የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 22.5 ቢሊዮን ብር የኮንዶሚኒየም ግንባታ ብድር መክፈሉን አስታወቀ 

በአማኑኤል ይልቃል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለኮንዶሚኒየም ግንባታ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወሰደው ብድር ውስጥ 22.5 ቢሊዮን ብር ያህሉን መክፈሉን የከተማይቱ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ። የከተማ አስተዳደሩ አሁን ያለበት የኮንዶሚኒየም ቤቶች ብድር 41.5 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ከንቲባዋ ገልጸዋል።

አዳነች አቤቤ ይህንን ያስታወቁት፤ የከተማዋ ምክር ቤት ዛሬ ቅዳሜ ሐምሌ 1፤ 2015 እያካሄደ ባለው መደበኛ ጉባኤ ላይ ነው። በዚህ ጉባኤ ላይ የከተማ አስተዳደሩን የ2015 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት ከንቲባዋ፤ ባለፉት 12 ወራት የተከናወኑ ዋና ዋና ጉዳዮችን አንስተዋል።

በከንቲባዋ ሪፖርት ውስጥ የተካተተው አንዱ ጉዳይ፤ የአዲስ አበባ የቤት አቅርቦትን የተመለከተ ነው። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከዚህ ቀደም ዕጣ በወጣባቸው 139 ሺህ ገደማ የኮንዶሚኒየም ቤቶች የማጠናቀቂያ ስራ ለማከናወን ታቅዶ፤ 93.5 በመቶው መሳካቱን ከንቲባዋ ገልጸዋል። በተጨማሪም የከተማ አስተዳደሩ እያስገነባቸው ካላቸው አስር ሺህ የኪራይ ቤቶች ውስጥ፤ አምስት ሺህውን እስከ ቀጣዩ ዓመት መጨረሻ እንደሚያጠናቅቅ በሪፖርታቸው ላይ ጠቅሰዋል።  

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮንዶሚኒየም ቤቶችን ከማጠናቀቅ ባሻገር፤ ለቤቶቹ ግንባታ ከወሰደው ብድር 35.1 በመቶ ያህሉን መመለስ መቻሉን አዳነች በሪፖርታቸው አመልክተዋል። የከተማው አስተዳደር ለሚገነባቸው የኮንዶሚኒየም ቤቶች የሚውለውን የቦንድ ብድር ሲያገኝ የቆየው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው።

በግንባታ ላይ የነበሩ የኮንዶሚነየም ቤቶች ባለፉት ዓመታት ሳይጠናቀቁ በመቆየታቸው ምክንያት የተጠራቀመው ብድር 54 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስተዳደሩ ከዚህ ቀደም አስታውቆ ነበር። ብድሩን የሰጠው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ዕዳው ሳይከፈል በመቆየቱ ሳቢያ፤ በ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ወራት ላይ ለከተማ አስተዳደሩ ተጨማሪ ብድር መስጠትን አቁሞ ነበር።

መንግስታዊው ባንክ እና የከተማ አስተዳደሩ ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ በጋራ ባደረጉት ግምገማ፤ ብድሩን መመለስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተነጋግረው ስምምነት ላይ መድረሳቸው መገለጹም ይታወሳል። በዚህ መሰረት የከተማው አስተዳደር በትላትናው ዕለት በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመት፤ ከንግድ ባንክ ከወሰደው ብድር ውስጥ “22.5 ቢሊዮን ብር ማቀናነሱን” ከንቲባ አዳነች በዛሬው የከተማዋ ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ተናግረዋል።

ይህ ብድር የተከፈለውም “የመኖሪያ ቤቶችን በዕጣ እንዲሁም የንግድ ቤቶችን በጨረታ በማስተላለፍ” የከተማ አስተዳደሩ ካገኘው ገንዘብ ላይ መሆኑን ከንቲባዋ ገልጸዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተወሰነውን ብድር መክፈል በመቻሉ፤ ያለበት የቦንድ ዕዳ “ወደ 41.5 ቢሊዮን [ብር] ዝቅ ማድረግ” መቻሉን አዳነች አስረድተዋል። የከተማው አስተዳደር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አምስት ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ብድር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መውሰዱን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከባንኩ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)