የመከላከያ ሰራዊትን “ከፋኖ ጋር የሚያዋጋ አጀንዳ አለመኖሩን” ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ

በአማኑኤል ይልቃል

የመከላከያ ሰራዊት አባላት “የፋኖ” ታጣቂዎችን “በመምከር ወደ ህዝባቸው እንዲመለሱ” እንዲያደርጉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጥሪ አቀረቡ። የመከላከያ ሰራዊትን “ከፋኖ ጋር የሚያዋጋ አጀንዳ አለመኖሩን” ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ተናግረዋል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ይህንን የተናገሩት ዛሬ ማክሰኞ ሐምሌ 4፤ 2015 በጅማ ከተማ በተካሄደው የሰራዊቱ የማዕከላዊ ዕዝ ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር ነው። የመከላከያ ሰራዊቱ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ካሉ ታጣቂዎች ጋር የሰላም ንግግሮችን በማድረግ “ሰላም እንዲፈጠር” ማድረጉን ያነሱት ኤታማዦር ሹሙ፤ የ“ፋኖ” ታጣቂዎችን ጉዳይም ከዚሁ ጋር አያይዘው ጠቅሰዋል። 

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ “ፋኖ በሚል አማራ ክልል ላይ የነበረውን እንቅስቃሴ በአብዛኛው በሰላም ወደ ቤተሰቡ እንዲመለስ ያደረገው መከላከያ ነው። በጣም ብዙ ሺህ የፋኖ አባላት ነው የነበረው” ብለዋል። የፋኖ አባላትን ወደ “ወደ ሰላማዊ ህይወት እንዲመለሱ ለማድረግ” ተቀምጦ የነበረው አማራጭ፤ ኤታማዦር ሹሙ “ጽንፈኛ ኃይል” ሲሉ በጠሩት ኃይል ተቀልብሶ እንደነበር ተናግረዋል። ይኸው ኃይል “ትጥቅህን ልትፈታ ነው” የሚል “ፕሮፓጋንዳ” በማሰራጨቱ ምክንያት “መንግስት ላይ መተኮስ የጀመሩ ፋኖዎች” መፈጠራቸውን ገልጸዋል።

በጫካ ከነበሩ የ“ፋኖ አባላት” መካከል፤ በሀገር ሽማግሌዎች እና በሃይማኖት አባቶች በተደረገ ጥረት “በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ” ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ህይወት መመለሳቸውን ኤታማዦር ሹሙ በዚሁ ንግግራቸው አስታውቀዋል። “እኛ የቀሩትም እንዲመለሱ ነው የምንፈልገው። ከፋኖ ጋር መዋጋት አንፈልግም። ምንም አጀንዳ የለንም። ከፋኖ ጋር የሚያዋጋን አጀንዳ የለንም” ሲሉም አክለዋል። የመከላከያ ሰራዊት አባላት የፋኖ አባላትን በመምከር፤  “የሌላ መገልገያ እንዳይሆኑ፣ ወደ ህዝባቸው እንዲመለሱ” እንዲያደርጉም ጥሪ አስተላልፈዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ የፋኖ አባላት “የህዝባቸውን ሰላም በማስከበር ወይም በመሳተፍ እንዲያስተካክሉ፤ መታጠቅ ከፈለጉ ደግሞ ወደ ፌደራል ፖሊስ፣ ወደ መከላከያ እና ወደ ክልል ፖሊስ እንዲገቡ መምከር ያስፈልጋል” ሲሉ በመደበኛ የጸጥታ መዋቅር ውስጥ መቀላቀል እንደሚችሉ ጠቁመዋል። ኤታማዦር ሹሙ ታጣቂዎቹ ሰላማዊ መንገድን ከመረጡ አሁንም አማራጮች እንዳሏቸው ጥቆማ ቢሰጡም፤ “በፋኖ ስም የሀገሪቱን ጸጥታ ማደፍረስ አይቻልም” ሲሉም ተደምጠዋል። “ያን ጊዜ እንጣላለን” ሲሉም አስጠንቅቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)