በአማኑኤል ይልቃል
በድጋሚ በተደረገው የወላይታ ዞን ህዝበ ውሳኔ ላይ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ሂደቱን በድጋሚ “እንዲሰረዝ” የሚያስገድዱ ተግባራት በዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ሲፈጸሙ እንደነበር የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ ተናገሩ። የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ በህዝበ ውሳኔው ዕለት፤ ምርጫ ቦርድ “ሌላ ውሳኔ እንደሰጠ” አድርገው መልዕክት ሲያስተላልፉ እንደነበርም አቶ ውብሸት ገልጸዋል።
የምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ይህንን ያሉት፤ ዛሬ ረቡዕ ሰኔ 28፤ 2015 በተካሄደ የፌዴሬሽን ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ ነው። የፌዴሬሽን ምክር ቤት በዛሬው ውሎ ከተመለከታቸው አጀንዳዎች ውስጥ፤ የ“ደቡብ ኢትዮጵያ” ክልልን ለመመስረት የተደረጉትን ህዝበ ውሳኔዎች በተመለከተ ምርጫ ቦርድ የሚያቀርበውን አጠቃላይ ሪፖርት ማዳመጥ አንዱ ነበር።
በነባሩ ደቡብ ክልል ውስጥ በሚገኙ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ላይ ባለፈው ጥር ወር እንዲሁም በወላይታ ዞን በድጋሚ ሰኔ ወር ላይ የተደረጉትን ህዝበ ውሳኔዎች አፈጻጸም የተመለከተ ሪፖርት በአቶ ውብሸት በንባብ ቀርቧል። ምርጫ ቦርድ ህዝበ ውሳኔውን ለማካሄድ ያለፋቸው ሂደቶች፣ የተገኘው ውጤት እንዲሁም ያጋጠሙት ችግሮች በዚሁ ሪፖርት በዝርዝር ተካትቷል።

በ26 ገጾች በተዘጋጀው በዚሁ ሪፖርት ውስጥ በችግርነት ከተጠቀሱ ጉዳዮች ውስጥ፤ በወላይታ ዞን ተከስተው ነበር የተባሉ የህግ ጥሰቶች ይገኙበታል። በወላይታ ዞን ባለፈው ጥር ወር የተካሄደው ህዝበ ውሳኔ እንዲሰረዝ ምክንያት የሆኑ የህግ ጥሰቶችን አጽንኦት ሰጥተው ያነሱት ምክትል ሰብሳቢው፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ 94 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ተናግረዋል። ከእነዚህ ውስጥ 76 ያህሉ ምርጫ አስፈጻሚዎች መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ውብሸት፤ አስራ ስምንቱ ደግሞ የቀበሌ አመራሮች እንደሆኑ አመልክተዋል።
ምርጫ ቦርድ ሰኔ 12፤ 2015 በወላይታ ዞን በድጋሚ ህዝበ ውሳኔ ሲያካሄድም ችግሮች እንዳጋጠሙት አቶ ውብሸት በዛሬው ሪፖርታቸው ጠቁመዋል። በህዝበ ውሳኔ ዕለት ድምጽ ለመስጠት የወጡ መራጮች የያዟቸው መታወቂያዎች፤ ከስድስት ወራት ባነሰ ጊዜ የተሰጡ መሆናቸው በሪፖርቱ እንደ አንድ ችግር ተጠቅሷል። ዕድሜያቸው ያልደረሰ ህጻናት የምርጫ ሰልፍ ላይ መገኘታቸው በተጨማሪ ችግርነት ተነስቷል።
“የቀበሌ አመራሮች ‘ለእርግብ አማራጭ ድምጽ ጨምሩ’ በማለት የምርጫ አስፈጻሚዎቹ ላይ ጫና ማሳደራቸው” በሰኔው ህዝበ ውሳኔ ላይ የታየ ሌላው ችግር መሆኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል። ምርጫ ቦርድ በእነዚህ ችግሮች ምክንያት የ25 ምርጫ ጣቢያዎች ውጤት እንዲሰረዝ እና ከአጠቃላይ ውጤቱ ጋር እንዳይዳመር ማድረጉን ምክትል ሰብሳቢው አቶ ውብሸት አስታውቀዋል። ከዚህ የምርጫ ቦርድ ሪፖርት በኋላ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት በሪፖርቱ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ እድል አግኝተዋል።

