ኢሰመኮ በትግራይ ክልል የሰብዓዊ መብቶች ክትትል መጀመሩን ገለጸ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በትግራይ ክልል የሰብዓዊ መብቶች ክትትል መጀመሩን አስታወቀ፡፡ ኮሚሽኑ በመቐለ የሚገኘውን ቢሮ መልሶ የማቋቋም እና የማደራጀት ስራ መጀመሩንም ገልጿል፡፡

ኢሰመኮ በትግራይ ክልል ሰብዓዊ መብቶች ክትትል የጀመረው ለኮሚሽኑ እና ለተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ጽህፈት ቤት በፌደራል መንግስት ጥያቄ ከቀረበ በኋላ መሆኑን የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡ በትግራይ ክልል የሚደረገው የክትትል ስራ፤ “ከዚህ በፊት የተፈጸሙትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምርመራ ስራ አይደለም” ሲሉ ዋና ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡

ኢሰመኮ እያካሄደው ያለው ክትትል፤ በትግራይ “ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በአሁኑ ወቅት ያለው የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ምን እንደሚመስል ማጣራት” እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ “ይህ የክትትል ስራ በትግራይ ክልል ላይ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በጦርነት የተጎዱት አጎራባች የአፋር እና አማራ ክልሎችንም የሚመለከት ነው” ሲሉም አክለዋል፡፡ (በሃሚድ አወል – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)