በአማኑኤል ይልቃል
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አራተኛ ዙር ሙሌት ከነሐሴ ወር መጨረሻ በፊት እንደማይጠናቀቅ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። የዘንድሮው የግድቡ ሙሌት “ለሱዳን እና ለግብጽ በቂ ውሃ መሄዱ እየተረጋገጠ” የሚከናወን መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ይህንን ያሉት ዛሬ ሐሙስ ሰኔ 29፤ 2015 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ ላይ ነው። በዛሬው የፓርላማ ውሎ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተነሱላቸው ጥያቄዎች ውስጥ የህዳሴው ግድብን የተመለከተው ይገኝበታል። ይህንን ጥያቄ ያነሱት ወ/ሮ ጀማነሽ ወልደሚካኤል የተባሉ የምክር ቤት አባል፤ የህዳሴው ግድብ ግንባታ “ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በጥሩ ሁኔታ እየተሰራ” መሆኑን አንስተው፤ በአጠቃላይ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም አሁን በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ማብራሪያ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል።
ለፓርላማ አባሏ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት አብይ “ህዳሴ በጣም መልከ መልካም ነው። ውብ ነው፤ በጣም ቆንጆ ነው። እንደዚያ ሆኖ ይቀጥላል” ብለዋል። የፕሮጀክቱ ግንባታን በተመለከተ ግን ዝርዝር ምላሽ ሳይሰጡ የቀሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ወሳኝ milestone” ሲሉ ስለጠሩት የእዚህ ዓመት የግድቡ ውሃ ሙሌት አካሄድ ግን ጥቂት ማብራሪያ አስደምጠዋል።
ከዚህ ቀደም በነበሩት ዓመታት በሐምሌ ወር “አጋማሽ” እና “የመጀመሪያው ሳምንት” ላይ የግድቡ የውሃ ሙሌት ተጠናቅቆ “ ‘ውሃ ፈሰሰ’ ተብሎ ይከበር እንደነበር” ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው አስታውሰዋል። “ዘንድሮ ቢያንስ እስከ ነሐሴ መጨረሻ፣ እስከ መስከረም መጀመሪያ ድረስ ያ ፕሮግራም አይካሄድም። ቀስ እያልን በቂ ውሃ ለሱዳን፣ ለግብጽ መሄዱን እያረጋገጥን ነው የምንሰራው። የእኛንም በማያጓድል፤ የእነሱንም ፍላጎት በሚመልስ” ሲሉ የዘንድሮው የህዳሴው ግድብ ሙሌት ከተለመደው ጊዜ ዘግይቶ እንደሚጠናቀቅ አመልክተዋል።
በዘንድሮው ዓመት ኢትዮጵያ “ሰፊ ዝናብ” ማግኘቷን የጠቀሱት አብይ፤ በግድቡ ሙሌት ሁለቱ ሀገራት “እንዳይገፉ” እና “የሚገባቸውን እንዲያገኙ” እንደሚደረግ ጠቅሰዋል። ሀገራቱ “የኢትዮጵያ ፍላጎት መልማት ብቻ መሆኑን እንዲገነዘቡ” ለማድረግም ሲባል፤ መንግስት “ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ እየሄደ” መሆኑን ተናግረዋል።
“የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት፤ ሱዳን እና ግብጽ ወንድሞቻችን፣ ጎረቤቶቻችን [ናቸው]። ልንነጠል የማንችላቸው ህዝቦች ናቸው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከዚህ ቀደምም ሁለቱ ሀገራት በህዳሴው ግድብ ላይ ያላቸውን “ስጋት” “ታሳቢ ያደረጉ” ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል። “የእኛ ቀጣዩ ጥያቄ ‘እንዴት በጋራ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ልንሰራ እንችላለን?’ [የሚል ነው]። አሁን በዚህ ከምንጨቃጨቅ ‘አዳዲስ ስራ እንዴት እንጀምር?’ የሚለውን ከወንድሞቻችን ጋር ለመነጋገር ዝግጁ ነን። ንግግሮችም ይደረጋሉ፤ ውጤት ይጠበቃል” ሲሉም አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)