የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ውሎ 

በሃሚድ አወል

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሀመድ ዛሬ ሐሙስ ሰኔ 29፤ 2015 በተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄ እና አስተያየቶች ምላሽ እና ማብራሪያ ሲሰጡ ውለዋል። በዛሬው ስብሰባ ከተገኙ 327 ፓርላማ አባላት መካከል ሃያ አንዱ፤ የሰላም እና ጸጥታ፣ ኢኮኖሚዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ ጥያቄዎችን አቅርበዋል። ከሰሞኑ በፓርላማ ስብሰባዎች ተደጋግሞ የተነሳው፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት የተሰሩ እና በግንባታ ላይ ፕሮጀክቶች ጉዳይም ዛሬም መነጋገሪያ ሆኗል።  

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን (አብን) ወክለው ፓርላማ የገቡት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፤ ጥያቄያቸውን ለአብይ ካቀረቡ  የፓርላማ አባላት መካከል ናቸው። ዶ/ር ደሳለኝ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በማቅረብ አስተያየታቸውን ቢጀምሩም፤ አብዛኛውን የጥያቄ ጊዜያቸውን ያዋሉት ግን በጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር ላይ ታይቷል ባሉት ድክመት ላይ ነው። የፓርላማ አባሉ በሀገሪቱ ተስተውሏል ላሉት “ሁለንተናዊ ሀገራዊ ምስቅልቅል፣ ቀውስ፣ ውድመት” እና “ሀገራዊ መክሸፍ” የመንግስትን እና የጠቅላይ ሚኒስትሩን “የወደቀ አመራር”፤ “ዋነኛ” ተጠያቂ አድርገዋል። 

“የኢትዮጵያ መልክዓ ፖለቲካ በሙሉ በሚባል ደረጃ የደም ምድር ሆኗል” ያሉት ዶ/ር ደሳለኝ፤ ለዚህ አስተያየታቸው በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የነበሩ እና ያሉ “ጦርነቶችን” በአስረጂነት አንስተዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ የገዢው ፓርቲ አመራር “የወደቀ” መሆኑን በድጋሚ ያነሱት የፓርላማ አባሉ፤   መፍትሔ ያሉትን አማራጭ በጥያቄ መልክ አቅርበዋል። “የሀገራዊ ቀውስ አፈላላጊ ጉባኤ እንዲዘጋጅ አድርገው፤ ሳይረፍድ ለሀገራዊ ቀውሱ መፍትሔ መላ ቢበጅ አይሻልም ወይ?” ሲሉም የአብኑ የፓርላማ ተወካይ መፍትሔውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አመላክተዋል።

ዶ/ር ደሳለኝ በብልጽግና ፓርቲ የሚመራው መንግስት እንዲሁም እራሳቸው አባል የሆኑበት ፓርላማ፤ ኢትዮጵያ “ከገባችበት የፖለቲካ ቅርቃር ማውጣት” አይችሉም ሲሉም ተደምጠዋል። በዚህም ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን እንዲያስረክቡ እና ፓርላማው እንዲበተን ሃሳብ አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ስልጣናቸውን “ለጊዜያዊ ሲቪል አስተዳደር እንዲያስረክቡ”፤ የህዝበ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም “ምክር ቤቱን እንዲበትኑ እና ለአዲስ ምርጫ መንገዱን እንዲጠርጉ” በይፋ ጠይቀዋል።

ከተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሳቅ እና ማጉረምረም ካስከተለው ከዚህ የዶ/ር ደሳለኝ ጥያቄ ሌላ፤ የሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮችን የተመለከቱ ጠንከር ያሉ ጥያቄዎችም ተነስተዋል። አቶ አኔሳ መልኮ የተባሉ የፓርላማ አባል፤ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ይስተዋላሉ ያሏቸውን የሰላም መደፍረሶች በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ጠይቀዋል። አቶ አኔሳ ካነሷቸው ችግሮች መካከል፤ “በተቀናጀ መንገድ” ይፈጸማሉ ያሏቸው “የአመራሮች እና የዜጎች ግድያ እና እገታ” ይገኝበታል። የጸጥታ ኃይሎችን ኢላማ ያደረጉ “ጥቃቶች” እየተፈጸሙ እንደሚገኙም የፓርላማ አባሉ አንስተዋል። 

