የአካባቢ ምርጫን በቀጣዩ ዓመት ለማካሄድ፤ በጀትን ጨምሮ ሌሎች “አስፈላጊ ነገሮች” መመቻቸት እንዳለባቸው ምርጫ ቦርድ ገለጸ 

በሃሚድ አወል

ለመጨረሻ ጊዜ በ2005 ዓ.ም የተካሄደውን የአካባቢ ምርጫ፤ ገንዘብን ጨምሮ “አስፈላጊ ነገሮች” ከተመቻቹ በሚቀጥለው ዓመት ለማካሄድ መታቀዱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ ተናገሩ። የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች በበኩላቸው በአካባቢያዊ ምርጫ አሸንፈው የታችኛው መዋቅር ምክር ቤቶችን መያዝ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

የአካባቢ ምርጫ በፌደራል መንግስት የ2016 በጀት ዝርዝር ውስጥ ባይካተትም፤ ትላንት ማክሰኞ ሐምሌ 4፤ 2015  በምርጫ ቦርድ አዘጋጅነት በተካሄድ ውይይት ላይ ግን አንድ የመወያያ አጀንዳ ሆኖ ተነስቷል። ምርጫ ቦርድ በተያዘው 2015 የአካባቢ ምርጫ ለማካሄድ አቅዶ 6 ቢሊዮን ብር ገደማ በጀት ጠይቆ  የነበረ ቢሆንም፤ በበጀት ዓመቱ በተወካዮች ምክር ቤት የተመደበለት በጀት ግን 212 ሚሊዮን ብር ብቻ ነበር። 

የፌደራል መንግስት ባለፈው ሳምንት በተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀለት የ2016 በጀት ዝርዝር ላይ የአካባቢ ምርጫ በድጋሚ አለመካተቱ፤ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ በነበረ ስብሰባ ከፓርላማ አባላት ጥያቄ አስነስቶ ነበር። የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፤ በሚቀጥለው ዓመት የአካባቢ ምርጫ የሚካሄድ ከሆነ እና የሚመለከተው አካል እስከወሰነ ድረስ የገንዘቡ ጉዳይ “በበጀት አስተዳደር የሚታይ ይሆናል” ማለታቸው ይታወሳል።  

ከፓርላማው ስብሰባ አንድ ሳምንት በኋላ በአዲስ አበባው ኢንተርሌግዠሪ ሆቴል ትላንት በተካሄደ የምርጫ ቦርድ እና የፓርቲዎች ውይይት ላይ፤ የአካባቢ ምርጫ የተመለከቱ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች  በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በኩል ቀርበዋል። የአርጎባ ብሔረሰብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ሀሰን መሃመድ “የአካባቢ ምርጫ በጣም ሊታሰብብት የሚገባ ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የቦሮ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ የሆኑት የሆኑት ዶ/ር መብራቱ አለሙ፤ የአካባቢ ምርጫ በቀጣዩ 2016 ዓ.ም እንዲካሄድ እንደሚፈልጉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። ዶ/ር መብራቱ “እኛ በጣም እንፈልገዋለን። ቢያንስ የታችኛው ምክር ቤት በተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲያዝ እንፈልጋለን” ሲሉ የአካባቢ ምክር ቤት በተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘንድ ያለውን አስፈላጊነት አብራርተዋል። 

ሆኖም የተቃዋሚ ፓርቱ አመራሩ የአካባቢ ምርጫ በቀጣዩ ዓመት መካሄድ ላይ ስጋት እንዳላቸው አልሸሸጉም። ለዚህ ስጋታቸው በምክንያትነት የሚጠቅሱት ደግሞ ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ምርጫውን ለማካሄድ ያላቸውን ቁርጠኝነት ነው። “አሁን በእውነት 2016 ላይ ወደ አካባቢ ምርጫ እንገባለን ወይ?” ሲሉም ጥርጣሬ አዘል ጥያቄያቸውን በስብሰባው ላይ አስደምጠዋል። 

የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ሰለሞን ታፈሰ በበኩላቸው፤ የአካባቢ ምርጫ ማካሄድ የሚኖረውን ፋይዳ አብራርተዋል። “ችግሮች ያሉት ታች ነው። የሰብዓዊ [መብት] ጥሰት ያለው ታች ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች ተከታይ ማግኘት የሚችሉት፣ አባላት ማፍራት የሚችሉት ታች ነው። ስለዚህ በእናንተም፣ በሌላውም በሚመለከተው [አካል] የአካባቢ ምርጫ እንዲደረግ እንድታበረታቱ ማለት እፈልጋለሁ” ብለዋል። 

የወለኔ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ፋይሰል አብዱልአዚዝ፤ ፓርቲዎች በሀገራዊ ምርጫ ተሳትፎ እንዲደርጉ በቅድሚያ የአካባቢ ምርጫ መደረግ እንዳለበት በአጽንኦት ተናግረዋል። አቶ ፋይሰል “የአካባቢ ምርጫ ሳይካሄድ ሀገር አቀፍ ምርጫ ማካሄድ የውሸት ነው የሚሆነው” ሲሉም የአካባቢ ምርጫ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ አስገንዝበዋል። 

ከአካባቢ ምርጫ ጋር በተያያዘ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ፤ “እኛ የአካባቢ ምርጫ እናደርጋለን ብለናል። ከዚህ በላይ የምለው ነገር የለም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። አቶ ውብሸት “የአካባቢ ምርጫ ለማድረግ ከገንዘብ ጀምሮ ብዙ አስፈላጊ የሆነ ነገር አለ። እነሱ የተመቻቹ ከሆነ፤ የራሳችንንን የአካሄድ ፕሮግራም አውጥተን እናካሄዳለን” ሲሉ የአካባቢ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ሊሟሉ የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ያሏቸውን ለተሰብሳቢዎቹ አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)