በቅድሚያ አስተያየት እና ጥያቄ ያቀረቡት የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ ለማ ናቸው። በህዝበ ውሳኔው ተፈጽመዋል ከተባሉ የህግ ጥሰቶች መካከል አመራሮች ተቀብለው “ማረም ያለባቸው ነገሮች” መኖራቸውን የጠቀሱት ዋና አስተዳዳሪው፤ ሆኖም ከዚህ ጋር በተያያዘ በዞኑ በቁጥጥር ስር የዋሉት አብዛኛዎቹ የምርጫ አስፈጻሚዎች መሆናቸው መዘንጋት እንደሌለበት አጽንኦት ሰጥተዋል። በወላይታ ዞን በድጋሚ ህዝበ ውሳኔ በተደረገበት ወቅት ከመታወቂያ ካርድ ጋር በተያያዘ ምርጫ ቦርድ የወሰደው እርምጃ፤ “በስውር” ለምርጫ አስፈጻሚዎች የተላለፈ መሆኑን አንስተውም ወቀሳ አሰምተዋል።
ይህ አሰራር ቦርዱ “ቀድሞ ያላስተዋወቀው” መሆኑን የጠቀሱት አቶ አክሊሉ፤ አሰራሩ የመጣው “ህዝብ በነቂስ ወጥቶ ድምጽ መስጠት ከጀመረ” እና “ከረፋዱ አራት ሰዓት በኋላ” መሆኑንም ተናግረዋል። በዚህም ምክንያት አንዳንድ መራጮች “ከሰልፍም ጭምር እንዲበተኑ” ተደርገዋል ሲሉ ወንጅለዋል። “ምርጫ የማስፈጸም ሚና ተሰጥቶት የመጣ ምርጫ ቦርድ፤ የመራጩን የመምረጥ መብት የተጋፋ አይነት ሆኖ አይተናል። ይሄ መታረም አለበት ብዬ አስባለሁ። ምናልባትም በቂ ማብራሪያ በዚህ ዙሪያ ቢሰጥ ጥሩ ይመስለኛል” ሲሉ አስተየታቸውን ሰጥተዋል።
ከእርሳቸው በኋላ አስተያየት የሰጡት የደቡብ ክልል አመራሮች ግን፤ የምርጫ ቦርድ ህዝበ ውሳኔውን “በገለልተኝነት” ማስፈጸሙን እና በወላይታ ዞን በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ “ጥሰቶች” መፈጸማቸውን ያመነ አስተያየት ሰጥተዋል። ከአቶ አክሊሉ በመቀጠል አስተያየት ለመስጠት እድል ያገኙት የደቡብ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ፤ ምርጫ ቦርድ “ጥሰት ናቸው” በሚል ያነሳቸው አብዛኛዎቹ ጉዳዮች “ስራ የሚጠይቁ” መሆናቸውን ተናግረዋል። “አንዳንድ ጉዳይ ተወስዶ ሲታይ እኛ ከቆየንበት ባህል አኳያ ውስብስብ ሆኖብናል” ሲሉ ከዲሞክራሲ ልምምድ ጋር የተያያዙ ችግሮች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ይገዙም ተመሳሳይነት ያለው ሀሳብ አንስተዋል። ምርጫ ቦርድ ህዝበ ውሳኔውን “በገለልተኝነት” ማስፈጸሙን የመሰከሩት አቶ ተስፋዬ፤ “ገለልተኝነታቸው ለማረጋገጥ መውሰድ የሚገባቸውን እርምጃዎች ይወስዳሉ” ሲሉ የቦርዱን አመራሮች አወድሰዋል። ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በወላይታ ዞን በድጋሚ በተደረገው ህዝበ ውሳኔ ላይ በችግርነት የተጠቀሰውን የመታወቂያ ጉዳይ በተመለከተም፤ ክስተቱ መፈጠሩን አምነዋል።
በመጨረሻ አስተያየት የሰጡት የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው፤ “እኔ በበኩሌ ለተነሱ ጥያቄዎች ቦርዱ ብዙም ልመልስ ብሎ እንዲለፋ አልፈልግም” ብለዋል። የክልሉ አመራር በተፈጠሩት የህግ ጥሰቶች “ማፈሩን” የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በህዝበ ውሳኔው ላይ የህግ ጥሰት የፈጸሙ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ ክልሉ ከፌደራል መንግስት ጋር እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ከሆኑት የደቡብ ክልል አመራሮች ለቀረቡ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች፤ የምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል። የህግ ጥሰቶችን በተመለከተ ከደቡብ ክልል አመራሮች የተሰጠው ምላሽ “በቂ” መሆኑን አቶ ውብሸት ገልጸዋል። የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ ላነሱት ጉዳይ ግን “በግዴታ” ምላሽ እንደሚሰጡ ለምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል። ዋና አስተዳዳሪው ምርጫ ቦርድ በተመለከተ ያቀረቡት ውንጀላ ተመዝግቦ የሚቀመጥ መሆን፤ ምላሽ ለመስጠት እንዳስገደዳቸውም አስረድተዋል።