እንዲህ አይነት የጸጥታ ችግሮች “ከሸኔ” ጋር የሰላም ንግግር ከተጀመረ በኋላም ጭምር በኦሮሚያ ክልል መቀጠሉን የጠቀሱት አቶ አኔሳ፤ “ከሸኔ ጋር የተጀመረው የሰላም ንግግር ሂደቱና ውጤቱ ምን ይመስላል?” ሲሉ ጠይቀዋል። ሌላኛው የምክር ቤት አባል አቶ መሀመድ አህመድ በበኩላቸው፤ መንግስት ከህዝባዊ ወሓነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጋር የተፈራረመው የሰላም ስምምነት ላይ ጥያቄ አንስተዋል። ስምምነቱን “ወደ መሬት በማውረድ እና ዘላቂነት ለማረጋገጥ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ?” ሲሉም አቶ መሀመድ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

@ethiopiainsider

“የአመራሮች እና የዜጎች ግድያ እና እገታ፣ የ ኃይሎችን ኢላማ ያደረገ ጥቃት፤ በተቀናጀ መንገድ እየተፈጸመ ነው” – አኔሳ መልኮ (የፓርላማ አባል) #ethiopia #ethiopiannews #news #ethiopianparliament🇪🇹 #abiyahmed #pmabiyahmed #peace ethiopiapeace security ethiopiainsider #ኢትዮጵያ #ዜና #ፓርላማ አብይአህመድ ጸጥታ ግድያ እገታ ኢትዮጵያኢንሳይደር

♬ original sound – Ethiopia Insider

አቶ አዳነ ተሾመ የተባሉ ሌላ የፓርላማ አባል፤ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች እየታዩ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት እንዲፈቱ እና የህዝቡን ሰላም ለማስጠበቅ በመንግስት በኩል እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ምን እንደሆኑ ጥያቄ አቅርበዋል። አቶ አዳነ ማብራሪያ የጠየቁበት ሌላኛው ጉዳይ፤ በአማራ ክልል የተፈጠረውን ችግር መንስኤ እና የክልሉ ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀት ሂደትን ነው። ሌላው ከሰላም እና ጸጥታ ጋር ተያይዞ የተነሳው ጥያቄ፤ በጦርነት የተፈናቀሉ ሰዎችን የሚመለከት ነው። ሀሰና ሀንፍሬ የተባሉ የፓርላማ አባል፤ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመመለስ ስለተሰራው ስራ ማብራሪያ ጠይቀዋል። 

ከሰሞኑ በፓርላማ በነበሩ የተለያዩ ስብሰባዎች ጥያቄ ሲነሳባቸው የነበሩት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀሳብ አመንጪነት የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ላይ ዛሬም ጥያቄዎች ተነስተዋል። ከኦሮሚያ ክልል አርሲ ነገሌ ብልጽግናን የተቀላቀሉት ወይዘሮ ጀማነሽ ወልደሚካኤል፤ ከፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ አስተያየት  ካቀረቡ ሶስት ሰዎች መካከል አንዷ ናቸው። ወይዘሮ ጀማነሽ እንደ “ገበታ ለሀገር” ያሉ ፕሮጀክቶች ላይ የተለያዩ ሃሳቦች እንደሚነሱ ገልጸዋል። ከእነዚህ ሃሳቦች መካከል “አርሶ አደሩ የማዳበሪያ እጥረት እያጋጠመው ባለበት እና የመልሶ ማቋቋም ስራዎች ከፍተኛ ሀብት በሚጠይቅበት ሁኔታ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነው ወይ የሚሉ ትችቶች” እንደሚገኙበት ጠቁመዋል። የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ተወካይዋ የፕሮጀክቶቹ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው በመጠየቅ አስተያየታቸውን ቋጭተዋል።  

