያጸደቀ ያለው በጀት አለመኖሩን” የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ገለጹ። መንግስት እንደ “ገበታ ለሀገር” ያሉ ፕሮጀክቶችን የሚገነባው፤ ህጋዊ አሰራርን ተከትሎ መሆኑንም የገንዘብ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። 

አቶ አህመድ ይህንን የተናገሩ ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 27፤ 2015 በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ነው። በዚሁ ስብሰባ፤ የፌደራል መንግስት ያቀረበውን የ2016 በጀት በተመለከተ ከምክር ቤቱ የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም ከሌሎች የምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች የገንዘብ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዛሬው ስብሰባ ከተነሱ ጥያቄዎች ውስጥ “ለቤተመንግስት እና ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክቶች “እየተሰበሰበ ነው” የተባለን “500 ቢሊዮን ብር” የተመለከተው ይገኝበታል። ይህንን ጥያቄ ያነሱት የተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አባል የሆኑት አቶ አበባው ደሳለው፤ የገንዘብ አሰባሰቡ “የመንግስትን አሰራር እና መመሪያ” ተከትሎ እየተፈጸመ ስለመሆኑ ጥያቄ አቅርበዋል። እኚሁ የፓርላማ አባል፤ “ይህ ብር የመንግስት ቋት ውስጥ አለ ወይ?” ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትሩ ማብራሪያ እንዲሰጡም ጠይቀዋል።

የምክር ቤት አባሉ አክለውም “ይህንን አይነት በግለሰቦች የሚሰበሰብ ገንዘብን ምን ያህል የህግ አሰራር ይደግፋል? የጥቅም ግጭት አያስነሳም ወይ?”  ሲሉ ተጨማሪ ጥያቄ ሰንዝረዋል። ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ፤ የፌደራል መንግስት “ለአዲስ ቤተ መንግስት ግንባታ” በሚል የበጀት ጥያቄ ለፓርላማው አለማቅረቡን ለምክር ቤቱ አባላት አስገንዝበዋል።

“የጫካ ፕሮጀክት” የሚባለው ፕሮጀክት “ብዙ የልማት ስራዎች በጋራ [እንዲከናወኑ] የታቀደበት” መሆኑን የጠቀሱት አቶ አህመድ፤ እርሱም ቢሆን “በበጀት የሚሰራ አለመሆኑን” ተናግረዋል። “በዚህ ፓርላማ ያልጸደቀ በጀትም ተግባራዊ አይሆንም። ታውቃላችሁ፤ ህጉ እንደዚያ ነው የሚለው። ስለዚህ ለቤተ መንግስት ግንባታ የተጠየቀ በጀትም የለም፤ እየጸደቀ ያለ በጀትም የለም” ሲሉ ለዚህ ፕሮጀክት የሚውል “የፐብሊክ ፋይናንስ” አለመኖሩን አስረድተዋል። 

“የገበታ ለሀገር” ፓርክ ግንባታዎችም “የልማት ፕሮጀክቶች” መሆናቸውን አቶ አህመድ በማብራሪያቸው ላይ ጠቅሰዋል። “የሸገር ፓርክ” እና “የሳይንስ ሙዚየም” የተገነቡት ከቻይና መንግስት በተገኘ ገንዘብ (grant) መሆኑን ለፓርላማ አባላት ያስረዱት የገንዘብ ሚኒስቴሩ፤ የሸገር ፓርክ “ምን ያህል የከተማውን የኑሮ quality እንዳሳደገ፣ ምን ያህል ማህበረሰቡን አገልግሎት እየሰጠ እንደሆነ የምታውቁት ነው” ሲሉ ፕሮጀክቱ “የቅንጦት” ጉዳይ አለመሆኑን አንስተዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ ይህንን ማብራሪያ እየሰጡ በነበሩት ወቅት፤ ሌላኛው የአብን የፓርላማ አባል አቶ ክርስቲያን ታደለ ንግግራቸውን በማቋረጥ “የስነ ስርዓት ጥያቄ” አንስተዋል። የገንዘብ ሚኒስትሩ የሚሰጡት ምላሽ፤ የምክር ቤቱን “የህግ እና የስነ ስርዓት ጉዳዮችን የጣሰ” እንደሆነ የገለጹት አቶ ክርስቲያን፤ “እርምት እንዲደረግ” ጠይቀዋል። 

