የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል በአዲስ አበባ በርካታ “የአማራ ተወላጆች ታስረዋል” አሉ

በሃሚድ አወል

“ጽንፈኛ” እና “ጸረ ሰላም” በሚል ከታሰሩ ከአስር ሺህ በላይ ግለሰቦች መካከል፤ “አብዛኞቹ የአማራ ተወላጆች” መሆናቸውን አንድ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባል ተናገሩ። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ “የምንይዘው ብሔር ለይተን አይደለም” ሲል የምክር ቤት አባሉን አስተያየት አስተባብሏል። 

ከየካ ክፍለ ከተማ ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ወክለው የከተማይቱን ምክር ቤት የተቀላቀሉት ዶ/ር ካሳ ተሻገር ይህን ያሉት፤ ዛሬ ቅዳሜ ሐምሌ 1፤ 2015 ጨምሮ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ በሰጡት አስተያየት ነው። ዶ/ር ካሳ “የታሳሪዎች አያያዝ ሰብዓዊነትን ታሳቢ ያደረገ አይደለም” ሲሉም ተችተዋል።

በዛሬው የምክር ቤት ጉባኤ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩን የ2015 እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል የሰላም እና ጸጥታ ጉዳይ አንዱ ነበር። ከንቲባዋ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአመራራቸው የተከናወኑ ተግባራትን ሲዘረዝሩ፤ “የከተማውን ሰላም እና ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል እና ለማወክ” ሲንቀሳቀሱ ነበሩ ያሏቸው “ከ2,000 በላይ ጸረ ሰላም ኃይሎች” በህግ እንዲጠየቁ መደረጉን ጠቅሰዋል።

አዳነች ሪፖርታቸውን አቅርበው ከጨረሱ በኋላ አስተያየት ከሰጡ የከተማይቱ ምክር ቤት አባላት መካከል አንዱ የሆኑት ዶ/ር ካሳ ተሻገር፤ ከንቲባዋ ከጠቀሱት ቁጥር በእጀጉ የሚልቅ አሃዝ በማንሳት በጉዳዩ ላይ “አለኝ” ያሉትን መረጃ አቅርበዋል። “በቁጥር ደረጃ የቀረበው ሁለት ሺህ ይላል። በእኔ መረጃ ደግሞ ከ10 ሺህ ያልፋል” ሲሉ የታሳሪዎች ቁጥር ከንቲባዋ የጠቀሱት ብቻ አለመሆኑን ዶ/ር ካሳ ጠቁመዋል። እኚሁ የምክር ቤት አባል ከአሃዙ በተጨማሪ ሌላም የልዩነት ሃሳብ አንስተዋል። 

“ጽንፈኛ ኃይሎች፣ ጸረ ሰላም ኃይሎች በሚል በእስር ቤት በአብዛኛው በጅምላ እየታሰሩ ያሉት የአማራ ተወላጆች ናቸው” ያሉት ዶ/ር ካሳ፤ “ምሁራን ፣አንቂዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የልዩ ኃይል አባላት ሁሉ በከተማችን እየታሰሩ ነው” ብለዋል። ከተጠርጣሪዎች አያያዝ ጋር በተገናኘ ተጨማሪ አስተያየት የሰጡት ዶ/ር ካሳ፤ እስረኞች ምግብ “እንደማይቀርብላቸው” እንዲሁም “በጊዜ ወደ ፍርድ ቤት የማይቀርቡበት ሁኔታ” መኖሩን ጠቁመዋል።

በሸራ ቤቶች ይሰሩ የነበሩ “በርካታ የአማራ ተወላጆች”፤ “የጽንፈኛ ኃይሎች መደበቂያ ናቸው” መባላቸውንም የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባሉ አንስተዋል። ህጋዊ ሰነድ ያላቸው ግለሰቦችም መኖሪያ ቤታቸው እንደፈረሰባቸውም ዶ/ር ካሳ አክለዋል። ይህን ጉዳይ ያነሱት “ልዩነትን ለማጉላት” እንዳልሆነ የተናገሩት ዶ/ር ካሳ፤ ከዚያ ይልቅ “በተግባር ችግር ያለ ስለሆነ ‘እዚህ ላይ ምን ያህል ሚዛናዊነት አለ?’ የሚለውን እንዲብራራልኝ ስለምፈልግ ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።