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክቶች በወይዘሮ ጀማነሽ አማካኝነት ጥያቄ ቢነሳበትም ከሌሎች ሁለት የፓርላማ አባላት ግን አድናቆት ተችሯቸዋል። አቶ መሃመድ አህመድ የተባሉ የተወካዮች ምክር ቤት አባል፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የኢትዮጵያን ገጽታ የሚለውጡ” ፕሮጀክቶችን በራሳቸው ተነሳሽነት በማከናወናቸው አድናቆታቸውን ገልጸውላቸዋል። ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክቶች አድናቆታቸውን የገለጹት ሌላኛው የምክር ቤት አባል ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ ናቸው።

@ethiopiainsider

“ዶ/ር አብይ አህመድ ታማኝ፣ ባለአደራ፣ selfless ሰው በመሆንዎ እንኮራቦታለን” – ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በፓርላማ #ethiopia #ethiopianews #news #ethiopianparliament🇪🇹 #ashebir #abiyahmed #pmabiyahmed #ethiopiainsider ኢትዮጵያ ዜና ፓርላማ አብይአህመድ አሸብርወልደጊዮርጊስ ኢትዮጵያኢንሳይደር

♬ original sound – Ethiopia Insider

“ብዙ የሀገራት መሪዎች በግል የሚያገኙትን እርዳታ እና ሽልማት ለራሳቸው፣ ለቤተሰባቸው መበልጸጊያ ያደርጋሉ” ያሉት ዶ/ር አሸብር፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩን፤ “ጨዋ፣ ታማኝ፣ ባለአደራ፣ selfless ሰው” ሲሉ አሞካሽተዋቸዋል። አብይ “በግል ጥረት” ያመጡትን ገንዘብ የህዝብ የልማት ስራዎች ላይ ማዋላቸውን የገለጹት ዶ/ር አሸብር፤ “ይህ ደግሞ ተገቢ የሆነ እውቅና እየተሰጠው ነው ብዬ አላምንም” ሲሉ ተጨማሪ ሙገሳ ለጠቅላይ ሚኒስተሩ እንደሚያሻ ጠቁመዋል። ዶ/ር አሸብር በፕሮጀክቶቹ ላይ ጥያቄ የሚያቀርቡ አካላትንም ተችተዋል። የፕሮጀክቶቹ አስፈላጊነት እና የገንዘብ ምንጭ ላይ ጥያቄ የሚያነሱ አካላት “ምን እየፈለጉ እንደሆነ አይገባኝም” ሲሉም ጠያቂዎቹን አጣጥለዋል።

የፓርላማ አባላቱ ጥያቄ እና አስተያየቶቻቸውን ካቀረቡ በኋላ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሰፋ ያለ ምላሽ እና ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል። የኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በመከፋፈል ማብራሪያቸውን ያስደመጡት አብይ፤ ከሰላም እና ጸጥታ ጋር በተያያዘ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ረዘም ያለ ጊዜ ወስደው ምላሾችን ሰጥተዋል። እርሳቸው ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ “ችግሮች ተበራክተዋል” በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ፤ የችግሮቹ ምክንያት ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መሆኑን ጠቁመዋል። በፖለቲካው ረገድ “ጽንፍ የያዘ ፖለቲካን” እና “የወል እውነት ማጣትን” ጠቅሰዋል። ስራ አጥነትም ሌላኛው ችግር መሆኑን አመልክተዋል።

አብይ ከሰላም እና ጸጥታ ጋር በተያያዘ አጽንኦት ሰጥተው ያብራሩት ሌላኛው ጉዳይ፤ ከክልል ልዩ ኃይሎች ጋር በተያያዘ መንግስታቸው ያሳለፈውን ውሳኔ ነው። ውሳኔውን “ጊዜ ወስደን ስንወያይ ቆይተን፣ አጥንተን በስራ አስፈጻሚ ተወያይተን፣ ተስማምተን፣ ኮሚቴ አደራጅተን፣ ሁሉን ክልል አወያይተን፣ በህግ እና በስርዓት የሄድንበት ነው” ሲሉም አካሄዱ እንዴት እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ቢሉም ይህ ውሳኔ ግን ከተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና ከአማራ ክልል የፖለቲካ ልሂቃን ተቃውሞ ሲገጥመው ቆይቷል። አብይ በዛሬው ማብራሪያቸው፤ ውሳኔው ከተላለፈ በኋላ “አንዳንድ ክልሎች ባልተገባ መንገድ ሄደውበታል” ሲሉ ተናግረዋል። 