“ማንኛውም ግለሰብ በግሉ ገንዘብ መሰብሰብ ይችላል። የሚሰበስበውን ገንዘብ ግን ለህዝባዊ  ዓላማዎች ሲያውለው፤ ገንዘቡ በመንግስታዊ ስነ ስርዓቶች ውስጥ ማለፍ አለበት” ሲሉ የገንዘብ ሚኒስቴር ይህንን የመቆጣጠር ኃላፊነት እንዳለበት አቶ ክርስቲያን በስነ ስርዓት ጥያቄያቸው አመልክተዋል። “በግል የተሰበሰበ ገንዘብ ለህዝብ ኢንቨስትመንት እስከዋለ ድረስ” በፓርላማው መጽደቅ እንዳለበት እና ቁጥጥር ሊደረግበት እንደሚገባም የፓርላማ አባሉ አንጽንኦት ሰጥተዋል።

ገንዘብ ሚኒስቴር የዚህን አይነቱን ገንዘብ የመቆጣጠር ኃላፊነት እያለበት አቶ አህመድ “በግራንት የመጣ ነው” በሚል ማብራሪያ መስጠታቸውን አቶ ክርስቲያን ተችተዋል። “ይሄ በአንድ የፋይናንስ ሚኒስትር ደረጃ ሲባል ለዚህ ምክር ቤትም አይመጥንም። በተለይ ለእኛ ህዝብን ወክለን እዚህ ለተቀመጥንም አይመጥንም። ህገ ወጥም ነው” ያሉት አቶ ክርስቲያን፤ “እርምት እንዲደረግ” ጠይቀዋል።

ከአቶ ክርስቲያን ንግግር በኋላ በድጋሚ ምላሽ መስጠት የቀጠሉት አቶ አህመድ በበኩላቸው፤ “ምንም አይነት የተጣሰ የምክር ቤት ስነ ስርዓት የለም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ከሌሎች አካላት በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ (grant) የሚሰሩ ፕሮጀክቶችም “በፐብሊክ ፋይናንስ አስተዳደር [ውስጥ] የሚያልፉ” መሆናቸውን ያስገነዘቡት አቶ አህመድ፤ ከቻይና መንግስት በተገኘ ድጋፍ ሁለቱ ፕሮጀክቶች ሲሰሩ “ግራንቱን የፈረመው” የገንዘብ ሚኒስቴር መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ከዚህም ባሻገር “የእድገት ምንጮችን ለማስፋት” እና “አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ለማበረታታት” ሲባል “ፈጠራ በታከለበት (innovative)” መንገድ የተሰበሰበ ገንዘብ መጠቀም “የሚከለክል ህግ አለ” ብለው እንደማያምኑ የገንዘብ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ገንዘቡ የተሰበሰበው “ፈቃደኝነት በተሞላበት ሂደት ነው። የተለያዩ የኢትዮጵያ ባለሀብቶች፣ ህዝቡ፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶችም ጭምር፤ የማህበራዊ ኃላፊነትን የመወጣት አካል ሆኖ፤ አዋጥተው በተሰበሰበ ገንዘብ ውጤታማ በሆነ መልኩ ወደ ስራ እየዋሉ ነው ያሉት” ሲሉ ለፕሮጀክቶቹ ገንዘብ የተገኘበትን ሌላኛው መንገድን አብራርተዋል። ምክር ቤቱ የፕሮጀክቶቹን አፈጻጸም “ሄዶ ማየት እና መከታተል” እንደሚችልም አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)