“በሰዎች ላይ የምንፈጥረው ግፍ ነገ በአብሮነታችን ላይ አደጋ ነው” ያሉት የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባሉ፤ በጉዳዩ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። ምንም እንኳን ጉዳዩ በዋናነት የፌደራል መንግስት ቢሆንም፤ የከተማ አስተዳደሩ በጋራ ተባብሮ ስለሚሰራ ጥያቄውን ማቅረባቸውን አስረድተዋል። 

ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ ከሰጡ ኃላፊዎች መካከል አንዱ የሆኑት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነሩ ጌቱ አርጋው፤ በዶ/ር ካሳ የተጠቀሰውን አሃዝ “በተጋነነ መንገድ” የቀረበ ነው ብለዋል። የፖሊስ ኮሚሽነሩ “በሁከት እና ብጥብጥ” እንዲሁም “በሽብር” ተጠርጥረው የተያዙ ግለሰቦች ብዛት 2,724 መሆኑን ለአዲስ አበባ ምክር ቤት አባላት ተናግረዋል። የእነዚህ ተጠርጣሪዎች ጉዳይ በ1,296 መዝገቦች ተጠናቅሮ በመታየ ላይ መሆኑንም አስረድተዋል። 

ኮሚሽነር ጌቱ “ተቋሙ በእጁ የሌለውን መረጃ ለጉባኤው በዚህ መንገድ ማቅረብ ተገቢ ነው ብዬ አላስብም” ሲሉ በዶ/ር ካሳ በቀረበው አስተያየት ላይ የተሰማቸውን ቅሬታ ገልጸዋል። “በአብዛኛው እየታሰሩ ያሉት የአማራ ተወላጆች ናቸው” በሚል በምክር ቤት አባሉ የቀረበውን አስተያየትም፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር አጥብቀው አስተባብለዋል። “በፖሊስ ደረጃ የምንይዘው ብሔር ለይተን አይደለም” ያሉት ኮሚሽነሩ፤ “ከፋፍሎ ‘ይሄ ብሔር በዛ’ በሚል ማስቀመጥ የሚያስፈልግ አይመስለኝም” ሲሉ ትችቱን አጣጥለውታል። 

ከሰብዓዊ መብት አያያዝ ጋር የቀረበውን አስተያየት በተመለከተም፤ “በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተብሎ የቀረበው ነገር መታረም አለበት ብዬ ነው የማስበው” ሲሉ ኮሚሽነር ጌቱ ተናግረዋል። ለዚህም እርሳቸው የሚመሩትን ተቋም አሰራር የፈተሸው የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ፤ ከሰብዓዊ መብት ጋር በተያያዘ በጥሰት የሚገለጽ ግብረ መልስ አለመሰጠቱን በአስረጂነት አንስተዋል።

ለእስረኞች የሚቀርበውን ምግብ በተመለከተ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለመደበኛ እስረኞች ከተፈቀደው በጀት በላይ “ለዚህ ኃይል” እያዋለ መሆኑን በመጥቀስ ኮሚሽነር ጌቱ በተቋማቸው ላይ የቀረበውን ትችት ተከላክለዋል። “አንዳንድ ጊዜ ተቋምን በዚህ ደረጃ ጥላሸት መቀባት፤ ለህዝብ እየሰራ የሰላም እና ጸጥታን እያረጋገጠ ያለ ተቋምንም በዚህ ደረጃ ያልሆነ ስያሜ መስጠት ተገቢ መስሎ አይታይም። ይሄ መስተካከል አለበት” ሲሉ የፖሊስ ኮሚሽነሩ በአጽንኦት ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)