የውሳኔው አፈጻጸም አሁን ያለበትን ደረጃ ሲያብራሩም፤ “ብዙ ርቀት ሂደናል ግን ይቀረናል። አንዳንድ የሸሸጉ፣ የደበቁ [አካላት] አሉ። ገና እያጠናን እናስተካክላቸዋለን” ብለዋል። “ኢትዮጵያ ውስጥ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከመከላከያ፣ ከክልል ፖሊስ [እና] አድማ ብተና ውጭ ያለ ህገ ወጥ ሰራዊት፣  የታጠቀ ኃይል፤ ደረጃ በደረጃ በህግ ወደ ስርዓት ይገባል” ሲሉም ለፓርላማ አባላቱ በአጽንኦት አስረድተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “በየቦታው አሉ” ያሏቸውን “ሽፍቶች” በተመለከተ፤ “በእኛ በኩል የሚሰራውን መስራት ይኖርብናል በነሱ በኩል ህግ ማስከበርና በድርድር የሚመለስ ካለም እያዩ መሄድ ጠቃሚ ይሆናል” ብለዋል፡፡ 

ከሰላም እና ጸጥታ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበላቸው እና ማብራሪያ የሰጡበት ሌላኛው ጉዳይ፤ በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች መካከል ያለውን ሁኔታ የተመለከተ ነው። የሁለቱ ክልሎች አመራሮች በአዳማ እና በባህርዳር ውይይቶች ማድረጋቸውን የጠቆሙት አብይ፤ “እነዚህ ውይይቶች የበለጠ መቀራረብ እያመጡ” መሆኑን ጠቁመዋል። ከክልሎቹ የተፈናቀሉ ዜጎችን በተመለከተም፤ “የኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች፤ የተፈናቀሉ  ሰዎችን በተመለከተ aggressively ሰርተው ማስተካከል ይችላሉ” ሲሉ ጉዳዩ በክልሎች እጅ ያለ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው የፓርላማ ውሏቸው፤ በፕሬዝዳንትነት የሚመሩትን ብልጽግና ፓርቲ እና መንግስታቸውን ላይ የቀረቡ ትችት እና ክሶችን በተመለከተም ምላሽ ያሉትን አስደምጠዋል። ክሶች መቅረባቸው “ምንም ጉዳት የለውም” ያሉት አብይ፤ ችግሩ “ደምሮ ሁሉን መጥፎ ማድረግ እና ሁሉን ጥሩ ማድረግ መካከል ላይ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

