የ51 የሽብር ወንጀል ተከሳሾችን ጉዳይ የሚመለከቱ ዳኛ በሌላ መተካት፤ በችሎት ቅሬታ አስነሳ 

በሃሚድ አወል

አምስት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን ጨምሮ የ51 የሽብር ወንጀል ተከሳሾችን ጉዳይ ከሚመለከቱት ዳኞች መካከል አንዱ መቀየራቸው በተከሳሾች እና ጠበቆቻቸው በኩል ቅሬታን አስነሳ። ጉዳዩን በተለመከተ በጽህፈት ቤት ቅሬታ የቀረበላቸው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት፤ “ዳኞችን መቀየር የፍርድ ቤቱ አስተዳደር ስልጣን ነው” ሲሉ ለጠበቆች ምላሽ ሰጥተዋል ተብሏል።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሶስተኛ የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ችሎት ለዛሬ ሰኞ ሐምሌ 3፤ 2015 ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው፤ ተከሳሾች ባቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት ነበር። ሆኖም በመቅረጸ ድምጽ የተቀዳው የባለፈው የችሎት ውሎ ሂደት ዘግይቶ በመገልበጡ እና አንዱ የችሎት ዳኛ በመቀየራቸው ትዕዛዙ አለመድረሱን ተናግረዋል።

በሃምሳ አንዱ ግለሰቦች ላይ በይፋ ክስ ከተመሰረተበት ከሰኔ 1፤ 2015 ጀምሮ መዝገቡን ሲመለከቱ የቆዩት ሶስት ዳኞች ሲሆኑ፤ ከእነርሱ መካከል የግራ ዳኛው በዛሬው ችሎት በሌላ ዳኛ ተተክተው ታይተዋል። ዛሬ በአካል ችሎት ፊት ከቀረቡት 23 ተከሳሾች መካከል የመናገር ዕድል የተሰጣቸው አምስት ተከሳሾች፤ ባቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ላይ ፍርድ ቤቱ ዛሬ ትዕዛዝ ሊሰጥ አለመቻሉ እንዳሳዘናቸው  ገልጸዋል።

“ኢትዮ ንቃት” የተሰኘው የዩ-ቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት የሆነችው መስከረም አበራ፤ “ውሳኔ ጠብቄ ነበር የመጣሁት” ስትል ተናግራለች። የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዋ “ለምን ዳኛ እንደተቀየረ ሊነገረን ይገባል” ስትል እሷ የተካተተችበትን መዝገብ ሲመለከቱት የቆዩት ዳኛ የተቀየሩበት ምክንያት ምን እንደሆነ ችሎቱን ማብራሪያ ጠይቃለች። መስከረም ሌላው ማብራሪያ የጠየቀችበት ጉዳይ፤ የባለፈው ቀጠሮ መቅረጸ ድምጽ “ያልተገለበጠበትን” ምክንያት ነው።

እንደ መስከረም ሁሉ ከዳኛ መቀየር ጋር ተያያዥ ጥያቄ ያቀረበው “የአማራ ድምጽ” የተባለው በዩቲዩብ የሚተላለፍ የግል መገናኛ ብዙኃን መስራች የሆነው ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ነው። “እኛ የምንፈልገው የተፋጠነ ፍትህ ማግኘት ነው” ያለው ጋዜጠኛ ጎበዜ፤ “ዳኛው የተቀየሩበት ምክንያት ይነገረን” ሲል ጠይቋል። እንደ ሁለቱ ተከሳሾች ሁሉ ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻውም በተመሳሳይ ከዳኛ መቀየር ጋር ያለውን ቅሬታ አቅርቧል። የ“አራት ኪሎ ሚዲያ” የዩ ቲዩብ መገናኛ ብዙሃን መስራች ጋዜጠኛ ዳዊት፤ “መዝገቡን የሚያውቁት ዳኛ ቢመጡ አይሻልም ወይ?” የሚል ጥያቄ ለችሎቱ አቅርቧል።

ለተከሳሾች ጥያቄ እና ቅሬታ ምላሽ የሰጡት የመሃል ዳኛ “በምን ተቀየረ የሚለው የእኛ ስልጣን አይደለም” ብለዋል። “ከዳኛ ቅየራ ጋር ተያይዞ የአመራሮች ስራ ስለሆነ አይመለከተንም፤ አናውቅም” ሲሉ ጉዳዩ የፍርድ ቤቱ አመራር ስልጣን መሆኑን አብራርተዋል። ከመቅረጸ ድምጽ ጋር በተያያዘ ለተነሳው ጥያቄም፤ መቅረጸ ድምጹ ዘግይቶ ከመገልበጡ በተጨማሪ አንደኛው ዳኛ በመቀየራቸው “በጉዳዩ ላይ ለመወያያት” ጊዜ እንዳልበቃቸው አስረድተዋል።

የመሃል ዳኛው ይህን ማለታቸውን ተከትሎ ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው፤ “አስቸኳይ ፍትህ እንደምናገኝ አስበን ነው የምንመጣው። [ዳኞችን]  አመራሮች ከሆኑ የሚመድቡት፤ በእኛ የፍትህ ሂደት ላይ ችግር ይፈጥርብናል” ሲል ስጋቱን ገልጿል። ጋዜጠኛው ያቀረበው ስጋት ላይ አስተያየትም ሆነ ምላሽ ያልሰጠው ፍርድ ቤቱ፤ ለሐምሌ 12፤ 2015 ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት የዛሬውን የችሎት ውሎ አጠናቅቋል። 

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሶስተኛ የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ችሎት፤ በቀጣዩ ሳምንት ረቡዕ በሚውለው ቀጠሮ በተከሳሾች የዋስትና ጥያቄ ላይ ትዕዛዝ እንደሚሰጥ አስታውቋል። ከዛሬው የችሎት ውሎ መጠናቀቅ በኋላ ሶስት የተከሳሾች ጠበቆች ከዳኛው መቀየር ጋር በተያያዘ ቅሬታቸውን ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሌሊሴ ደሳለኝ አቅርበዋል። ጠበቆቹ በዚሁ ጉዳይ ላይ ከፕሬዝዳንቷ ማብራሪያ መጠየቃቸውን ከጠበቆቹ አንዱ የሆኑት አቶ ሄኖክ አክሊሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

የዳኛው መቀየር “የተከሳሾችን የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብት የሚጎዳ” መሆኑን በመግለጽ ቅሬታቸወን እንዳቀረቡ አቶ ሄኖክ ጨምረው ገልጸዋል። ከሶስት ወራት በፊት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት ሌሊሴ፤ “ዳኛ መቀየር የፍርድ ቤቱ አስተዳደር ስልጣን ነው” የሚል ምላሽ ለጠበቆች መስጠታቸውን አቶ ሄኖክ አመልክተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)