በአማኑኤል ይልቃል
ከኢትዮጵያ ሁለት ሚሊዮን ገደማ ሰራተኞችን ለመቅጠር የውጭ ሀገራት ለስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ጥያቄ ማቅረባቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። ባለፉት 11 ወራት፤ 100 ሺህ ገደማ ሰዎች “ህጋዊ በሆነ” የውጭ ስምሪት ስራ ማግኘታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ ይህንን ያስታወቁት ዛሬ በተካሄደ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ የተገኙት፤ ከተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ማብራሪያ ለመስጠት ነበር። የስራ አጥነትን ጉዳይ ያነሱት ዶ/ር አሰለፈች ኮቼ የተባሉ የፓርላማ አባል፤ ችግሩ “አሁንም በጣም አሳሳቢ” መሆኑን ተናግረዋል።
በየዓመቱ ከዩኒቨርስቲዎች የሚመረቁ ወጣቶች እና “ሌሎች” ስራ ፈላጊዎች ቁጥር “በርካታ መሆኑን” በመጥቀስም፤ መንግስት የስራ አጥነትን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ምን ሊሰራ እንዳሰበ የፓርላማ አባሏ ጠይቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በየዓመቱ “ሶስት ሚሊዮን አዳዲስ ሰዎች” ስራ ፈላጊ ሆነው ገበያውን እንደሚቀላቀሉ አስታውሰዋል።
ይህ ጉዳይ “በራሱ ከፍተኛ ፈተና” መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለዚህም መንግስታቸው የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴርን በማቋቋም ለስራ እድል ፈጠራ ትኩረት መስጠቱን አስገንዝበዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ “ከፍተኛ ለውጥ እያመጡ ካሉ የፌደራል ተቋማት አንዱ” መሆኑን የገለጹት አብይ፤ በዚህ በጀት ዓመት 11 ወራት ውስጥ ብቻ 3.1 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ስራ ማግኘታቸውን አስረድተዋል።
ከተፈጠረው ከዚህ የስራ እድል ውስጥ 2.4 ሚሊዮን ገደማ የሚሆነው ከግብርና እና አገልግሎት ዘርፎች መሆኑን የጠቀሱት አብይ፤ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ደግሞ 600 ሺህ ገደማ ሰዎች ስራ ማግኘታቸውን አመልክተዋል። በእነዚህ ወራት ውስጥ በህጋዊ የውጭ የስራ ስምሪት ስራ ያገኙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 100 ሺህ ገደማ መሆኑን አክለዋል።
ከኢትዮጵያ ሄደው በውጭ ሀገራት የሚቀጠሩ ስራተኞች ለማግኘት በርካታ ፍላጎት መኖሩን በማብራሪያቸው የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በአሁኑ ወቅት “ሁለት ሚሊዮን ገደማ የሰራተኛ ጥያቄ” እንደቀረበለት አብራርተዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሰራተኞችን ለማቅረብ ከተለያዩ ሀገራት ጋር “እየተፈራረመ” መሆኑም ለፓርላማ አባላቱ አስታውቀዋል።
የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር “ይህንን ለማስተናገድ በሚያደርገው ጥረት የፓርላማው እና የሰፊው ህዝብ ከፍተኛ ድጋፍ ያስፈልገዋል” ያሉት አብይ፤ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚደረግ ድጋፍ ዜጎች “ወደ ውጭ ህጋዊ ሆነው” እንዲጓዙ እና “ጥቃት ሳይደርስባቸው የተሻለ ገቢ አንዲያገኙ ለማድረግ” እንደሚያግዝ ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)