አብይ አመራራቸው “ለሀገራዊ ምስቅልቅሉ” ተጠያቂ ነው በሚል ለቀረበባቸው ክስ፤ ፓርቲያቸው በቅርቡ በነበረው ስብሰባ የእርሳቸው “አመራር ጥፋት አምጥቶብናል” እንዳላላቸው በመጥቀስ ምላሽ ሰጥተዋል። የብልጽግና ፓርቲ በሚቀጥለው ሶስት፣ አራት ወራት ስብሰባ እንዳለው የጠቆሙት አብይ፤  ፓርቲያቸው “ጥፋት አምጥቶብናል ካለ የብልጽግና ጉዳይ ነው የሚሆነው” ሲሉም አመራራቸውን በሚመለከት የቀረበው ትችት በፕሬዝዳንትነት የሚመሩት ፓርቲ ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል። ፓርላማው ተበትኖ ምርጫ እንዲካሄድ ለቀረበው አስተያየትም፤ “ምርጫ ይካሄድ የሚለው [ሃሳብ] በጣም ጠቃሚ ነው። ግን ሶስት ዓመት መታገስ አለብን። በየሳምንቱ ምርጫ ስለማይደረግ” ሲሉ መልሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራራቸውን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ እንደሰጡት ሁሉ፤ በእርሳቸው ሃሳብ አመንጪነት የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን በሚመለከት የተነሱ አስተያየቶች ላይም ሰፋ ያለ ማብራሪያ አቅርበዋል። ፕሮጀክቶቹ እየተጠናቀቁ ሲሄዱ ጥያቄዎች እየጎሉ መምጣታቸውን ያነሱት አብይ፤ “የስራው ማለቅ የሚያማቸው ሰዎች አሉ ማለት ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። “ሀገር ማልበስ፣ ለትውልድ መሰረት መጣል፣ ትምህርት ቤት መገንባት፣ የአዛውንቶችን ቤት ማፍረስ፣ እጅ አጠሮችን ማጋራት፣ በፋይናንሻል ኦዲት ሂሳብ ሊራከስ የሚችል ጉዳይ አይደለም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ተነሳሽነቱ እንደ ጎርጎራ ያሉ ፕሮጀክቶችን በመጥቀስ በጠበበ መልክ መታየት እንደሌለበት ሞግተዋል።   

“ኢኒሼቴቩ በጣም ሰፊ ነው። የገንዘብ ምንጩም በጣም ሰፊ ነው። ተደምሮ ግን ያለብንን የድህነት መጠን መቀነስ እና የሰዎችን ተጠቃሚነት ማሳደግን ታሳቢ ያደረገ ነው” ሲሉ ከፕሮጀክቶቹ ጀርባ ያለውን አመክንዮ አስረድተዋል። ፕሮጀክቶቹ በመንግስት በጀት እንደማይሰሩ ያነሱት አብይ፤ በ“ደጋግ ኢትዮጵያውያን” እና በውጭ ሀገር መንግስታት ድጋፍ እንደሚሰሩ አመልክተዋል። ለዚህም በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ በቻይና እና በፈረንሳይ መንግስት ድጋፍ ተገነቡ ያሏቸውን የአንድነት ፓርክ፣ የኢዩቤልዩ ቤተ መንግስት እና የወዳጅነት ፓርክ ፕሮጀክቶችን በማሳያነት ጠቅሰዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሮጀክቶችን “ኦዲት” በተመለከተም፤ የሀገራቱን መሪዎች “ጠይቁ” ሲሉ ተደምጠዋል። ከፕሮጀክቶቹ ጋር በተያያዘ ጥያቄዎች የበረከቱበትን ምክንያት አብይ ሲያብራሩም፤ “ተከናወኑ፣ ተሳካላቸው፤ በሆነ መንገድ አድርገን፣ ሽንቁር ፈልገን ይሄን ስኬት እናጠልሽ ብለው የሚነሱ ምስኪን ፖለቲከኞች አሉ” ብለዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለት ሰዓት ተኩል ገደማ የፈጀውን ማብራሪያቸውን ሲያሳርጉ፤ “ብተዋቸው ስለሚሻል አንዳንድ የተውኳቸው ጉዳዮች አሉ” ብለዋል። አብይ ምላሽ ሳይሰጡ ካለፏቸው ጥያቄዎች መካከል፤ “ከሸኔ ጋር የተጀመረው የሰላም ንግግር ሂደቱና ውጤቱ ምን ይመስላል?” በሚል በአቶ አኔሳ መልኮ የቀረበው አንዱ ነው። ሌላኛው የፓርላማ አባል አቶ ብርሃኑ ሀንካራ ያነሱት እና ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት የሚመለከተው ጥያቄም በተመሳሳይ በአብይ ምላሽ አልተሰጠውም። የአቶ ብርሃኑ ጥያቄ፤ “በአሁኑ ጊዜ ከጎረቤት አገሮቻችን በተለይ ከኤርትራ ጋር ያለን ግንኙነት እንዴት ይታያል?” የሚል ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)