በህዝበ ውሳኔው ከተፈጸሙ የህግ ጥሰቶች ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉ የምርጫ አስፈጻሚዎች ብዛት ከፍ ያለ መሆኑ በአቶ አክሊሉ “በተደጋጋሚ” ሲነገር እንደነበር የጠቀሱት የምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ፤ ለዚህም ምላሽ ያሉትን ጠንከር ባለ ቃላት አስደምጠዋል። “ [ዋና አስተዳዳሪው] ‘የእናንተ አጥፊዎች፤ ከእኔ አጥፊዎች ይበዛሉ’ የሚሉት ነገር አለ። የእርስዎን አጥፊዎች ደብቀው፤ እኛ ከመዝገቡ ጋር ቁርኝት ያላቸውን አጥፊዎች አጋልጠን ስለሰጠን ነው የእኛ ቁጥር የበዛው” ሲሉ በአቶ አክሊሉ የተነሳውን ትችት ተከላክለዋል።
“[አቶ አክሊሉ] ግምት ውስጥ የማያስገቡት፤ የእሳቸው አጥፊዎች አቅም ያላቸው ናቸው። አንዱ ለ150 ሰው የሚሆን ነው” ሲሉም የዞን፣ የወረዳ እና የቀበሌ አስተዳዳሪዎች ያላቸው ስልጣን ለንጽጽር የማይቀርብ መሆኑን አብራርተዋል። በወላይታ ዞን የተለያየ እርከን ላይ ያሉ አስተዳዳሪዎች፤ በምርጫ አስፈጻሚዎች ላይ ያደርጉት ነበር ያሉትን ጫና ለዚህ በማሳያነት ጠቅሰዋል። በዞኑ በድጋሚ ህዝበ ውሳኔ በተደረገበት ዕለትም፤ የዞኑ አስተዳዳሪ “ከቁጥጥር ውጪ” የሆነ ድርጊት ሲፈጸሙ እንደነበር አቶ ውብሸት በማብራሪያቸው ላይ አንስተዋል።
በድምጽ መስጫው ዕለት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር እንዲሁም የደቡብ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ እና ሌሎች የክልሉ አመራሮች “በጉዳዩ ውስጥ ገብተው እርምጃ ባይወስዱ” ኖሮ፤ ቦርዱ ህዝበ ውሳኔውን በድጋሚ “ይሰርዘው እንደነበር” ምክትል ሰብሳቢው ተናግረዋል። “አቶ አክሊሉ በዚያ ቀን ያደርጉ የነበረው ነገር ምንድነው? ዋና የኦፕሬሽን ኃላፊያችንን harass ያደርጉ ነበር። ከህግ ክፍላችን ጋር፣ ከእኛ ውጪ ግንኙነት ያደርጉ ነበር። ‘መመሪያ ተላልፎላችኋል፤ ቦርዱ ሌላ ውሳኔ ሰጥቷል’ እያሉ ነበር የሚነግሯቸው” ሲሉ በዕለቱ የተፈጠረውን ችግር ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት አስረድተዋል።
ምርጫ ቦርድ በህዝበ ውሳኔው ሂደት ላይ በወሰዳቸው እርምጃዎች፤ የመራጮችን ድምጽ “ማስከበሩን” እና “ከአጭበርባሪዎች ማዳኑን” በመጥቀስም ቦርዱ “የመራጩን የመምረጥ መብት ተጋፍቷል” በሚል ለቀረበው ትችት አቶ ውብሸት ምላሽ ሰጥተዋል። የምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ በማብራሪያቸው ማጠቃለያ ላይ ከዚህ በኋላ በደቡብ ክልል አማካኝነት መወሰድ አለበት ያሉትን እርምጃም ጠቁመዋል።
“ለዚህ ጊዜ መባከን፣ ለዚህን ያህል ገንዘብ ወጪ ምክንያት የሆኑትን፣ የእኛ የምንችላቸውን አጥፊዎች አውጥተን ሰጥተናል። ትኩረት ሰጥታችሁ ዳግም ተመሳሳይ ነገር እንዳይደረግ በሌላውም ጊዜ ትምህርት እንዲሆን፤ አቅም ላላቸውም አጥፊዎች፣ በስልጣን ላሉትም አጥፊዎች ወደ ህግ ፊት የሚቀርቡበትን ሁኔታ እንድታመቻችሁ አደራ እላለሁ” ብለዋል አቶ ውብሸት። በወላይታ ዞን የተከሰተው ችግር “ለምክር ቤቱ የማይመጥን” እንደሆነ የጠቀሱት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ በበኩላቸው፤ የህግ ጥሰት የምርመራ ስራው እንደሚቀጥል አመልክተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)